ramatohara cover 1

የአገር ወይስ የሥነ ጽሑፍ ፍቅር?

ሚዩዚክ ሜይዴይ ተብሎ በሚታወቀው እና በየአሥራ አምስቱ ቀን እሁድ በብሔራዊ ሚዩዚየም አዳራሽ ውስጥ የመጽሐፍት ግምገማ በሚደረግበት ጉባዔ ላይ “ዴርቶጋዳ” ለግምገማ እንደሚቀርብ የሰሙ ብዙ ሰዎች ከውይይቱ ሰዓት ቀደም ብለው አዳራሹን ሞልተውታል። አዳራሹም ከዚህ በፊት በዚህ ጉባዔ ላይ አስተናግዶት ከሚያውቀው ቁጥር እጅግ የበለጠ ተሳታፊ አስተናግዶ ነበር። የአዳራሹ መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ በመያዛቸው ምክንያት እጅግ ብዙዎች ቆመው ከመድረክ ምን ይመጣ ይኾን በሚል ጉጉት ይጠባበቃሉ። ውይይቱ ሳይጀመር አንስቶ በአዳራሹ የሁለት ወገን ሐሳብ ውጥረት እንዳለ ይታይ ነበር። የስብሰባውም ውጤት እንደውጥረቱ ሁሉ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሔደ እሰጥ አገባ ኾነ።

የውይይቱን መነሻ ግምገማ እንዲያቀርቡ የተጋበዙት የመቀሌ ዩኒቨርስቲው አቶ አራጌ ይመር በጉባዔው ላይ ተከስቶ የነበረውን እሰጥ አገባ ሲያስታውሱ “ፈጽሞ የመጽሐፍ ግምገማ አይመስልም ነበር” ይሉታል። አቶ አራጌ ለአዲስ ነገር እንደገለጹት የመጽሐፉ ወዳጆች ደራሲው “ለምን ይነካብናል?” በሚል ማንኛውንም ሐሳብ ለመቃወም ቆርጠው የገቡ ሲኾን፤ ተቃራኒውም ወገን “መጽሐፉ አይረባም” የሚለውን አቋም አጠንክሮ አንጸባርቋል። በመኾኑም እንደ አቶ አንዳርጌ አባባል “የመጽሐፉ ግምገማ ሳይደረግ ቀርቶ ግልጽ ስድድብ ሲሰማ አምሽቷል”። አቶ አንዳርጌ የመጽሐፉን አፍቃሪዎች የሥነጽሑፍ ሐሳብ ይዘው ሳይኾን የመጡት “ስለ አገር የተጻፈ ብቸኛ መጽሐፍ ነው” ከሚል ጭፍን ድምዳሜ በመነሳት እርሱን መቃወም ስህተት እንደኾነ ሲያንጸባርቁ እንደነበረ ይናገራሉ።

የአገር ወይስ የሥነ ጽሑፍ ፍቅር?

ይስማእከ ለመጀመሪያ ጊዜ የጻፈው “ዴርቶጋዳ” የተባለው መጽሐፉ አልሸጥ ብሎ አስቸግሯቸው እንደነበረ የመጽሐፉ አሳታሚ አቶ ዐይናለም መዋእ ይናገራሉ። “ለአራት ወራት ያህል አልሸጥ ብሎን በመጀመሪያው ዙር ካሳተምነው 3000 ኮፒ ውስጥ 950ውን ያህል ብቻ ነበር ለመሸጥ የቻልነው” ይላሉ አቶ ዐይናለም። በመኾኑም አቶ ዐይናለም በመጽሐፉ ላይ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረውን አንድ ማሻሻያ እንዲያደርግ ለይስማእከ ሐሳብ አቀረቡ። ብዙም ሰው ስላላነበበው በወቅቱ ይቀርብ የነበረው አስተያየት በሽፋኑ ዲዛይን ላይ ነበር። “አጎጠጎጤ ያላቸው ወንድ መነኩሴ ሽጉጥ ሲተኩሱ የሚያሳየውን ስእል ብዙዎች አልወደዱለትም፤ ያስፈራል ሃይማኖታዊም ትርጉም ይሰጣል። ስለዚህም ይህን እንዲቀይረው ነገርኩት” ይላሉ አቶ ዐይናለም። ለአንዳንዶች ግን ይህ የሽፋኑ ለውጥ በወቅቱ ገበያውን ይዘውት የነበሩትን የትርጉም ሥራዎች ለማስመሰል የተደረገ ሙከራ ነው።

