የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?

ዶክተር አሸብር እያጠቁ ነው!

የቀድሞው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የአሁኑ ብቸኛው የግል የፓርላማ አባል፣ ምናልባትም የወደፊቱ ርእሰ ብሔር ዶ/ር አሸብር ከመሰናዘርያ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አቶ መለስ ዜናዊን ለማሞካሸት ትንፋሽም ቃላትም ያጠራቸው ይመስላል፡፡ ሁለት ገፅ ሙሉ በሚሸፍነው ቃለ ምልልሳቸው የአቶ መለስን ስም ያልጠሩበት አንቀፅ ለማግኘት ያስቸግራል፡፡

የዶን፣ የአልማታ፣ የማስተርዴንት የጥርስ ህክምና ማእከላት ባለቤት የሆኑት ዶክተሩ ሶስቱንም ማእከላት የሰየሙት በራሺያ ከተሞች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የመጀመርያ ልጃቸው ስምም ‹‹ዶን›› እንደሚባል ተናግረዋል፡፡ በኢንቨስመንት የመሰማራታቸው ሚስጥርም አቶ መለስና ኢህአዴግ በፈጠሩት ምቹ የልማት ሁኔታ እንደሆነ አልሸሸጉም፡፡ ‹‹በቅርቡ 30 የሚሆኑ የጥርስ ሀኪሞች ተመርቀው ስራ ስላላገኙ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ እንዳመለከቱ ነገሩኝ›› የሚሉት ዶክተር አሸብር በዚህም “በእጅጉ ተደናገጥኩ” ይላሉ፡፡ ‹‹ የዚህ አይነት ሁኔታ የሚያስወቅሰው እኛ በዘርፉ የተሰማራነውን ባለሀብቶች ነው እንጂ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊን አይደለም፡፡ መንግስት ማስተማር ነው ግዴታው›› ብዬ ለወጣቶቹ ካስረዳኋቸው በኋላ እኔ ጋር ቀጠርኳቸው›› ይሉናል፡፡

‹‹ፓርላማው ሰአት ሳይገድብ ለአገራችን የሚሆኑ ሀሳቦችን እንዳነሳ ሰፊ እድል ሰጥቶኛል፤ ለዚህም ገዥው ፓርቲና የተከበሩ አፈ ጉባኤን ከልብ አመሰግናለሁ›› ብለዋል ዶክተሩ፡፡ የስፖርቱ መዳከምን ዋንኛው ችግር ስፖርቱን ብቃት ባላቸው ሰዎች ያለመመራቱ እንደሆነ አስገንዝበው ‹‹አሁን ግን መንግስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ስፖርት ወዳዱን ህዝባችንና ባለሀብቶችን ከክብር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጀርባ በማሰለፍ የስፖርቱን ህዳሴ ለመፍጠር ወቅቱ አሁን ነው፡፡›› ሲሉም ከአቶ መለስ ጋር መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን ተንብየዋል፡፡

አገራችን የብዙ ብሔር ብሔረሰቦቸና ህዝቦች ሀገር ናት፡፡ የፕሬዝዳንትነቱ ወንበር ደግሞ አንድ ብቻ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ፕሬዝዳንት ካልሆንኩ ብዬ የማስብበትና የምጨነቅበት አንዳችም ምክንያት የለኝም፡፡የሚሉት ዶክተሩ የፓርላማ አባል መሆኑ በራሱ ከተወሰኑ ትልቅ ስኬትና አየጥጋቢ ውጤት ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህም የረካሁ ስለሆንኩ ሌላ ስልጣን እመመኝበት ምክንያት የለኝም፡፡›› ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ አብራርተዋል፡፡

ዶክተሩ ከሼክ አላሙዲን በተለይም ከረዳቶቻቸው ጋር እሰጣ አገባ ውስጥ በመግባት ይታወቁ ነበር፡፡ በቅርቡ ግን በፓርላማ ለሼኩ የምስጋና ቃል አዥጎድጉደውላቸዋል፡፡ ከአገሪቱ ቁጥር አንድ ባለሀብት ጋር ተቀያይሞ ወደ ፕሬዝዳንትነት ጉዞ ዳገታማ እንደሚሆን የገመቱ የሚመስሉት ዶክተሩ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ስለ ሼኩ ይህንን ብለዋል፡፡

