የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?

የደርግ ባለ ሥልጣናት እና አወዛጋቢው ይቅርታቸው

ሁሉም የአገር ቤት ጋዜጦች የደርግ ባለ ሥልጣናትን የይቅርታ ጉዳይ አንስተው ጽፈዋል። በተለይም ሪፖርተር፣ አውራምባ ታይምስ እና ሰንደቅ ሰፊ ዘገባዎችን አስነብበዋል። ሰንደቅ ጋዜጣ በረቡዕ ዕትም የፊት ገጹ የደርግ ባለ ሥልጣናትን የይቅርታ ጉዳይ አንስቶ ጽፏል፡፡ “የደርግ ባለ ሥልጣናትን የይቅርታ ጥያቄ መንግሥት አያውቀውም” በሚል ርዕስ። ጋዜጣው በቅድሚያ በኮ/ል መንግሥቱ ኀ/ማርያም መዝገብ 18 ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ እንደተወሰነባቸው አስታውሶ ይቅርታቸው ሕገ-መንግሥታዊ ድጋፍ ይኑረው አይኑረው የሚለው ጉዳይ አወዛጋቢ እንደኾነ ይገልጻል። ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ፣ ኮ/ል ፍሰሐ ደስታ፣ ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ፣ ሻምበል ለገሰ አስፋው፣ ሻለቃ አዲስ ተድላ፣ ሌ/ኮ እንዳለ ተሰማ፣ ሻምበል ገሰሰ ወ/ኪዳን፣ ሜጀር ጄኔራል ውብሸት ደሴ እያንዳንዳቸው በሞት እንዲቀጡ ግንቦት 18 ቀን 2000 ዓ.ም የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠ ቢኾንም የአገሪቱ ርዕሰ-ብሔር ግን እስካሁን ፍርዱን ባለማጽደቃቸው ተፈጻሚ እንዳልኾነ ይጠቅሳል።

ከዚህ መዝገብ ሌላ ሻለቃ ካሳዬ አራጌ፣ ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ፣ ሻምበል በጋሻው አታላይ፣ ም/መቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፣ ኮሎኔል ናደው ዘካሪያስ፣ ም/መቶ አለቃ ጴጥሮስ ገብሬ፣ ም/መቶ አለቃ አራጋው ይመር፣ ሻለቃ ደጀኔ ወንድማገኘሁ እና  መቶ አለቃ ደሳለኝ በላይ፣ ሁሉም በተለያየ መዝገብ ጥፋተኛ ኾነው በመገኘታቸው የሞት ቅጣት ተበይኖባቸዋል።

ኮ/ል ካሳሁን ታፈሰ በፍርድ ሂደት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲኾን፣ ፍርድ ቤቱ በሌሉበት የሞት ውሳኔ ያስተላለፈባቸውን ኮ/ል መንግሥቱ ኀ/ማርያምን፣ ሻለቃ አዲስ ተድላን፣ ኮ/ል ብርሃኑ ባየህን ፖሊስ ካሉበት ቦታ አድኖ በመያዝ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነበር።

ይህን የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔን ተከትሎ ተከሳሾቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው አራቱን የሐይማኖት መሪዎችን እና አቶ መለስ ዜናዊን በደብዳቤ ቢጠይቁም መንግሥት ግን በጉዳዩ ላይ በቀጥታ ተሳትፎ አለማድረጉን ሰንደቅ ጋዜጣ አንድ የፍትህ ሚኒስትርን ከፍተኛ ባለሥልጣን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሰንደቅ ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሞያዎች ለቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት ይቅርታ ለማድረግ ከተፈለገ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት ሲሉ ነግረውታል። የዘር ማጥፋት ወንጀል በኢትዮጵያ ሕግ ይቅርታም ኾነ ምኅረት አያስገኝም፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28(1) በእነዚህ ወንጀሎች ለተሳተፉ ጥፋተኞች በሕግ አውጪውም ኾነ በማንኛውም የመንግሥት አካል በምኅረት አይታለፍም።