ከሽፋኑ ለውጥ በኋላ የመጽሐፉ ሽያጭ የተለየ ኾነ። ለይስማእከ ለራሱ ይኾናል ብሎ ባልገመተው ኹኔታ እጅግ ከሚሸጡ መጽሐፍት መካከል አንዱ ለመኾን በቃ። ዛሬ ይስማእከ የዚህኑ “ዴርቶጋዳ” የተሰኘ መጽሐፉን ሁለተኛ ክፍል “ራማቶሐራ”ን አሳትሟል። አቶ ዐይናለምም ሽያጩ ያስደሰታቸው ይመስላል ለዚህ ጽሑፍ ባናገርኳቸው ወቅት “ዴርቶጋዳ እስካሁን 130 000 ራማቶሓራ ደግሞ 50 000 ያህል ኮፒ” መሸጡን ይናገራሉ። አንዳንዶቹንም የልጁ “ችሎታ” ከሚሉት በላይ እንደኾነባቸው በፌስቡክም ኾነ በሌሎች መንገዶች ከሚገልጿቸው አድናቆቶች ይስተዋላል። በተቺዎቹ ዘንድ ግን አንድ ጥያቄ መጠየቁ አልቀረም “ሰዉን ምን ነካው፤ ሥነ ጽሑፍ ጠፋበትን?”

ይስማእከ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ የሚጠቅሳቸው እና “የሥነ ጽሑፍ ስብራቱን” በ “ወጌሻ ምክራቸው” እንደጠገኑለት የሚያወድሳቸው “መካሪዎቹ” ያላዩዋቸው የሚመስሉ እጅግ ብዙ፣ ብዙ “ስብራቶች” በመጽሐፉ ውስጥ በጉልህ ይስተዋላሉ። የይስማእከ በእድሜ ወጣት ከመኾኑ የተነሳ እንደ ባለቅኔው ጸጋዬ ገብረመድኅን አባባል “በሳርም፣ ባሳርም” ተምሮ ያልጨረሳቸው ብዙ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። (በድፍረት የሠራቸው ብዙ ስህተቶች እንዳሉ ባይዘነጋም) በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ስማቸውን ያነሳቸው የሥነ ጽሑፍ ባለሞያዎች ግን እነኚህን የሚጎረብጡ ስህተቶች እንዴት ሊያልፏቸው እንደቻሉ ለብዙዎች ያስገርማቸዋል። በእርግጥ ይስማእከ እነዚህ ሰዎች በመጽሐፉ ላይ የነበራቸው አስተዋጽዖ እስከምን ድረስ እንደነበረ አይነግረንም። በመኾኑም እነዚህን ሰዎች እርሱ ስማቸውን ስለጠቀሰ ብቻ የስህተቱ አጋር አድርጎ ማሰብም  አስቸጋሪ ሊኾን ይችላል። ይስማእከም የእነርሱን አስተያየት “ሙሉ በሙሉ” እንዳልተቀበለ በስልክ ውይይታችን ላይ ገልጿል። ምክንያትም አለው፤ “የራሴ የኾኑ ቀለሞች ከመጽሐፉ እንዲጠፉ አልፈለግሁም” የሚል።

መጽሐፉ የሚያጠነጥንበት ዋነኛ ሐሳብ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች ከየሚሠሩበት የተለያ ተቋም የምጽአት ቀን መነጠቅን በመሰለ መሰወር በመጥፋት በድብቅ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያሳይ ነው። የጉዳዩ አነሳሽ እና ጠንሳሽ ተደርገው የሚወሰዱት ሟቹ የጠፈር ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉ ይመስላሉ። ምንም እንኳን ስማቸው ከቅጣው ትርጉም ወደሌለው “ሻጊዝ” ወደሚለው ስም የተቀየረ ቢኾንም የአባታቸውን ስም ጨምሮ ስለእኚሁ ገጸባሕርይ የተሰጡት መግለጫዎች ሁሉ ቅጣው ስለመኾናቸው ጥርጣሬ እንዳይገባ ያደርጋል። በእኚሁ ሻጊዝ እጅጉ በሚባሉ ሳይንቲስት ውትወታ ምክንያት ከየሚሰሩባቸው ገናና መሥሪያ ቤቶች በመልቀቅ ወደአገራቸው ወደኢትዮጵያ በመምጣት ጣና ሐይቅ ባሉት ደሴቶች ስር ወደተገነባው “ከተማ” የገቡት ምሁራን አገራቸውን ለማሳደግ ማድረግ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ “ሁሉም ተሟልቶላቸዋል”። መሥራት እንዳለባቸው የተነገራቸው አንድ ነገር የፈጣን ባቡር ሀዲድ ሲኾን ከዚህ በተጨማሪ ፍንጫቸው የሚታዩ ነገሮች በደፈናው “ጥናት እና ምርምር፣ ሥልጠና እና ሕክምና” ነክ የኾኑ ነገሮች እንደተጨማሪ ነገር ይታያሉ።

