የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?

የተቃዋሚዎች ሰፈር እንዴት ከረመ?

የተቃዋሚዎች ጎራ ሁሌም ተመሳሳይ የመከፋፈል ዜናዎችን የሚያስተናግድ  ሆኗል፡፡ ፍትህ ጋዜጣ ‹‹ተቃዋሚዎች እንዴት ከረሙ›› በሚል ርእስ ያሰፈረው ጽሁፍ ተቃዊሚዎች በዚህ አመት ያሳለፉትን አበይት ዉጣ ውረድ ይዳስሳል፡፡ የመጀመርያ አንቀጽ እንዲህ ይነበባል፡፡

የመኢኣድ አመራሮች እርስ በርስ ተናጩ፡፡ ሻለቃ ጌታቸው ለመኢአድ ሳያሳውቁ ወደ አሜሪካ ሸመጠጡ፡፡ ዶ/ር ታድዮስ ቦጋለ የመኢአድ ሊ/መንበር ነኝ ከማለታቸው ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ከተኙበት የህክምና አልጋ እንደ ቻይና ካራቴ ተገለባብጠው ተነሱ፡፡አንድነትንና ዝም አንልሞችን ለመሸምገል የተደረገው ሙከራ ከሸፈ፡፡ ብርቱካን ከእስር ተፈታች፡፡ ብርቱካን ደቡብ አፍሪካ ሄደች፡፡ ብርቱካን ከደቡብ አፍሪካ ተመለሰች፡፡ብርቱካን እስከአሁን ወደ ፓርቲው አልተመለሰችም፡፡አንድነት ፓርቲ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን አከበረ፡፡ ብቸኛው የመድረክ የፓርላማ ተመራጭ ፓርላማ በመግባቱ ፕ/ር በየነና ዶ/ር መራራ አወገዙት፡፡ አንድነት ከመድረክ ሊወጣ ነው፡፡ መኢአድ፣አንድነትና፣ብርሃን ፓርቲ ሊዋሀዱ ነው፡፡ የአረና አመራር ራሳቸውን አገለሉ፡፡ ስየ መፅሀፍ ጻፉ፡፡ አቶ ልደቱ በአሜሪካ ተቃውሞ ገጠማቸው፡፡አቶ አየለ ጨሚሶ 5ኛው አለምአቀፍ የፌዴራሊዝም ጉባኤ የተሳካ ነበር አሉ፡፡ የአቶ አየለ ምክትል አቶ ለገሰ ቢራቱ ከፓርቲው ተባረሩ፡፡ አቶ አየለ ጨሚሶ ለፓርቲያቸው ስራ ከኪራይ ቤቶች ያገኙትን ቢሮ ለዳቦ ቤት አከራዩት፡፡ ራዕይ ፓርቲ ለሁለት ተከፈለ፡፡የመኢብን ሊቀመንበር በቢሯቸው የሚያካሄዱት የድለላ ስራ ደርቷል፡፡ የኦብኮው አቶ ተስፋየ ቶሎሳ በሽልማት ያገኙት መሬት የገንዘብ ምንዛሬ በመጨመሩ ዋጋው መናሩ እንዳስደሰታቸው ተገለፀ፡፡

ዶ/ር ዳኛቸው ከአውራምባ ታይምስ ጋር

በይቅርታ ጉዳይ ላይ ነው ጋዜጣው ያናገራቸው፡፡ ይቅርታው ለፖለቲካ ፍጆታ ይውላል የሚል ስጋት አለ ሲል የጠየቃቸውን ጋዜጠኛ እንዲህ አሉት፡፡‹‹ መንግስት የሚያደርገው ነገር በሙሉ የራሱን ጥቅም ያገናዘበ ነው፡፡ ግን ይቅርታው የፖለቲካ ፍጆታነት ያውለዋል ተብሎ ሰዎች ይቅርታ አይደረግላቸው? እነ ብርቱካ አይፈቱ? ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ ይታደራል እንዴ?

