የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ

የአገር ቤት ጋዜጦች የወረቀት ዋጋ ሲወፍር እነርሱ ይቀጭጫሉ፡፡ ኑሮ ሲንር እነርሱ ይከስማሉ፡፡ ለወራት ያህል ሲንገታገት የቆየው ሳምንታዊው አዲስ ፕሬስ ጋዜጣ በመጀመርያ አካባቢ ተጣጣረ፤ ወደ በኋላ ላይ አንድ ሳምንት እያረፈ በመውጣት አጣጣረ፡፡ በመጨረሻም ብዕሩን ሰቀለ፡፡ አዲስ ፕሬስ ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት በአገር ቤት የጋዜጣ ገበያ ላይ ባለመታየቱ ከጋዜጦች ዓለም እንደተሰናበተ ይገመታል፡፡

ያም ኾኖ አንዳንድ ጋዜጦች በአስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ ኾነው ትርጉም የሚሰጡ ጽሑፎችን  ይዘው በመውጣት በጠባቡ የኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ውስጥ ይታትራሉ፡፡ አውራምባ ታይምስ አንዱ ነው፡፡

ይህ ጋዜጣ በዚህ ሳምንት ከኀይሌ ገብረሥላሴ እና ከቀድሞው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ጋራ ሰፊ ቃለ መጠይቅ አድርጎ አስነብቧል፡፡

አምባሳደር ዴቪድ ሺን ስለ ኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ

በኢትዮጵያ አምባሳደር ከነበርኩበት ወቅት አንስቶ በፕሬስ ነጻነት ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የበለጠ አዎንታዊ ለውጥ ባለመኖሩ አዝኛለሁ፡፡ ኹኔታው እንደ ድሮ ተመሳሳይ እና በአንዳንድ ገጽታዎቹም የኋሊት የተጓዘም ነው የሚመስለው፡፡ ለምሳሌ እኔ እንደምገነዘበው በኦሮምኛ የሚታተም ጋዜጣ ዛሬ በአገሪቱ የለም፡፡ በዘጠናዎቹ መጀመርያ አካባቢ በርካታ የኦሮምኛ ጋዜጦች ነበሩ፡፡ በዚያ ወቅት የነበሩ አንዳንድ ተቃዋሚ ጋዜጦች ሞያዊነትም ኾነ ሐላፊነት የሚሰማቸው አልነበሩም፡፡ ዛሬ ያለው ኹኔታ እንዲያ እንዳይደለ እገምታለሁ፡፡

አምባሳደር ዴቪድ ሺን ስለ አቶ መለስ ዜናዊ

በአስተሳሰብ ብቃት ደረጃ ምጡቅ ናቸው፡፡ በተለይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በስፋት ያነባሉ፡፡ ጥሩ አድማጭም መኾን ይችላሉ፡፡ የራሳቸውን መከራከርያዎች በግልጽ እና ግቡን በሚመታ መልኩ አሰዳድረው ያስቀምጣሉ፡፡ ሲናደዱ ወይም ከአንተ አቋም ጋራ ሳይስማሙ ሲቀሩ ቃላት አይመርጡም፡፡ የሚያምኑበትን ይናገሩታል፣ የሚናገሩትን ያምኑበታል፡፡ ያኔ በ1990ዎቹ መጀመርያ እንኳ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ንግግራቸው አስገራሚ ነበር፤ በጊዜ ሂደትም ተሸሽሏል፡፡ በጫካ ሳሉ የነበራቸው የሽምቅ ዉጊያ ተሞክሯቸው ባሕርይ ቅሪት አሁንም አለ፡፡ በዋዛ የሚበገሩ አይደሉም፡፡ የደኅንነት ጉዳይ ሁሌም ጥብቅ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባትም ይህ ስጋታቸው በመላው ኢትዮጵያ በስፋት እና በተደጋጋሚ እንዳይንቀሳቀሱ ሳያደርጋቸው አልቀረም፡፡ መረጃን በጥብቅ የሚይዙ ሲኾን ለምስጢራዊነትም ዋጋ ይሰጣሉ፣ ይህም በአጠቃላይ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ መገለጫ እንደኾነ ድምዳሜ ነበር፡፡

በአምባሳደርነት ዘመንዎ በትክክል አልሠራሁትም የሚሉት

መጀመርያ አካባቢ አዲስ አበባ በነበረኝ ቆይታዬ የፕሬሱ አንዳንድ ክፍሎች ሐላፊነት የማይሰማቸው መኾናቸውን ባለመገንዘብ መንግሥትን ከሚቃወሙ ፕሬሶች ጋራ ግንኙነት አድርጊያለሁ፡፡ ይህ ጥረት መንግሥትን ሊያስቆጣው እንደሚችል አውቄ ነበር፡፡ አስቆጣውም፡፡ ነገር ግን ከእኔ ጋራ ግንኙነት መፍጠርን ለራሳቸው ዓላማ ጥቅም ላይ ባዋሉት እና ሐላፊነት ሳይሰማቸው መጓዝን በቀጠሉበት የግሉ ፕሬስ አካላት ላይ ያመጣው አዎንታዊ ውጤት አልነበረም፡፡ ኾኖም ይህ ተሞክሮ ጠንካራ፣ ፕሮፌሽናል እና ነጻ የግል ፕሬስ ስለማስፈለጉ የነበረኝን አመለካከት አልለወጠውም፡፡ ኾነም ቀረ ኹኔታውን በተሻለ መንገድ ማራመድ ይገባኝ ነበር፡፡

