ይቅር ባይ፣ ይቅር ተባይ፣ ይቅር አባባይ አሉ? ይቅርታና እርቅስ?

የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በይቅርታ ከእስር ሊፈቱ ነው ሲባል ዓመታት ተቆጥረዋል። የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር የአራት ሃይማኖቶች መሪዎች ለዚሁ ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን መግለጻቸውና ተስፋ መስጠታቸው ብቻ ነው። የይቅርታው ወሬ በስፋት መነገር እንደጀመረ ከየአቅጣጫው የሚሰማው አስተያየት ግን ሌሎችንም ተመሳሳይ አጋጣሚዎችን የሚያስታውስ ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት አቶ ስየ አብርሃ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ሌሎቹም “ይቅርታ ካልጠየቁን” የሚለው ጥያቄ በተቃዋሚው ጎራ የፖለቲካው ማጠንጠኛ እስኪመስል አሰልችቶን እንደነበር አይዘነጋም። ብዙዎቹ ይቅርታ መጠየቁን የፈለጉት ለፖለቲካዊ ዓለማ፣ የአሸናፊነት ጥማታቸውን ለመወጣት፣ “አሳየናቸው” ብሎ ለመመጻደቅ እንጂ ስለ እርቅ ወይም እርሱ ስለሚያስከትለው ውጤት የምር አስበውበት አይደለም። በሌላ በኩል አቶ መለስና ደቀ መዝሙሮቻቸው “ይቅርታ የሚባል ነገር የለም” እያሉ ሲፎክሩ ከርመው “ድንገት” ከ“ይቅር ባዮች” ብጽእና ለመሰቀል ሲሞክሩ ታዝበናል።

በተመሳሳይ አጋጣሚዎች የሚፈጸሙት ድርጊቶች እና የሚሰሙት አስተያየቶች እንደማኅበረሰብ ይቅርታን አሸናፊነትን የማሳያ ተራ መሳሪያ አድርጎ ከመመልከት አለመላቀቃችንን የሚያሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ኢሕአዴግ ባለፉት አምስት ዓመታት “ይቅርታ እና እርቅ” የሚሉት ጽንሰ ሐሳቦች ገና ቤተ መንግሥቱ አካባቢ ዝር አለማለታቸውን በተግባር አሳይቶናል። በቅርቡ ብርቱካን የተፈታችበት ሁኔታ በፖለቲካ መዋቅራችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰቡም ውስጥ ጥልቅ የአስተሳሰብ ችግር እንዳለ ያለተጨማሪ ማስረጃ የሚያረጋግጥ ነው። ከመንግሥት ውጭ ያለው አካልም የዚሁ በሽታ ተጠቂ ነው።

አንድ ጥፋተኛ የተባለ ወይም የሆነ ሰው “ይቅርታ” “ጠይቆ” ከእስር ወይም ከሌላ ዓይነት ቅጣት “ነጻ” መደረጉን በራሱ የሚቃወም ሰው ብዙ አይገኝም። ቁም ነገሩ ያለው ይቅር ባዩ “ስለጥፋቱ” ወይም አጠፋ ስለተባለው ነገር የደረሰበት ልባዊ ድምዳሜ፤ ይቅርታውን የሚጠይቅበት ምክንያት እና ፋይዳው ብቻ አይደለም። ይቅርታ ተጠያቂው እና አድራጊውም ወገን ደረሰብኝ ስለሚለው ጉዳት ብቻ ሳይሆን ስለጉዳቱ አድራሽ፣ ይቅርታውን ስለሚሰጥበት የሞራል እና የሕግ መሠረት እንዲሁም ስለይቅርታው ተናጠላዊና ሁለንተናዊ ፋይዳ የሚኖረው እምነትና ግብ የይቅርታውን ምንነት በተጨባጭ ይወስነዋል። ብዙውን ጊዜ ደግሞ በሁለቱ መካከል ይቅር አባባዮች አሉ። የእነርሱ ማንነት፣ የሞራል ተቀባይነት፣ በተግባር ለሕሊናዊ ዳኝነት የሚሰጡት ቦታ እና ከእርቁ ውጤት የሚፈልጉት ነገርም እንዲሁ እርቁን እርቅ የሚያደርግ፤ አለዚያም ድራማ የሚያሰኝ ሊሆን ይችላል።