‹‹ሼኩ ከመንግስት በመቀጠል ለዚች ሀገር ደከመኝ ሰለችኝ ሳይሉ ምንም ጥቅም ለማያገኙበት ስፖርት እያገዙ ያሉና የሀገሪቱ ስፖርት የጀርባ አጥንት ናቸው፡፡ በ2006 የአለም ህዝብ ጉድ እስኪል በእሳቸው ደረጃ ያሉ ሀብታሞች ያልፈጠሩትን ተአምር መፍጠር ቸልዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ከመቶ በላይ ዜጎቻችን ወደ ጀርመን የአለም ዋንጫ በመውሰድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሌለበት ሰንደቅ  ዓላማችን በጀርመን ስቴድየሞች እንዲውለበለብ አድርገዋል፡፡ በዚህም የአለም ህዝብ ጉድ እስከሚል ዜጎቻችን በአለም ዋንጫ ናኝተውበታል፡፡ ከዚህ መገመትና ማወቅ የቻልኩት የኢትዮጵያ ስፖርት ሼህ መሀመድን የመሰለ ዋስ ጠበቃ የሚሆን ለችግር ደራሽ ዜጋ በኢትዮጵያ እንዳልተፈጠረ ነው፡፡››

‹‹ አሁንም እንጠይቃለን ለምን መብራት ይቆራረጣል?››

ኢቴቪ በቅርቡ የገመና ድራማ ሽልማት በተካሄደበት እለት መብራት መቋረጡን ተከትሎ ‹‹ በመብራት መቋራጥ ምክንያት ህዝቡ እያማረረ ነው፡፡››  የሚል ዜና ባልተለመደ ሁኔታ ማቅረቡን ሰንደቅ ጋዜጣ አስታውሶ በሚመለከታቸው አካላት የሚሰጠው መልስ ግን አሁንም አጥጋቢ አለመሆኑን በርእሰ አንቀፁ ጽፏል፡፡ ግልገል ጊቤ ሁለት ከ11 ወራት በኋላ ተጠግኖ  ሥራ ጀምሯል፡፡ ሆኖም አሁንም ድረስ ‹‹በቂ አቅርቦት አለ ችግሩ የቴክኒክ ነው›› የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ህብረተሰቡ አስቀድሞ እንዲዘጋጅ ለምን እንደማይነገረው ግን አሁንም ድረስ ግልፅ አይደለም” ይላል ሰንደቅ፡፡ ያለውን ችግር ፍርጥ አድርጎ ለህዝብ ማሳወቅ ሚስጥር እንደማባከን አድርጎ የሚያይ የህዝብ ግንኙነት ስትራቴጂ ትክክል አይደለም የሚለው ጋዜጣው ‹‹አሁንም እንጠይቃለን፣ ለምን መብራት ይቆራረጣል?›› ሲል ርእሰ አንቀፁን ይደመድማል፡፡

‹‹ጆሊ ባር›› ራሱን ወደ መካከለኛ ገቢ አሳደገ

በ1959 አንደተመሰረተ የተነገረለት ታሪካዊው ጆሊ ባር የዛሬን አያድርገውና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች የጋዜጣ ጥም ማርኪያ ነበር፡፡ በድሮው ጊዜ ደግሞ በተለይም የእድሜ ባለፀጎች ይህንን ቤት ሻይ ቡና የሚሉበት፣ የሆድ የሆዳቸውን የሚጫወቱበት ልዩ ስፍራ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ፎርቹን ባሳለፍነው እሁድ እንደፃፈው ‹‹ጆሊ ባር›› ፍፁም ልዩ እድሳት ተደርጎለት ራሱን ለመካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች እንዲሆን አድርጎ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ከሶስት አመታት እድሳት በኋላ ስሙንም ‹‹ጆሊ ባር ኤንድ ግሪል›› በሚል ለውጦታል፡፡ አያሌ የፈረንጅ ምግቦችን በፈረንጅ ምግብ እብሳዮች ከሽኖ ያቀርባል፡፡ ይጠንቀቁ! አንድ ቢራ በጆሊ ባር 30 ብር ያስከፍላል፡፡