ለሥራው የሚያስፈልገው ገንዘብም ሩቅ አይደለም በዚያው በጣና ሀይቅ ውስጥ ጣሊያን አስጥሞት የሔደውን የወርቅ ክምችት ማውጣት ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው። ይህም ሀብት የተቀበረበት ትክክለኛ ቦታ በኢንጂነር ሻጊዝ እጅጉ እና በዶክተር ሚራዥ ጀርባ ላይ ተነቅሶ ይገኛል። በልጅነቱ ተጥሎ ተገኝቶ በገዳም ውስጥ ያደገው ዶክተር ሚራዥ ሌላም አንድ ሚስጥር ይዞ ነበር መስቀል መሰሉን የወርቁን ክምችት መክፈቻ ቁልፍ። ይህ ሁሉ ኾኖ ሳለ በሲ አይ ኤ እና በሞሳድ ጥብቅ ክትትል ይደረግበት የነበረውን ኢንጂነር ሻጊዝን ለማምጣት በተደረገው ሙከራ በስህተት በፕላስቲክ ሰርጀሪ እሱን መስሎ የተሰራውን ሌላ ሰው ይዘው መጡ። በዚህም ሰው ጭንቅላት ውስጥ በሞሳድ የተቀበረው ፈንጂ በመፈንዳቱ ምክንያት የደሴቱ ስር “ከተማ” ዴርቶጋዳ ፍርስርሱ ወጣ።

ቁጥር ሁለት ዴርቶጋዳን ለማሳየት ቃል በመግባት የሚጠናቀቀው ዴርቶጋዳ፤ ቁጥር ሁለት ዴርቶጋዳን በጎንደር ከተማ ሌላ ተራራ ሥር በሁለተኛው መጽሐፉ ራማቶሓራ ውስጥ ማሳየት ይጀምራል። ሌላ ተጨማሪ በድርጊት የተሞላ ትረካን የያዘው ራማቶሓራ ኢንጂነር ሻጊዝን ለማምጣት የሕክምና ባለሞያዎችን በመላክ የሞሳድ እና የሲአይኤ ሰራተኛ በኾነች ኢትዮጵያዊት ሴት ሰላይ (ሜሮዳ) ረዳትነት ኢንጂነሩን ለማምጣት የተደረገውን ዘመቻ ያሳያል።

መጽሐፉ በባህርይው ምስጢራዊ (mystery) ይሁን ልብ አንጠልጣይ (thriller) አይለይም። እንደ ምስጢራዊ ልቦለዶች ሁሉ የተደበቀን ነገር ለማግኘት የሚስጥር ጽሑፍ (የጸጋዬ ገብረመድኅንን ሰቆቃወ ጴጥሮስ የተሰኘ ግጥም) መፍታት የሚታይበት ነው። ይህም በብዙ መልኩ ሲታይ ምክንያቱ የማይገባ ምስጢራዊነት ነው። ምክንያቱም ጉዳዩ ምስጢር ኾኖበት ሊፈታ የሚታገለው አንዱ ገጸ ባሕርይ (ዶክተር ሚራዥ)ብቻ ነው። ይህም ገጸ ባሕርይ በዋሻው ውስጥ ያለው ተፈላጊነት ሚስጥራዊውን ጽሑፍ መፍታት አቅቶት ወይም በተሳሳተ መንገድ ተረድቶት ጉዞውን ሳያሳካ ቢቀር በምን ሊተካ እንደሚችል አይታወቅም። ምክንያቱም የዋነኛውን ድብቅ ክፍል ቁልፍ የያዘው እርሱ ነው ተብሎ ይገመት ስለነበረ ነው።