አንድ ነጥብ በድጋሚ ላስረግጥ፤ እነዚህ በሦስቱም ወገኖች ዘንድ ሊፈተኑ የሚገባቸው ነገሮች ተሟሉም አልተሟሉም እንዲሁ “በሰብአዊነት” ብቻ የታሰረ “ከተጸጸተና ይቅርታ ከጠየቀ” መፈታቱን መደገፍ ከእርቅና ከይቅርታ ጥልቅ ሞራላዊና ስነልቦናዊ ትርጉምና ውጤት ጋራ ተፈጥሯዊ ግንኙነት ላይኖረው ይችላል። እንዲህ ሲሆን ይቅርታ ጠያቂውም፣ ሰጪውም ሆነ አሸማጋዩ ወገን (አንዱ ወይም ሁሉም) ድራማ እየሠሩ እንኳን ቢሆን እነርሱ ብዙዎቻችን በተግባር የማናውቀውንና የማናደርገውን የይቅርታ መንፈስ ተጋሪዎች ሊሆኑ አይችሉም። እርቁም ቁስልን የሚያጠግ “መድኀኒት” ሊሆን አይችልም። ለዚህም ነው እርቅ ጀግንነት ነው የሚባለው፤ ሕሊናና ልብ በአንድነት ቆርጠው ካልገቡበት የማይደረስበት ልእልና ስለሆነ። ማራኪ ምርኮኛውን በነጻ ሊለቀው ይችላል፤ ይህ ማለት ግን በመካከላቸው እርቅ ወርዷል ማለት አይደለም። ምርኮኛ “ይቅርታ ጠይቅ” ተብሎ ይቅርታ ቢጠይቅ፣ ማራኪው “ይቅር አልኩ፤ ታረቅኩ” ብሎ ሊናገር ይችላልን? ውለታና እርቅ ለየቅል ናቸው።

ቀደም ሲል በገለጽኩት የሰብአዊነት መሠረት የደርግ ባለሥልጣናት እንዲፈቱ የሚፈልጉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ተቃራኒውን ድምጽ ከሚያሰሙት በብዙ እጥፍ እንደሚበልጡ እገምታለሁ። እኔም መፈታታቸውን የምደግፈው ነው። ከዚህ ባለፈ ግን ይቅር ተባዮቹ (ይቅርታ ጠያቂዎቹ)፣ ይቅር ባዮቹ እና አባባዮቹ በተመሳሳይ የመንፈስ ደረጃ ያሉ አልመሰለኝም፤ የይቅርታና የይፈቱ ወሬውም ከሰብአዊ አዘኔታ ባሻገር የይቅርታውን መሠረቶች እና ፋይዳዎች ገና አንስቶ አልጨረሰም። በዚህ ዙሪያ ሊነሱ ከሚችሉት ጥያቄዎች ጥቂቱን አንስቼ የራሴን አስተያየት ላክል።

 1. አራቱ/አምስቱ ወገኖች (ይቅርታ ጠያቂዎቹ፤ ይቅርታ ሰጪዎቹ- ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው፣ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ይቅር አባባዮቹ) በተቀራራቢ የግንዛቤ፣ የሞራል ልእልና እና ቁርጠኝነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
 2. አምስቱ ወገኖች ይቅርታውን ከሚፈልጉባቸው የተለያዩ ምክንያቶች መካከል መሠረታዊ የሚሏቸውን ይጋሯቸዋል?
 3. ይቅርታው በውጤቱ እነዚህን ወገኖች የሚያስተሳስር ፋይዳ አለውን?