ኾኖም በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሁለት መሠረት ፕሬዝዳንቱ የሞት ፍርዶችን  ወደ ዕድሜ ልክ እስራት የመቀየር ሥልጣን አላቸው፡፡

ይህ ኾኖ ሳለ የአራቱ ሐይማኖት መሪዎች በጋራ ለባለሥልጣናቱ ምኅረት ለማስገኘት ላለፉት ሁለት ዓመታት እየሠሩ እንደኾነ ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ የቀይ ሽብር ሰማእታት ቤተሰቦች እና ወዳጆች ማኅበር በምኅረት ጥያቄው ላይ እንደ መንግሥት ሁሉ የደረሰው ነገር እንደሌለ ጠቅሶ ኾኖም በመርህ ደረጃ ይቅርታ ቢደረግላቸው እንደማይቃወም መግለጹን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡

አንድነቶች በቅርቡ አንድ ሊኾኑ ይችላሉ

ሰንደቅ ጋዜጣ ታማኝ ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ እንደጻፈው አንድነት ፓርቲ ውስጥ የተፈጠሩት አንጃዎች 99 በመቶ የእርቅ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በቅርቡም የእርቀ ሰላም ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ እንደ አዲስ አመራር ይመረጣል፡፡ በዚህ የእርቅ ጉባኤ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ስየ አብረሃ እና አቶ አንዷለም አራጌ  እንደማንኛውም አባል በመራጭነትና በተመራጭነት መሳተፍ እንደሚችሉ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ ሁኔታው እንደታሰበለት ከሄደ ህክምናቸውን በደቡብ አፍሪካ አጠናቀው ወደ አገርቤት የተመለሱትን የፓርቲውን መሥራች ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ወደ ፖለቲካ ለመመለስ ምቹ ኹኔታን እንደሚፈጥር ጋዜጣው ያለውን ግምት ገልጧል፡፡

ኢትዮጵያ ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኀይል መሸጥ ትጀምራለች

የኮርፖሬሽኑን የስትራቴጂክ ማኔጅመንት ሐላፊ ጠቅሶ ሰንደቅ ጋዜጣ እንዳስነበበው በርግጥም ኢትዮጵያ ሐይል ለመሸጥ ተቃርባለች፡፡ ወደ ጅቡቲ የሚደርሰው መሥመር ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡ ጅቡቲ 50 ሜጋ ዋት ያህል ለመግዛት ፍላጎት ብታሳይም ይህ የሚወሰነው የአገር ውስጥ ፍጆታ ታይቶ ይኾናል ብለዋል ሐላፊው፡፡  እንደጋዜጣው ዘገባ ከአሁን በኋላ የሚቀረው ነገር ስምምነትን መፈራረም ብቻ ነው፡፡

ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ ምን ያህል እንደኾነ ሐላፊው ከመግለጽ የተቆጠቡ ሲኾን የገቢው መጠን በሚሸጠው የኀይል ብዛት እንደሚወሰን ግን ተናግረዋል፡፡ ሽያጩ ከተጀመረ በኋላ ሲያስፈልገን መልሰን መግዛት የምንችልበት ኹኔታ ይኖራል ብለዋል፡፡

ጊልጊል ጊቤ ሁለት የጥገና ሥራው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ጋዜጣው የዘገበ ሲኾን በሂደት ለሱዳን እና ለኬንያ የኀይል ሽያጭ ሊካሄድ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ አገራቱ አንድ ኪሎ ዋት እስከ 35 ሳንቲም ዶላር ሊገዙ እንደሚችሉ ይገመታል ሲል ሰንደቅ ጽፏል፡፡

ቢራ ጨመረ

የብርን ከዶላር ጋር መራራቅ ተከትሎ ሜታ እና ቢጂአይ ቢራ ፋብሪካዎች ባሳለፍነው ሳምንት የዋጋ ማስተካከያ አድርገዋል፡፡ በአማካይ ስምንት በመቶ ጭማሪ እንዳደረጉ የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ  የቅዱስ ጊዮርጊስ ድራፍት የበርሜል ዋጋ ከ310 ወደ 335 ብር ያደገ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ቢራ ደግሞ የሰላሳ ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቢራ ከ10 – 13 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓመት 1.6 ቢሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ ቢመረትም የአገር ውስጥ የቢራ ፍላጎት ግን ከዚህ በብዙ ይልቃል፡፡