የሰላማዊ ትግል አዋጪነቱ አጠያያቂ እንደሆነ የተጠየቁት ዶክተሩ በፍፁም እንደማይስማሙ ይናገራሉ፡፡‹‹ከሰላማዊ ትግል ውጪ ምንም አማራጭ የለም›› በሰላማዊ ትግል ለውጥ ካልመጣ በሌላ መንገድ ለውጥ አመጣለሁ››ብሎ የሚያስብ ለውጥ ያመጣል ብየ ስለማላምን ነው፡፡ በፍልስፍና መነሻና መድረሻ የሚባል ነገር አለ፡፡ መነሻ ላይ የምታደርገው እንቅስቃሴ መድረሻህን ይፐውዘዋል፡፡ ከመነሻህ የሰዎችን አንገት በመቁረጥ ስልጣን ይዤ ዴሞክራሲ አመጣለሁ የምትል ከሆነ እኮ ስልጣን ከያዝክ በላም አንገት መቁረጥህን አታቆምም››

በ97 ምርጫ ላይ ታሪካዊ ስህተት ተሰርቷል የሚሉት ዶክተሩ ይህም የመጣው ከጋዜጠኞች፣ከዲያስፖራውና ከራሳቸው ከፖለቲከኞች ነበር ይላሉ፡፡ ያኔ ቅንጅቶች ወደ ፓርላማ መግባት አለባቸው ስል ‹‹ኢህአዴግ ነው›› ነበር የተባልኩት፡፡

የቦሌው ጎዳና…

የእንግሊዝኛው ፎርቹን ጋዜጣ ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ድልድይ ያለው መንገድ ግንባታ በመጪው የካቲት ወር ሊጀመር እንደሚችል ፅፏል፡፡ 4ኪሎ ሜትር ርዝመትና 40 ሜትር ስፋት የሚኖረው ይኽ ጎዳና በ60 ሚሊዮን ዶላር በአዲስ መልክ ይገነባል፡፡ የቻይናው ‹‹ሲአርቢሲ›› የመንገድ ስራ ግንባታውን እንደሚያከናውን ይጠበቃል፡፡

መንገዱ የአገር መሪዎች በመጡ ቁጥር የሚዘጋና ብዙ ተሸከራካሪዎችን የሚያስተናግድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በስራ መግቢያና መውጫ ሰአታት ከፍተኛ መጨናነቅ ይታይበታል፡፡ ግንባታው በ18 ወራት ሲጠናቀቅ ግን የትራፊክ መብራት የሚያቆመው መኪና አይኖርም፡፡ ኦሎምፒያ፣ ወሎ ሰፈርና ርዋንዳ አካባቢ ተላላፊ መንገድ ስለሚገነባ ከመስቀል አደባባይ ቦሌ ጫፍ የሚሄዱ መኪናዎች ለመቆም አይገደዱም፡፡

ፎርቹን ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው  ዎርቤክ ህንፃ ፊትለፊት ከሚገኝ ህንፃ ውጭ አንድም ህንፃ በዚህ መንገድ ምክንያት አይፈርስም፡፡

ጋዜጣው ‹‹አጅንዳ››በሚለው አምዱ ደግሞ ኦሎምፒያ አካባቢ ያሉ ሰፈሮች/ 12 ሄክታር መሬት ይሸፍናሉ/ ለልማት አገልግሎት ሊፈርሱ እንደሚችሉ ፅፏል፡፡ በተለይም ከ‹‹ጌቱ ኮሜርሻል›› ጀርባ ያሉ ሰፈሮች በየካቲት ወር ቁርጣቸውን ያውቃሉ፡፡

መስቀል አደባባይ ሊያምርበት ነው

የእንግሊዝኛው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደፃፈው የአዲስ አበባ መስተዳደር መስቀል አደባባይን በልዩ ሁኔታ ሊያድሰው እቅድ ይዟል፡፡ 50ሚሊዮን ብር በሚሆን ወጪ በአዲስ መልክ የሚያሸበርቀው መስቀል አደባባይ ዲዛይኑን ላሸነፉት ሶስት ግለሰቦች የ80ሺህ፣ የ60ሺህ  እና የ 40ሺህ ብር ሽልማት ሰጥቷቸዋል፡፡ መስቀል አደባባይ ግንባታው 3 አመት ሊፈጅ ይችላል ተብሏል፡፡የቅዳሜው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው የፃፈው፡፡