በግሌ ይቅርታ ጠያቂዎቹ ከሌሎቹ ወገኖች በተሻለ በዘመናቸው ስለሆነው ነገር በእርጋታ ለማሰብ የሚያስችል አጋጣሚ እንደተፈጠረላቸው ይሰማኛል። የእስር ቅጣቱ ካስከተለባቸው ጉዳት በላይም ያለፈውን በመገምገም እና አሁን ያለፉበትን በማሰላሰል የሚገጥማቸው ስነልቦናዊ ጉዞ የበለጠ ይፈትናቸዋል። ስለእያንዳንዱ ሰው በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም (ባይገባም) ብዙዎቹ ከልባቸው ሊጸጸቱ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። ስለዚህም ይቅርታውን የሚጠይቁት ከእስር ለመፈታት ብቻ እንደማይሆን እገምታለሁ። ይህም ለይቅርታ እና ለእርቅ በተሻለ ደረጃ የተገቡ ያደርጋቸዋል የሚል ተስፋ አለኝ።

ከብዙ ይቅርታ ጋራ ሌሎቹ ወገኖች ሙሉ በሙሉ ለይቅርታ ውል ወደሚያበቃ የመንፈስ እርጋታና ልእልና የደረሱ አይመስለኝም፤ ይህ አስተያየት ግን “የኢትዮጵያ ሕዝብ”ን አይመለከትም። ይቅርታው ይወርድበታል እስከሚባልበት ጊዜ ባለው ጊዜ እዚያ ይደርሳሉ ካልተባለ በቀር ከሌሎቹ ወገኖች (ተበዳዮችና ቤተሰቦቻቸው፣ መንግሥት እና አሸማጋዮቹ/ይቅር አባባዮቹ) የሚበዙት ስለእርቁ የሚገባውን መንፈሳዊ ዝግጅት ስለማድረጋቸው እጠራጠራለሁ።

ከተበዳዮችና ከቤተሰቦቻቸው ወገን በብዛት የሚሰማው ድምጽ ቁጣና ቂም ጨርሶ ያልለቀቀው ነው፤ “ይቅር ብንልም አንረሳላችሁም” የሚል ቅድመ ሁኔታ መሰል ማሳሰቢያ የሚቀመጥለት ነው (ይረሳ ወይም ሊረሳ ይችላል ያለ ወገን ያለ ይመስላል)። በሌላ በኩል ደግሞ “የሃይማኖት መሪዎቹ እንዴት እኛን በግል መጥተው አላናገሩንም” የሚሉ “የክብራችን ተነካ” ቅሬታዎች በሚዲያ ይቀርባሉ። አልፈውም “ባለሥልጣናቱ ላደረሱት ጭፍጨፋ ተገቢው የቅጣት ውሳኔ ስለተላለፈባቸው ይህንን ውሳኔ ለማስቀልበስ መሯሯጥ አያስፍልግም ሲሉም ይከራከራሉ።” ይህን መሰል አቤቱታዎች ጥያቄውን የአገርና የሕዝብ ከመሆን ፈጽሞ ነጥለው የጥቂቶች ያደርገዋል። እነዚህ ድምጾች ምን ያህሉን ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸውን እንደሚወክሉ በእርግጠኝነት መናገር አይቻል ይሆናል፤ መገመት ግን ይቻላል። እነዚህ ሰዎች “ለእርቅ የበቁ እና የተገቡ ናቸው” ለማለት አልችልም፤ እውነተኛ ይቅርታ ለመስጠትም እንደዚያው። እርግጥ በተቃራኒው ለይቅርታ የበቁና የተገቡ እንደሚኖሩ ተስፋዬ ነው። ይህን አስተያየት ስሰጥ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” የሚል “የአያገባህም፤ አይገባህም” አስተያየት ሊሰጥ እንደሚችል እገምታለሁ። በግልም ይሁን በቤተሰብ በደርግ ስለደረሰብን በደል እንደ አዲስ ለመናገር ጊዜው ስላልመሰለኝ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ ለመስጠትም ተጎጂነት የግድ ሊሆን ስለማይገባው ከዝርዝሩ መቆጠብን መርጫለሁ።

መንግሥትን በተመለከተ ብዙ ማለት የሚገባ አይደለም። በቃልም በድርጊትም መንግሥታችን ስለ ይቅርታ ያለውን እምነትና ግንዛቤ አይተናል።