ኀይሌ እና ዉስኪ

ኀይሌ በመቶ ሺሕ ዶላር ክፍያ የጆኒ ዎከር ዉስኪ ማስታወቂያ መሥራቱ እያነጋገረ ነው፡፡ ኀይሌ የስፖርት ሰው ኾኖ እንዴት ይህን ይሠራል በሚል የተተቸ ሲኾን እርሱ ግን ‹‹ጠጡ ግን ሐላፊነት ውሰዱ›› የሚል መልእክትን አስተላልፏል፡፡ ኢትዮጵያውያን ውስኪን ዘመድ ወዳጅ ሲጠይቁ ይዘዉት እንደሚሄዱ እና ማስታወቂያውን መሥራቱ ችግር እንደሌለው ይከራከራል፡፡ ከተከፈለው መቶ ሺህ ዶላር ውስጥ ከዚህ ውስጥ 22 በመቶ ለእንግሊዝ መንግሥት በታክስ መክፈሉን፣ 15 በመቶ ለማኔጀሩ እንደሚደርስ እና በእጁ የሚደርሰው ክፍያ 73ሺህ ዶላር ብቻ እንደኾነ ለአድማስ ጋዜጣ ተናግሯል፡፡

እባብ፣ ኤሊ እና የመሳሰሉትን የሚበላው ኢትዮጵያዊ

አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ የኾነው ፀጋዬ ግርማ ጅብ፣ ውሻ፣ አይጥ፣ እባብ እና ኤሊ እንደሚበላ ጎግል ጋዜጣ ሄጄ ዐይቼ አረጋግጫለሁ ሲል አርብ ዕለት ዘግቧል፡፡ ፀጋዬ 22 ዓመቱ ሲኾን እንስሳቱን የሚበላው ከሞቱ በኋላ ጠብሶ በምላጭ እየቆራረጠ ሲኾን በቀን ውስጥ ቢያንስ ስምንት አይጥ ስልቅጥ አድርጎ ይበላል፡፡ አይጦችን በጥሬውም አይምራቸውም፡፡ ዉሻ በሕይወት እያለ በማረድ ጠብሶ ይበላል፡፡ ኤሊንም ቅርፊቷን ፈጥፍጦ በማውጣት እንደሚበላ ጎግል ጽፏል፡፡

የጅብ ቆዳ ይፈለጋል በሚል ቆዳውን ከገፈፈ በኋላ ስጋውን ልቅመሰው ብሎ ከቀመሰው በኋላ እንደወደደው እና ከዚያ በተለያዩ ጊዜያት አራት የሞተ ጅብ መብላቱን ይናገራል፡፡ ፀጋዬ ቤተሰቦቹ ጉዳዩን በማወቃቸው ከቤት አባረውታል፡፡ አሁን በቀን ሥራ ነው የሚተዳደረው፡፡

እስካሁን አንድም ጊዜ አለመታመሙን፣ አእምሮው ጤናማ መኾኑን እንስሳቱ ከመደበኛ ምግቦች የበለጠ ጣፋጭ እንደኾኑለት ይናገራል፡፡ ፀጋዬ እስካሁን ያልሞከረው የድመት ስጋን ነው፡፡ ‹‹ድመት ስጋዋ ያቃጥላል›› ይላል፡፡ ጎግል ጋዜጣ እንደዘገበው፡፡

ፍትህ ጋዜጣ እና ድፍረቱ

ዘወትር አርብ ለኅትመት የሚበቃው ፍትህ ጋዜጣ በመንግሥት ላይ መራር ጽሑፎችን በማተም ይታወቃል፡፡ የዚህ ሳምንቱ ፍትህ ጋዜጣን ያስተዋለ የዚህ ጋዜጣ ዕድሜ ሊያጥር እንደሚችል ሊተነብይ ይችላል፡፡