ባምቢስ ራሳቸውን ሳቱ

የዝነኛው ባምቢስ ሱፐርማርኬት ባለቤት ሚ/ር ካራላንቦስ ባምቢስ 87 ሚሊዬን ብር ታክስ አልከፈሉም ተባሉ፡፡ አምነው አስተያየት አድርጉልኝ አሉ፡፡ እድሜያቸውንና ለአገር ያበረከቱትን አስተዋፀኦ ከግምት በማስገባት 34 ሚሊዬን ብር ቅጣት ተቀነሰላቸው፡፡ የታክስ እዳው እንደሚያሳስራቸው ሲነገራቸው ቢሮ ውስጥ ራሳቸውን ስተው ባልቻ ሆስፒታል ለአንድ ቀን እንደተኙ ታውቋል፡፡ ግሪካዊው ባምቢስ ኢትዮጵያ የመጡት በ1944 ሲሆን አሁን የ80 አመት የእድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ የረቡእ ሪፖርተር ጋዜጣ ነው ይህን የዘገበው፡፡

ተዋናይ ሰለሞን ቦጋለና አቶዝ መኪናው

ከቅርብ አመታት ወዲህ ስሙ በፊልም እየገነነ የመጣው ሰለሞን ቦጋለ ከሳምንታዊው አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር፡፡ ‹‹አባይ ወይስ ቬጋስ›› በተሰኘው ፊልም ያሳየው ብቃት ከፕሮዲዩሰሩ የአቶዝ መኪና እንዲሁም ከኤድናሞል ባለቤት የ20ሺህ ብር ሽልማት አስገኝቶለታል፡፡ ምርቃቱ በቴሌቪዥን ለኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ የተላለፈው ይኽው ፊልም ላይ ሰለሞን የአቶዝ መኪና ተሸላሚ እንደሆነ ሲነገረው ፊቱ ላይ ምንም የመደነቅ ስሜት አላሳየም ነበር፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ተጠይቆ ‹‹ገና ባህርዳር እያለን ቴዲ መኪና እንደሚሸልመኝ ነግሮኝ ነበር›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የተሸለማት መኪና የተነዳችና 80ሺህ ቤት ታርጋ እንደሆነች ተናግሯል፡፡ ተጨማሪ ክፍያ እንዳልተሰጠውና ክፍያው በመኪናው እንደተጣጣ አልሸሸገም፡፡ አቶዝ ከተማ ውስጥ ጥሩ ስም እንደሌላት ገልፆ ‹‹ሆኖም የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም›› ሲል ለሽልማቱ አቃቂር ማውጣት እንደማይፈልግ ለአውራምባ ተናግሯል፡፡

ተዋናዩ የኢህአዴግ አራቱን አባል ድርጅቶችን ያውቃቸው አንደሆን በጋዜጣው ሪፖርተር ተጠይቆ እንደማያውቃቸው የተናገረ ሲሆን የአፋር ዋና ከተማ ማን እንደሆነች ሲጠየቅም ማስታወስ ተስኖታል፡፡

አስቴር አወቀና የ‹‹ፖለቲካ አቋሟ››

አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ በፊት ገፁ የአስቴር አወቀ ፖለቲካው አቋም ዲያስፖራውን እያወዛገበ እንደሆነ ጽፏል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንፀባርቃዋለች በተባለው ፖለቲካዊ አቋም ፖልቶኮችና ድረገፆች ባካሄዱት ቅስቀሳ በዋሽንግተን ዲሲ ያሰናዳቸው ኮንሰርቷ የተመልካች ድርቅ እንደመታው ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ ድምፃዊቷ በብአዴን 30ኛ አመት ክብረ በአል ላይ ስሟ መጠቀሱ እንዳላስደሰታቸው ይገመታል ይላል ዘገባው፡፡ ከዚህ በላይ አስገራሚ የሆነው ደግሞ አስቴር በቅርቡ ያሳተመችው ‹‹ጨጨሆ›› አልበም በነዚህ ድረገፆች  ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶት መገኘቱ ነው፡፡ጨጨሆ ጎንደር ሀሙሲት ውስጥ የምትገኝ የአቶ አዲሱ ለገሰ የትውልድ ስፍራ በመጥቀስ ‹‹ለተሰናባቹ የብአዴን ሊቀመንበር የቀረበ ውዳሴ ነው›› ሲሉ የተቃውሞ ቅስቀሳ አካሄደውባታል፡፡ በዚሁ አልበም ላይ ‹‹ የንብ አውራ መሳይ›› የሚል አረፍተነገር መኖሩም ፖለቲካው ትርጉም ተሰጥቶት ኢትዪጵያዊያን በኮንሰርቷ እንዳይገኙ አድርጓቸዋል ይላል ዘገባው፡፡