የሸራተን ሰማእታት

በሸራተን አካባቢ ያሉ ነዋሪዎቸ ቤታቸው ውስጥ ሳሉ በአፍራሽ ግብረሀይል መኖርያቸው እንደፈረሰባቸው የፃፈው ሳምንታዊው ፍትህ ጋዜጣ ነው፡፡  በቀድሞው ወረዳ 14 ቀበሌ 25 ውስጥ ነዋሪ የነበሩ ተነሺዎች ከቤት ሳይወጡ ቤቱ በላያቸው ላይ እንዲፈርስ የተደረገው ምትክ ቤት ሳይሰጠን አንለቅም በማለታቸው ነው፡፡ ጋዜጣው እንደሚለው ነዋሪዎቹ ባልተዘጋጁበትና ባላሰቡት ሁኔታ የቤታቸውን ንብረት ሳያወጡ የቀበሌው አስተዳዳሪና የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት ለማፍረስ የመጡትን ግብረኃይሎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማና የኢህአዴግን የንብ ምልክት ያለበትን ምስል ይዘው ከነልጆቻቸው ቢማፀኑም የቤታቸው ጣርያ ከመፍረስ አልዳነም፡፡ፍትህ ነዋሪዎቹ አሁንም ጣርያ በሌለው ቤት እየኖሩ እንደሆነ ዘግቧል፡፡

ጋዜጣው በተያያዘ ዜና እንደዘገበው ለሸራተን ማስፋፍያ የሚውለውን አካባቢ ለማፍረስ ተደራጅተው  የነበሩ ሁለት ወጣቶች ቤት በማፍረስ ላይ እያሉ የቤቱ ግድግዳ ተንዶባቸው ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

ከውሻ ጋር አንሶላ የተጋፈፉት የ80 አመቱ አዛውንት

‹‹በኮልፌ ቀራኒዬ ክፍለ ከተማ ከውሻ ጋር የግብረስጋ ግንኙነት ያደረጉት የ 80 ዓመት አዛውንት ጥፋተኛ ተባሉ፤ ግለሰቡ ከዚህ ቀደም ከፍየል ጋር ግንኙነት ያደርጉ እንደነበረና ፍየሏም መሞቷን የዓቃቢ ሕግ ምስክሮች ገልፀዋል፡፡›› መሰናዘርያና ሰንደቅ ጋዜጣዎች በጉዳዩ ላይ እንደዘገቡት አዛውንቱ በምርኩዝ ድጋፍ ፍርድ ቤት ቀርበው ድርጊቱን መፈፀማቸውን አምነዋል፡፡‹‹ ተፀፅቻለሁ፣ንሰሀም እገባለሁ›› ሲሉ ለዳኛው ተናግረዋል፡፡