እንደ ልብ አንጠልጣይ ልብወለድ (thriller) ሁሉ የእነዚህን አገራቸውን ለማሳደግ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ሙከራ ሊያደናቅፉ የሚሞክሩ የተደራጁ የስለላ ቡድኖች የሚያደርጉትን መሰናክል ለማሳየት ይሞክራል። ሲአይኤ፣ ሞሳድ፣ ግብጻውያን ሰላዮች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላዮች፣ አንዳንድ ጊዜም ከመሬት ተነስተው ተቃዋሚ (protagonist) የኾኑ ግለሰቦች ተጠቅሰዋል። ያም ኾኖ እነኚህ እኩያን ድርጅቶች እና ግለሰቦች መሰናክል የስማቸውን ያህል ያልጠነከረ እና ታሪኩን ልብ አንጠልጣይ እንዲኾን ያላደረገ ቀላል መሰናክል ኾኖ ይታያል። እነዚህም እኩያን ያን ያህል መስዋዕትነት ለመክፈል የሚያነሳሳቸው ምክንያትም አልተገለጸም።

ከዚህ ሁሉ በላይ በሁለተኛው መጽሐፉ ውስጥ ደራሲው በቀጥታ ድርጊቱን የሚያመለክቱ ትረካዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ታሪክን፣ የትምህርት ቤት ጉዳዮችን እና የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመተረክ እንዲሁም የአዝማሪ ቤት ግጥሞችን እና ቅኔዎችን በመተንተን የሚወስደው ጊዜ መጽሐፉን ቀድሞ ከተነሳበት የሥነ ጽሑፍ ዘውግ አውጥቶ የሰከነ ትረካ እንዲመስል በማድረግ መጽሐፉን አርዝሞታል። የመጽሐፉም አብዛኛው ክፍል የብርሃኑ ድንቄን “አልቦ ዘመድ” እንዲመስል ተገዷል። ይባስ ብሎም አቶ ብርሃኑ ድንቄ “አልቦ ዘመድ” ውስጥ በተለየ ትኩረት የሚያብራሩት የሊቁ የክፍለዮሐንስ “ዓለም እስከጊዜሃ” የሚለው ቅኔም በሌላ መንገድ በራማቶሓራ ውስጥ ተተርጉሟል።

በራማቶሓራ እና በዴርቶጋዳ ውስጥ የሚታየው አንድ ጥሩ ነገር ታሪኩን ትእይንቱን ከሚመለከቱ የአገሪቱ ሁኔታ ጋር ለማዛመድ ያደረገው ጥረት ነው። ብዙዎቹ የታሪኩ ክስተቶችም ደራሲው ያደረገውን ጥናት የሚያሳዩ ናቸው። ነገር ግን ደራሲው ጥናት ቢያደርግባቸው ኖሮ ሊያስወግዳቸው የሚችሉም እጅግ ብዙ ስህተቶችን ሰርቷል። ሊወስዷቸው ከመጡ እስራኤላውያን ጋር በእብራይስጥ የሚግባቡት ሽማግሌ ፈላሻዎች(ይስማእከ ምናልባት እነኚህ ሽማግሌዎች ወደኢትዮጵያ የፈለሰው ቤተ እሥራኤል የመጀመሪያ ትውልድ አድርጎ አስቧቸው ይመስላል) እንዲሁም የእስራኤላውያኑ ቋንቋ እብራይስጥ “ግማሹ” የተገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ “ተቆፍሮ” እንደኾነ ይነግረናል። (ቋንቋ ተቆፍሮ ይወጣል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ወደጎን ብንለው እንኳን ይህን የሚመስል ታሪክ አለመኖሩ ብቻ በቂ ችግር ኾኖ ራስምታት መፍጠሩ አይቀርም።)

በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት የግለሰብ ስሞች በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የማይመስሉ አንዳንዴም ቅጽል ስም የሚመስሉ ናቸው። ዣንጊዳ፣ ሚራዥ፣ ሜሮዳ፣ ሻጊዝ፣ ዲዲሞስ፣ ፊንሐስ፣ ሲጳራ እና አናንያ ኢትዮጵያውያን ገጸባህርያት ናቸው። ነገር ግን አንዱም ለኢትዮጵያዊ አንባቢ ትርጉም ያላቸው አይደሉም። ሲጳራ እና አናንያ የሚሉት ስሞች በአንድ ላይ መቀመጣቸው መጽሐፍ ቅዱስን ላነበቡ ሰዎች የሚፈጥረውን ሌላ ትርጉም እንተወው እና ሌሎቹ ስሞች ያላቸው ትርጉም አልባነት ሕጻናት ለሚያዩዋቸው ነገሮች በዘፈቀደ የሚያወጧቸውን ስሞች መምሰላቸው ምክንያት ያለው አይመስልም። ከዚህም ሁሉ በላይ በሁለተኛው መጽሐፍ ውስጥ እንደ መጠሪያ ስም የሚያገለግለው “አርባጫ” የሚለው ቃል በአንደኛው መጽሐፉ ውስጥ ሌላ ነገር ኾኖ ቀርቦ ይታያል። ስደተኞች ረሃብ ሲጠናባቸው የሚበሉትን አፈር ደራሲው “አርባጫ አፈር” እያለ ይጠራዋል። ይህም ደራሲው የቃሉን ትርጉም ባያውቀውም እንኳን በድፍረት ለመጠቀም ያለውን ነጻነት የሚያሳይ ነው።

