hailu_shawol 1

“ጠቅላለ ጉባዔው ያለ ውድድር ኢንጂነር ኀይሉ ሻውልን በለቅሶ እና በደስታ በፕሬዝዳንትነት እንዲቀጥሉ አድርጓል”

(ሙሉ  ገ.)

ታኅሳስ 17 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ለሁለት ቀን ያደረገውን 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሲያጠናቅቅ  “በጤንነት እና በዕድሜ ምክንያት ውልጣናቸውን ለተተኪ ወጣት ማስረከብ” እንደሚፈልጉ ሲናገሩ የነበሩት  ኢንጂነር ኀይሉ ሻውል ብቻቸውን ተወዳድረው በድጋሚ የፓርቲው ፕሬዝዳንት መኾናቸውንም አሳውቋል።  አቶ ያዕቆብ ልኬ ደግሞ የፓርቲው  ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ኾነው ተመርጠዋል።

ፓርቲው  እሁድ ምሽት በአይቤክስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው “የፓርቲው ፕሬዝዳንት በቀጥታ በጠቅላላ ጉባዔው የሚመረጡ ሲኾን ለዕጩነት የቀረቡ የላዕላይ ም/ቤት አባላት ለጠቅላላ ጉባዔው ቢቀርቡም፤ ጠቅላላ ጉባዔው  ያለ  ውድድር አቶ ኀይሉ ሻውልን በለቅሶ እና በደስታ በፕሬዝዳንትነት እንዲቀጥሉ አድርጓል” ብሏል።  ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ለፓርቲው የሥራ አስፈሚ ኮሚቴ አባልነት ኢንጂነር ኀይሉ ሻውል፣ አቶ ያዕቆብ ልኬ፣ ዶክተር ታዴዎስ ቦጋለ፣ አቶ ማሙሸት አማረ፣ አቶ እንድርያስ ኤሮ፣ አቶ ገለቱ ጀጀርሳ፣ አቶ በለጠ ገብሬ፣ ወ/ሮ መሠሉ ረዳ፣ አቶ አዳሙ  ተሰማ፣ ኢንጂነር ሽፈራው ዋለ፣ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፣ አቶ ብዙዐየን ገብረ ማርያም፣ አቶ ብርሃኑ ወ/ሰንበት፣ አቶ አብርሃም ጌጡ፣ አቶ ብሩ ዲሲሶ፣ ዶክተር በዛብህ ደምሴ፣ አቶ ዐየናቸው ተፈሪ፣ አቶ ጌታቸው ባያፈርስ እና ኮሎኔል ታምሩ ጉልላትን መርጧል።  የፓርቲው ዋና ጸሐፊ፣ የድርጅት ጉዳይ ሐላፊ፣ የውጭ ጉዳይ ሐላፊ፣ የአስተዳደርና የፋይናንስ ጉዳይ ሐላፊ እና ሌሎች የሥልጣን ቦታዎች ሹመት በይደር ታልፏል፡፡

ከዚህ ጋራ በተያያዘ የቀድሞ የመኢአድ ሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ የነበሩት ወይዘሮ መሶበወርቅ ቅጣው የሚገኙበት ዐሥራ ሦስት የሚኾኑ አባላት ያሉት፤ ራሱን “የመኢአድ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” ብሎ የሰየመው ቡድን እሁድ ምሽት ላይ በአይቤክስ ሆቴል በር ላይ በመሰብሰብ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።  ኮሚቴው  በመኢአድ አመራር  ውስጥ ይሠራል ያለውን ሕገ-ወጥ አሠራር እንደሚቃወም አሳውቋል። “ አባላትን ያለአግባብ የማገድ እና የማባረር፣ በፓርቲው ውስጥ ጠንካራ ሰዎች እንዳይሠሩ እንቅፋት በመፍጠር፣ የፓርቲውን ሥራ በአግባቡ እንዳይከናወን በማድረግ፣ በጥቅም በመተሳሰር ቡድን በመፍጠር፣ በጎጥ በመሰባሰብ መንደርተኝነትን በማስፋፋት እኩይ ተግባራትን ያከናውናሉ” ሲል ኮሚቴው  በመኢአድ አመራር አባላቶች ላይ ቅሬታ አቅርቧል። ኢንጂነር ኀይሉ  ሻውል “ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጣቸውን የመሪነት ዕድል በመጠቀም ፍትኀዊ ተግባራትን እንዲያከናውኑ እና ቀደም ሲል የፈጸሟቸውን ስኅተቶች የማስተካከል ታሪካዊ ግዴታ እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል” ብሏል።

የመኢአድ ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ያዕቆብ ልኬ በበኩላቸው “እነዚህ ሰዎች የፓርቲው ጽ/ቤት እያለላቸው በየቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ በመሰባሰብ ስለ መኢአድ ሲነጋገሩ የአንጃ ዐይነት ባሕርይ በማሳየታቸው በዲስፕሊን ጉድለት ከፓርቲው የታገዱ እና የተወገዱ ናቸው፤ መኢአድን ለሦስት እና ለአራት ተከፍሏል ብለው አሉባልታ የሚያስወሩትም እነርሱ ናቸው”  ብለዋል።

የመኢአድ ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ያዕቆብ ልኬ  እንደተናገሩት “ ሥራ አስፈጻሚው ውስጥ  ነበርኩ፣ ያለ አግባብ የተባረረ አንድም አባል የለም፤ ጥፋታቸውን አውቀው ይቅርታ እንዲጠይቁ አሊያም ለበላይ አካል ያቅርቡ ብለን መልስ ሰጥተናል። እነርሱ ግን ይሄን ሳያደርጉ ሥራ አስፈጻሚውን ሰድበው ጽፈዋል፤ እነርሱ ታገዱ እንጂ ከፓርቲው አልተባረሩም ነገር ግን የፓርቲውን ሕገ ደንብ ካላከበሩ አይመለሱም ብለዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከታኅሳስ 16 – 17 ቀን 2003 ዓ.ም ባደረገው 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከ55 ዞኖች እና ከ360 ወረዳዎች 420 የወረዳ እና የዞን የመኢአድ አመራሮች በአዲስ አበባ አይቤክስ ሆቴል መሳተፋቸው ታውቋል።

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email