የ‹‹አስካሉካን ፍርድ››

አዲስ አድማስ ጋዜጣ የአስካሉካን የፍርድ ውሳኔ ተበዳዮችን ማስቆጣቱን በፊት ገፁ ዘግቧል፡፡ ለወራት ያህል ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ያገኘው ይህ የፍርድ ሂደት ተከሳሾቹን በ4 አመት ከስድስት ወር እስራት ብቻ እንዲቀጡ በመወሰን መጠናቀቁ ክፉኛ ያሳዘናቸው ተበዳዮች ‹‹ዜጎች በፍትህ የመተማመን ስሜት የሚያጠፋ ውሳኔ‹› ብለውታል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የአለም ዋንጫን አሳያችኃለሁ በሚል 1200 ሰዎችን በማታለል 45 ሚሊየን ብር ይዞ የተሰወረው ተከሳሽ በቅርቡ ጀርመን ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን መንግስት ተጠርጣሪው ተላልፎ እንዲሰጠው የጠየቀ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ለተበዳዮቹ ነግረዋቸዋል፡፡ ሆኖም በአስካሉካን ስራ አስኪያጅ ላይ የተወሰነው ብይን ‹‹ህገወጦችን የሚያበረታታ›› ሲሉ ተችተውታል፡፡ ‹‹ተራ ሞባይል ለሰረቀ እንኳ እንዲህ አይነት ውሳኔ አይሰጥም፤ እንዲህ ከሆነማ ቀጣዩን የለንደን ኦሎምፒክ እናዘጋጃለን›› ሲሉ ተበዳዮቹ ሀዘናቸውን ገልፀዋል ሲል አድማስ ፅፏል፡፡

የአቶ መለስን ሀብት ማወቅ ይፈልጋሉ?

የመንግስት ባለስልጣናት ሀብታቸውን እያሳወቁ ነው፡፡ አቶ መለስ፣ፕሬዝዳንት ግርማ፣ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ እና ሌሎች 26 ከፍተኛ ባለስልጣናት ሀብታቸውን አሳውቀዋል፡፡ ሀብት ማሳወቅያ ቅፁ 62 ገፆች ሲኖሩት በስራ ውጥረት ምክንያት ሰነዱን ያልሞሉ ባለስልጣናት ሰሞኑን ያስረክባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሁሉንም ባለስልጣናት ንብረት ለመመዝገብ 6 ወር ይፈጃል፡፡ ከዚያ በኃላ አንድ ሰው ምክንያት ይኑረውም አይኑረውም የባለስልጣናቱን ሀብት አገላብጦ ማየት ይችላል፡፡ በድረ-ገፅም ይለቀቃል፡፡ አድማስ ጋዜጣ ነው የፀረ ሙስና ባለስልጣኑን ጠቅሶ  የዘገበው፡፡

ስምንት የግል ቴሌቪዥን ቻናሎች በኢትዮጵያ

አውራምባ ጋዜጣ ብሎንበርግን ጠቅሶ እንደዘገበው በቀጣዩ የፈረንጆች አመት ስምንት አዳዲስ ቻናሎች ይከፈታሉ፡፡ በኢትዮጵያ ነው ይህ ይሆናል የተባለው፡፡ አቶ በረከት ስምኦን ናቸው ይህንን ያሉት፡፡

ደርጎችና የእርቁ ጉዳይ

‹‹የአገር ቤት ጋዜጦች ባሳለፍነው ሳምንት በእርቁ ዙርያ በስፋት እየፃፉ ነው፡፡ ጎግል ጋዜጣ ቁልፍ የፖለቲካ ሰዎችን አነጋግሯል፡፡

1.       ‹‹በ97 ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ሆነን እነዚህን የሀይማኖት መሪዎች ይቅርታ እንዲጠይቁ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ከካቶሊክ መሪ በስተቀር የቀሩት የሰጡን መልስ ተመሳሳይ ነው፡፡ መንግስትንና እግዜአብሔርን መቃወም አትችሉም የሚል መንፈስ ነበረው፡፡ የሓይማኖት መሪዎቹ በመንግስት ሳንባ የሚተነፍሱ ይመስላሉ፡፡›› ዶ/ር መረራ ጉዲና

2.     ‹‹ በመርህ ደረጃ በእርቅ አምናለሁ፤ በሞት ፍርድ አላምንም፡፡ ስለዚህ አርቁን እደግፋለሁ፡፡›› ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ

3.     ‹‹በህጉ መሰረት በዘር ማጥፋት የተከሰሰ ሰው ይቅርታ የለውም ይላል፡፡ መንግስት ይሄንን እንዴት ይፈታዋል?›› አቶ ልደቱ አያሌው

4.     ‹‹እርቁን እናደርጋለን የሚሉት በምርጫ 97 ያ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም የት ነበሩ?›› ዘሪሁን ገ/እግዚያብሄር