ቀሪው አካል የይቅርታ አዋላጆቹ ናቸው፤ የሃይማኖት መሪዎቹ። በቅድሚያ ምንም ቢሆን ይህንንም መሞከራቸውን አልነቅፍም፤ እንዲሳካላቸው እመኛለሁ። ከዚያ ውጭ ግን እነርሱም ቢሆኑ ያለባቸው ሸክም ከባድ ነው። የይቅርታና የእርቅ ምክንያት ለመሆን እውነተኛና ፈታሒ መሆን ያስፈልጋል፤ ይህ ቢያስቸግር እንኳን ተደርጎ መቆጠርን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ በተግባር እንጂ ልብስ በማሳመርና መጽሐፍ በመጥቀስ የሚገኝ ጸጋ አይደለም። ከዚህ አንጻር ቤተ ሃይማኖቶቹም ሆኑ መሪዎቻቸው ስለፍትሕ በእውነትና ያለአድልዎ ሲናገሩ ተሰምተው አያውቁም፤ በአገሩ የሌሉ እስኪመስል ድረስ የንጹሐን መከራና ሞት በተመለከተ “እንጸልይ” የማለት ፍቅርና ሐላፊነት እንደሚሰማቸው አሳይተውን አያውቁም። ተባባሪ መሆኑም በቀረላቸው በጸደቁ ነበር። ስለዚህ ከመንፈስና ከሞራል ልእልና አኳያ ካያነው፣ በእኛ በተራዎቹ ዜጎች ዐይን እነርሱም ይቅርታና እርቅን ለማዋለድ ገና የበቁ ሆነው አይታዩም። እንደዚህም ሆኖ ግን ይህ ሙከራቸው በራሱ ወደምንናፍቀው ደረጃ የሚሸጋገሩበት አጋጣሚ እንዲሆንላቸው በመመኘት “ይቅናችሁ” እንላቸዋለን።

ይቅርታው ለምን ተፈለገ?

የደርግ ባለሥልጣናት ይቅርታውን የጠየቁት ከእስር ለመፈታት ብቻ ከሆነ ከአካላዊ እስር እንጂ ከመንፈስ እስራት አይፈቱም። የእኛን አገር አላቅም እንጂ በሌሎች ቦታዎች ይቅርታ የሚሰጡም ሆነ የሚቀበሉ ሰዎች ስነልቦናዊ እገዛ/ምክር የሚያገኙበት እድል ይሰጣቸዋል። በዚህ በኩል የተደረገ ነገር ስለመኖሩ አልሰማሁም፤ ነገር ግን ቢኖር ለሁለቱም ወገን ጠቃሚ ነው። መንግሥትም ቢሆን ይህን መሰል እርምጃዎች ፖለቲካዊ ጥቅም እንዳላቸው ሳይዘነጋ (ፖለቲካዊ ጥቅም ማግኘቱ ነውር የለውም) ከዚያም ሰፋ አድርጎ ቢመለከት አገራዊ ጥቅም እንደሚኖረው አያጠራጥርም። ይህ እውነታ ለአሁኑ መንግሥት ይሠራል ወይ ብሎ መጠየቅ ሌላ ጉዳይ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ታሳሪዎቹ ሊፈቱ የሚችሉበት የሕግ ሥርዓት በራሱ ሊታይ የሚገባው ቁም ነገር ነው። የሕግ ባለሞያዎቻችን አንዱ በአመክሮ ሊፈቱ ይችላሉ ይላል፤ ሌላው ደሞ በእነርሱ ክስ ጥፋጠኛ የተባለ ይቅርታም አመክሮም የለውም ይላል። ከሕጉና ከፍልስፍናው በተጨማሪ በግለሰብም ይሁን በማኅበረሰብ ደረጃ ስለ ወንጀልና ወንጀለኞች ያለን አመለካከት፣ ስለ ይቅርታ በተግባር ያለን እምነት ሁሉ “የይቅርታ” ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የውይይቱ አካል የሚሆኑ ናቸው።

የቀድሞዎቹ ባለሥልጣናት ይቅርታ መደረጉ የሚኖረውን ፋይዳ ለመመዘን የሚያስቸግር መስሎ ይታያል። በግሌ አጋጣሚው ስለ ታሪኩ እንድንነጋገር ከማድረግ አልፎ፤ በቀጥታ ከተጎጂዎችና በበዳዮች መካከል ያለውን ግንኙነት (ቢያንስ በመንፈስ) ከማከሙ በቀር የተለየ አገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ይህ ድርጊት ከተፈጸመ 30 ዓመታት እየተቆጠሩ ነው። አዲሱ ትውልድ ከዝና በቀር የሆነውን አያውቀውም። ይቅርታው ዛሬ ባለው የአገሩቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የሚያስከትለው ተጨባጭ ውጤት አይኖርም።