የአገር ቤት ምርቃት

ኢትዬ ቻናል፡- ከቴአትር ስራ ወጥተሸ መኖር ትችያለሽ?

ሀረገወይን አሰፋ፡- አዎን እችላለሁ፡፡

—-

‹‹አበበ ግደይ ለሸገር ፈረመ›› እንቁ መፅሄት

—-

‹‹ቴሌ ዘጠኝ ሺህ ሰራተኞችን ቀነሰ፡፡ ሰንደቅ ጋዜጣ

‹‹ውይ በእናትህ አታዋርደኝ፡፡ እኔ የባለስልጣን ስም…(ራሷን ያዘች)፡፡ አቶ ስዩም መስፍን ናቸው? /እየሳቀች/ ናቸው፤ በእውነት ናቸው፡፡ ልክ ነኝ አይደል?››

ተወናይት ሜሮን ጌትነት አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ  አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማን ይባላሉ ብሎ ለጠየቃት ጥያቄ የሰጠችው ምላሽ፡፡

—-

‹‹ጌቱ ገለቴን ከወንጀል ክስ አለአግባብ ነፃ አድርገዋል የተባሉ ዳኛ ከስራቸው ተሰናበቱ፡፡››

ሰንደቅ ጋዜጣ

‹‹ከንፈሩ ላይ ባልስመው ኖሮ ‹ሲኑ› ይበላሽ ነበር››

አርቲስት ብሌን ማሞ ደማቅ ቀይ የከንፈር ቀለም ተቀብታ ማራኪ በተባለ ወርሃዊ  መጽሔት የፊት ገጽ ላይ የተናገረቸው፡፡

—‹‹መክፈል አለብህ ብለው ከወሰኑ ሱፐርማርኬቱንና ቤቴን ሽጬ አገሬ እገባለሁ፡፡››

ከፍተኛ የግብር እዳ እንዲከፍሉ የተጠየቁት የባምቢስ ሱፐርማርኬት ባለቤት ሚስተር ባምቢስ ለሪፖርተር ጋዜጣ

‹‹አስቸጋሪ ስለነበርኩ በኤችአይቪ መያዜ ሲያንሰኝ ነው፡፡››

አቶ ዘላለም አሸናፊ የተባሉ ግለሰብ ለእንቁ መፅሄት የተናገሩት

የሳምንቱ አስገራሚ ዘገባ

‹‹አር ኬሊ ከቦሌ ወደ ተዘጋጀለት መኪና ሲያመራ ፊቱ ላይ ጥሩ ስሜት ይነበብበት ነበር፡፡››

ኢቲቪ ከትናንት በስቲያ ምሽት ሁለት ሰአት በዋና የዜና እወጃው የ ‹‹አር ኤንድ ቢ›› አቀንቃኙ አርኬሊ ኢትዮጵያ መግባቱን አስመልክቶ ያቀረበው ዘገባ፡፡

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

2 Responses to “የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?”

  1. ‹‹አር ኬሊ ከቦሌ ወደ ተዘጋጀለት መኪና ሲያመራ ፊቱ ላይ ጥሩ ስሜት ይነበብበት ነበር፡፡›› bewuketu sesemaw betam betam betam askagnalech…..aye ETV meche yehon ken yemiwotaleh??

  2. ETV IS SHEMLESS.GOD BLESS ETHIOPIA.

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.