5.     ‹‹ሌሎችን አግልሎ ረጅም አመት ታስረው በእድሜና በህመም ከተጎሳቆሉት ጋር እርቅ እያሉ መደራደር ፌዝ ነው፡፡ለሬሳ ይቅርታ የሚያደርግና ከሬሳ ጋር የሚደራደር አሳፋሪ ነው፤ የተለመደ የፖለቲካ ቀልድ ነው፤ አጀንዳ ለማስቀየር የታለመ ነው፡፡›› አቶ ወንድሙ ኢብሳ

አቶ ተክለብርሃን አምባዬ

የኤድናሞል ባለቤት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ ባለፈው ሳምንት በኢቲቪ በቀጥታ ስርጭት የተመረቀውን ‹‹አባይ ወይስ ቬጋስ›› ፊልምን በግል  ከተመለከቱ በኃላ በመደሰታቸው ለሁለት ተዋናዮች የገንዘብ ስጦታ አበርክተዋል፡፡ ተዋናይ ሰለሞን ቦጋለና ተዋናይት ብሌን ማሞ እያንዳንዳቸው የእኚህን ባለሀብት ሀያ ሺህ ብር ስጦታ ተቀብለዋል፡፡ ‹‹ጎበዝ ልጆች ናቸው፤መሸለም ይገባቸዋል፡፡ ደራሲውን ቴዎድሮስ ተሾመንም ለመሸለም እያሰብኩ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል-ለአድማስ ጋዜጣ፡፡ ያለው ማማሩ!

የአገር ቤት ምርቃት

‹‹ትላልቅ የመንግስት መ/ቤቶች ፊልሙን ስፖንሰር አድርገዋል፡፡ እነዚህ ደርጅቶች ሌሎችን የኪነጥበብ ስራዎች ሰፖንሰር ሲያደርጉ ብዙም አይታዩም›› ጋዜጠኛ ፅዮን ግርማ ለ‹‹አባይ ወይስ ቬጋስ›› አዘጋጅ ቴዎድሮስ ተሾመ የጠየቀቸው ጥያቄ፡፡

‹‹ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከ70ሺህ ብር በላይ ወጪ አድርጌያለሁ፤ ይህን ገንዘብ ከስረህ ውጣ የምትሉኝ ከሆነ ደብዳቤ ፃፉልኝና ከፓርላማ እወጣለሁ››  በፓርላማ ብቸኛው ተቃዋሚ አቶ ግርማ ሰይፉ ሚስጥራዊ ስብሰባ ላይ ተናገሩት ብሎ ኢትዮቻናል ጋዜጣ የዘገበው፡፡

‹‹ኮልፌ አካባቢ የሴተኛ አዳሪዋን አፍንጫ በጥርሱ  ቆርጦ የጣለው ግለሰብ ለውሳኔ ተቀረጠረ››መሰናዘርያ ጋዜጣ

‹‹ቆሻሻ ፍለጋ የገባው እጄ ትኩስ የህፃን ልጅ አስክሬን ይዞ ወጣ፡፡›› ወ/ሮ ጥሩነሽ /የማዘጋጃ ቤት የፅዳት ሰራተኛ/ ለሰንደቅ ጋዜጣ ከተናገሩት

‹‹ የመሬት መንቀ|ጥቀጡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ 26 ተማሪዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት አደርሷል፡፡›› አዲስ ዘመን ጋዜጣ

‹‹ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሁለተኛውን የእርቅ ልኡካን ወደ አሜሪካ ሊልክ ነው፡፡›› ነጋድራስ ጋዜጣ

‹‹ምንአልባት ውጭ ያደረ ብረት መስሏቸው ከሆነ የባቡር ሀዲድ ሁሌም ውጭ ነው የሚያድረው፡፡›› አቶ ጥኡመ ተክሌ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ሀዲድ ስራ አስኪያጅ በባቡር መስመሮች ዝርፊያ ተበሳጭተው ለሰንደቅ የተናገሩት