በአሁኑ ሁኔታ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ መፍጠር ይችል የነበረው የቅንጅት አመራሮች በድጋሚም ብርቱካን የተፈቱበት “የይቅርታ” እና “የእርቅ” ሁኔታ እውነተኛ ቢሆን ነበር። ከዚያም በፊት በነበሩት አጋጣሚዎች በ1980ዎቹ የፖለቲካ ቀውስ የተፈጠሩትን “ቁስሎች” እና መሰሎቻቸውን ማከም በተገባ ነበር። አሁንም መተማመንን ለማምጣት እና መጥፎ ስሜቶችን ሊያስቀር የሚችል አገራዊ እርቅ ያስፈልጋል፤ አልረፈደም። ይህ ማለት ይቅርታ ጠያቂያና ተቀባይ በስም ተለይተው፣ በአድራሻ ተጠርተው የሚጠያየቁበት ግለሰባዊ መልክ ያለው ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በእርቅና በፍቅር መንፈስ ሊታከሙ የሚገባቸው ስሜቶች አሉ። የቤት ሥራው የሁሉም ወገን ነው፤ የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ። በተረፈ አሁን ባለንበት ሁኔታ የደርግ ባለሥልጣናት ይቅርታ በቀጥታ በግለሰቦች፣ ግፋ ቢል ደግሞ “ከታሪክ ጋራ” የሚደረግ እርቅና ትምህርታዊ ትውስታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ካለው ለመረዳት ዝግጁ ነኝ።

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

6 Responses to “ይቅር ባይ፣ ይቅር ተባይ፣ ይቅር አባባይ አሉ? ይቅርታና እርቅስ?”

 1. Mesfine,
  As usual another superb analysis.

 2. Good analysis!If this regime wishes to change its image let it reconcile with the nation! Let the nation forgive this regime first – there are many Innocent people who are languishing in different dreadful prisons in Ethiopia because of their political view. Let them set free these innocent people. Let those people who are sought as criminals/ or sentenced in absencia, those who are wondering out of the country because of their political stand should set free first. Otherwise it is all hypocrisy as usual.

 3. I am a bit surprised that this matter has attracted our attention and even a blog is committed to the topic. It has been 20 years since these people were arrested. Their continued imprisonment or release from prison have no signficance to Ethiopian politics or to the life of the Ethiopian people, except the families of the prisoners and their victim’s families. However, there are thousands of political prisoners who are languishing in jail with no convicted crime and on trumped up charges. Pardon and forgiveness have relevance and be given public attention only when they are directed to these prisoners. I couldn’t tell what the government is trying to achieve by making such a dust-up. Perhaps it is trying to give some dose of amusement to its beloved ‘subjects’.

 4. When you are a victim of such an act things are beyond such a rosy analysis. It is easier than done. I have lost my father, mother and two uncles because of the savagery acts of Meleaku Tefera and co. in Gonder for simple reason that they were protestant Christians. I was raised with no dad or mom near me. This trauma has left life long misery in my persona. For some of you its an academic exercise..or Ghandi, Martin Luther King bla bla rhetoric. I wish I didn’t lost my parents and had the luxury to comment like you do .. For me that is something that defined my life and my world outlook…Justice must be delivered and weyane has no right to release these savages

 5. thanks to mesfine, you shows the meaning of “YEKRTA” in our culture!!

 6. Dear Mesfineeee,
  What a nice piece is it?
  The meaning and value of pardon may get its inherent value in Ethiopian context, when the people are ready for it. I hope reader will not misunderstand me deliberately or otherwise. I think Ethiopians are far from able to think about it let alone giving it. What is going currently in the name of pardoning is just gesture/exercise with out the substance required for pardoning. If it does anything, it only abuses the philosophy and value attached to pardoning.

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.