ደራሲው ለገጸባሕርያቱ ስም ብቻ ሳይኾን ቅጽል ስምም ይሰጣቸዋል። ነገር ግን ስም በሚሰጥበት ጊዜ ይታይበት የነበረው ችግር በቅጽል ስሞቹ ላይም መንጸባረቁ አልቀረም። “ባለክንፉ በራሪ”፣ “አሞራው የራዳር ሳይንቲስት”፣ “አጥማጇ አቦ ሸማኔ” የመሳሰሉት ቅጽል ስሞች አንዳንዴ ቅጽል ስሙ እና ስለ ገጸባሕርይው ለመግለጽ የተፈለገውን ነገር አይገልጹም፤ አንዳንዴም ትርጉም አልባ ናቸው።

ደራሲው የሚጠቀምባቸውም አገላለጾች የመጽሐፉን ሌላ ገጽ ለመግለጥ ትእግስትን የሚፈታተኑ ናቸው። ቋጥኝ የሚያክል ራስ፣ በአውራጣታቸው ቆመዋል (ከእንግሊዘኛው አባባል በቀጥታ የተተረጎመ ይመስላል)፣ “ያቃጥሩብናል”፣ “የታሪኳን ደም ስትጠባ”፣ “የግምባር ሸንተረር” (መስመር ለማለት ይመስላል)፣ “በጥቁር ልብስ ከታጀለው ደረቷ”፣ “ደቦል ድንጋይ”፣ “ጥልቅ አረንጓዴ ኮብራ መኪና” የመሳሰሉት አገላለጾች የደራሲውን የአማርኛ ቋንቋ እውቀት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው። ከእነዚህ ሁሉም በላይ ደራሲው የሩካቤ ስጋን ትእይንቶች ለመግለጽ የሚተቀምባቸው አባባሎች የሚያስገርሙ ናቸው። አንዱን እንደምሳሌ ብንወስድ፤ “ቀጭን ወገቧ ታጥፎ ሽንጡ ውስጥ ገብቷል” ይላል ደራሲው። እንደምን ያለ ትእይንት ይኾን? ደራሲው በመጀመሪያው መጽሐፉ የምእራፍ ሁለት መግቢያው ያደረገውንም አረፍተ ነገር ለምን እንደተጠቀመበት ማወቅ ያስቸግራል። “በውድ ዋጋ ነው የተገረዝሽው?” በሚለው ጥያቄ የሚጀመረው ምእራፍ ስለ ግርዛቷም ይሁን ከእሱ ጋር ዝምድና ስላላቸው ጉዳዮች ሳያነሳ ይጠናቀቃል። እነዚህ እና ብዙ ስህተቶቹ መጽሐፉን አሰልቺ አድርገውታል።

በአጠቃለይ መጽሐፉ በልጅነት ህልሞች የተሞላ፣ ደህና ሊባል የሚችል የታሪክ ሤራ ያለው ነገር ግን በደካማ የቋንቋ አጠቃቀም እና የጠቅላላ እውቀት  ግንዛቤ ማነስ ምክንያት ለመነበብ አስቸጋሪ የኾነ ድርሰት ነው። ይህም ሁሉ ኾኖ ብዙ አንባቢ አግኝቷል። ለምን የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም። ለአንዳንዶች “ሕዝቡ ድርሰት ርቦት ይኾን ሳይመርጥ የሚያነበው?” የሚለው ጥያቄ በቀላሉ የማይታለፍ ነው። ነገር ግን የመቀሌ ዩኒቨርስቲው አቶ አራጌ የሚዩዚክ ሜይዴይ ታዳሚዎችን ባዩበት ኹኔታ ከብዙ አንባቢዎቹ ዘንድ የሚገለጸው ጉዳይ መጽሐፍቱ አገራዊ ጉዳዮች በመንካታቸው የመወደዳቸው ጉዳይ ነው። በዚህም ተባለ በዚያ ለመጽሐፍቱ የተቸራቸው ፍቅር ከሥነ ጽሑፍ ውበት ይልቅ ለአገራዊ ጉዳይ ያደላ ይመስላል።

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email