‹‹47 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ  መሬት በሙስና የወሰደች የክፍለከተማ አስተናጋጅ በ6ዓመት ከዘጠኝ ወር እስር እንድትቀጣ ተፈረደባት››  ኢትዮቻናል ጋዜጣ

‹‹ከጄኔራል ታደሰ ብሩ ጋር በመሆን መገንጠል የሚባለው ቃል ከመምጣቱ በፊት ለኦሮሞ ህዝብ እውቅና መታገል ጀመርን፡፡ ጄኔራል ታደሰ ለኔልሰን ማንዴላ ሽጉጣቸውን ሰጥተው ሲያሰለጥኑ ተመልክቻለሁ፡፡›› ዶ/ር ሞጋ  ፉሪሳ የኦፍዴን ሊ/መንበር ለሰንደቅ ጋዜጣ

‹‹አሁን አንተ ጋዜጠኛ ነህ፤ ያኔ /በደርግ ጊዜ/ ቢሆን ኖሮ ይህንን ቃለምልልስ እንኳ ማድረግ አትችልም ነበር፡፡ የበፊቱና የአሁኑ ሁኔታ ይለያያል ነው የምልህ፡፡ይህንን የፈለገ ቢሆን እውቅና መስጠት ይኖርብናል፡፡››ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ለአውራምባ ጋዜጣ

‹‹ማረምያ ቤት የሚገኘው የድምፃዊት ሀይማኖት ግርማ  የቀድሞ ባል ‹‹ኦማሂሬ››የተሰኘ መፃህፍ አሳተመ›› ጎግል ጋዜጣ

‹‹ሀይሌ ውስኪ ጠጡ›› አለ እኛ ተወን እንዲሁም ሰክረናል አልነው፡፡›› አውራምባ ታይምስ በሽሙጥ አምዱ የፃፈው

የሳምንቱ አስገራሚ ዜና

‹‹ሀመልማል አባተ ፍትህ በማጣቷ ነጠላ ዜማ እንደምትለቅ አስታወቀች፡፡›› ሪፖርተር ጋዜጣ

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

3 Responses to “የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?”

 1. I really enjoy this section most. It gives me a relief to know what has happened at home

  Thank you ADDISNEGER ONLINE

  and cheers!

 2. ‹‹በ97 ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ሆነን እነዚህን የሀይማኖት መሪዎች ይቅርታ እንዲጠይቁ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ከካቶሊክ መሪ በስተቀር የቀሩት የሰጡን መልስ ተመሳሳይ ነው፡፡ መንግስትንና እግዜአብሔርን መቃወም አትችሉም የሚል መንፈስ ነበረው፡፡ የሓይማኖት መሪዎቹ በመንግስት ሳንባ የሚተነፍሱ ይመስላሉ፡፡›› ዶ/ር መረራ ጉዲና

  I like this guy! He always knows what to say. I think he has been overlooked but probably he is the highest weight opposition in the past.

 3. ‹‹በኮልፌ ቀራኒዬ ክፍለ ከተማ ከውሻ ጋር የግብረስጋ ግንኙነት ያደረጉት የ 80 ዓመት አዛውንት ጥፋተኛ ተባሉ፤ ግለሰቡ ከዚህ ቀደም ከፍየል ጋር ግንኙነት ያደርጉ እንደነበረና ፍየሏም መሞቷን የዓቃቢ ሕግ ምስክሮች ገልፀዋል፡፡›› መሰናዘርያና ሰንደቅ ጋዜጣዎች በጉዳዩ ላይ እንደዘገቡት አዛውንቱ በምርኩዝ ድጋፍ ፍርድ ቤት ቀርበው ድርጊቱን መፈፀማቸውን አምነዋል

  What is going on? Who are these journalists? This is akin to a campaign to destroy the values of the Ethiopian society. The individual could probably be insane. But this is no News to be reported on a Newspaper. Last time one of this tabloids reported the perverse dietary habit of an individual. Are these one of those ‘limtatawi’ journalists???

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.