ኀይሌ ለአውራምባ

ስለ ፖለቲካ

‹‹ወደ ፖለቲካ ከገባሁ በቀጥታ ወደ ተግባር ነው የምገባው፡፡ ፖለቲከኛ ስኾን ምንድን ነው መሥራት ያለብኝ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ ማቋቋም ነው ወይስ ፖለቲካ ሲስተም ውስጥ ገብቼ በፓርላማ ተሳትፎ ማድረግ ነው፤ ወደፊት የማስብበት ነው፡፡››

ስለ ብርቱካን

‹‹ሽማግሌዎቹ ራሷን የምታረጋጋበት ቦታ የት ይኹን፣ ሲሉ ምን ችግር እዚያ ትሂድ እና ለፈለገችው ጊዜ ትቆይ አልን ግን ብዙም አልቆየችም፡፡ ምናልባት ስላልወደደቸው ሊኾን ይችላል /ሳቅ/››

ስለ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ

‹‹ይህ ሰውዬ ለዚህ ሁሉ ስህተት የበቃው አንድ ስልክ ሲደውልልኝ አለማናገሬ ነው፡፡ ሰውየውን በግል አውቀዋለሁ፡፡ ከእኔ ጋራ በተያያዘ ጥሩ ያልኾኑ ጽሑፎችን ይጽፋል፡፡ እኔን ከማነጋገር ውጭ የሚጽፋቸው አሉ፡፡ በነገራችን ላይ ሲደውልልኝ ወደ ሐዋሳ እየሄድኩ ነበር እና ስልኩን አላነሳሁትም፡፡ ከዚያ ማኔጀሬ ጋራ ይደውልና ለምን ስልክ አያነሳልኝም፤ ይለዋል፡፡ እሱም ኀይሌ በጣም ቢዚ ነው፤ እንዴት ስልክ ሊያነሳልህ ይችላል ይለዋል፡፡ በመቀጠልም የፖለቲካ ጫና አለበት ስልኩ ይጠለፋል እንዴ ብሎ ይጠይቀዋል፡፡

ስለመርዳት

ርዳታ እንዳረክ በተደጋጋሚ ስታወራ በተረጂው ላይ የሞራል ስብራት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለዚያም ሲባል የማደርጋቸውን ነገሮች መናገር አልፈልግም፡፡ የምናደርገው ነገር ለእከሌ ለእከሌ ብለን ሳይኾን ለራሳችን የአእምሮ ርካታ መኾን አለበት፡፡

ኀይሌ በራሱ ላይ ስለተቀለዱ ቀልዶች

‹‹ ዶሮዋ መንገዷን ስታቋርጥ ኀይሌ ምን አለ ተባለ- ዶሮዋ ስታቋርጥ ማን ነበረ፡፡ ኬንያውያን ነበሩ አሯሯጭ /ፔስሜከር/ አላት፡፡ ሌላ የሰማሁት ደግሞ ሌባ እኔ ቤት ገባ አሉ፡፡ ኀይሌ አባሮ ሊይዘው ቢሞክር አልያዝ ሲለው- ቆይ አውቄኻለሁ ቀነኒሳ ነህ ብሎ መለሰ የሚለውን ሰምቻለሁ፡፡ ቀልዶችን በጥሩ ጎናቸው ማየት ይኖርብናል፡፡ ኀይሌ የማይደርስበት ሰው ቀነኒሳ ነው ማለታቸው እንጂ ቀነኒሳን ሌባ ለማለት አይደለም፡፡

የአገር ቤት ምርቃት

በነሐሴ ወር ኢትዮጵያ ውስጥ በዴድኩበት ጊዜ የራሴን ብሎግ እንኳን ከፍቼ መመልከት ባለመቻሌ አዝኜ ነበር፡፡ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ለአውራምባ

‹‹ሰው ይሙት አልልም፤ ገበያ የለም ግን እላለሁ›› ተካልኝ ስሜ የሬሳ ሳጥን ሻጭ ለሮዝ መጽሔት

‹‹ዕቅዱ ባይሳካ ሥልጣንዎትን ይለቃሉ ወይ›› የመድረክ ተወካይ ለአቶ መለስ ስለትራንስፎርሜሽኑ

‹‹የቀድሞዎቹ ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ወዴት አሉ?›› ፍትህ ጋዜጣ

‹‹ምርጫን ለማወክ አሲረዋል የተባሉ የመከላከያ አባላት እስከ 18 ዓመት በሚደርስ እሥራት ተቀጡ›› ሰንደቅ ጋዜጣ

‹‹እርሻ እያሰብኩ ነው›› ኀይሌ ለአውራምባ

‹‹ቃር ቃር የሚለው ቃር ቃር ይበለው እንጂ ከቻይና ጋራ ያለን ግንኙነት አይቋረጥም›› አቶ መለስ በፓርላማ

‹‹ወደቦንጋ አቅጣጫ አልወረደም እጂ የባቡር መሥመሩ ጅማ ላይ አይቆምም፡፡›› አቶ መለስ ለዶ/ር አሸብር

ጥያቄ ‹‹ቲያትር ቤት ስትቀጠር ደሞዝህ ስንት ነበር?

መልስ ፡-“ሀምሳ ብር”

ጥያቄ፡- ከ35 በኋላ አሁን ደሞዝህ ስንት ነው?

መልስ፡- አይ ዝም ማለት ነው ምንም ያህል አልተራራቀም፡፡ አርቲስት አልዓዛር ሳሙኤል ለአውራምባ

‹‹ዲያቆን በጋሻው በነጻ ተሰናበተ›› አውራምባ

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

2 Responses to “የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ”

  1. Hey Addis Neger!

    I love this format. summary of the Ethiopian Press. I only get this format from you. It gives me the best of the week.

    Please go on!

    Heny

  2. i’m so sorry about addis press mohamed Ali & nebiyu halile was work on it . o ethiopia

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.