ፍትህ በአርብ ዕለት ዕትም በፊት ገጹ ላይ የጆተኒ ካርቱን በመሳል ፌዴራሊዝም ላይ ለመሳለቅ ሞክሯል፡፡ ሁለት የኤሕአዴግ ባለውልጣናት ጆተኒ ሲጫወቱ በምስሉ ይታያሉ፡፡ በጆተኒው ላይ ያሉት ተጫዋቾች ደግሞ በክልሎች ተወክለዋል፡፡ የጆተኒው ሁለቱ በረኞች ትግራይን ወክለዋል፡፡ ብዙዎቹ የጆተኒ ተጫዋቾችም ትግራይ የሚል ተጽፎባቸዋል፡፡ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ ሀረሪ አንድ አንድ የጆተኒ ተጫዋቾችን ወክለዋል፡፡

ከዚህ ምስል ዝቅ ብሎ የአቶ በረከት እና የአቶ መለስ ምስል ከኮ/ል መንግሥቱ ኀ/ማርያም ጎን ይታያል፡፡ የዚህ ፎቶ ርእስ ያስደነግጣል፡፡ “ከእናንተ አንዱ ኀጢአት የሌለበት ይውገረው”

ገመና ድራማ እና የሚዲያ ወከባው

ፌደራሊዝም እና ገመና ድራማ ያለፈው ሳምንት የመንግሥት ሚዲያዎችን ሰፊ ሽፋን ተቆጣጥረውት ቆይተዋል፡፡ ለ700 ሺሕ ትንሽ የቀረው የድራማው ተመልካች ድምፅ ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ብቻም ሳይኾን ተከታታይ ቅስቀሳ ሠርቷል፡፡ ሙሉ ዓለም እና ሠራዊት ሰፊ ማስታወቂያ ሠርተውለታል፡፡ በኢትዮጵያ የድራማ ታሪክ እንዲህ ዐይነት የሕዝብ ንቅናቄን የፈጠረ አልተከሰተም ተብሏል፤ አከራካሪ መደምደሚያ ቢኾንም፡፡ የኅትመት እና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል፡፡ አንድም ጋዜጣ ስለ ገመና ሳይጽፍ ወደ ገበያ አልወጣም፡፡

ሸራተን በተካሄደው የሽልማት ሥነ-ሥርዐት በሚኒስትር ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡ አቶ በረከት ስምዖን፣ ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ አባይ ፀሐዬ፣ ሬድዋን ሁሴን እና ዶክተር አሸብር በስፍራው ከተገኙት መካከል ናቸው። ተዋናዮቹ በሽንጣም የሊሙዚን መኪና ሸራተን መጥተው በቀይ ምንጣፍ ተረማምደው ወደበዚሁ ሽልማት ሥነ ሥርዐት ላይ መሠረት መብራቴ 50 ሺሕ ብር፣ ፈቃዱ ተክለማርያም 40ሺሕ ብር፣ ሚፍታህ አሕመድ 30ሺሕ ብር፣ ሜሮን ጌትነት 20 ሺሕ ብር፣ ጀማነሽ ሰለሞን 10 ሺሕ ብር  ተሸላሚ ኾነዋል። ከተወዳዳሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በመኪና እና በበራሪ ወረቀት በመታገዝ በናዝሬት እና በአዲስ አበባ ከፍተኛ ቅስቀሳ ላይ እንደከረሙ ተዘግቧል፡፡ በድራማው ላይ ተሳታፊ ለነበሩት ሁለት ሕፃናትም የብር ሽልማት ተደርጎላቸዋል። ሕጻን ሐዋርያ እና ሕጻን ፓንዶራ እያንዳንዳቸው 5ሺሕ ብር አግኝተዋል። ገመና ድራማ በቀጣይነት በሁለተኛ ኤፒሶድ መታየት እነደሚጀምርም ተገልጿል። “ኤርታ አዋርድ” ተብሎ በየዓመቱ እንደሚቀጥልም እንዲሁ። ድራማውን በተመለከተ ኢቲቪ ከምሽቱ ሁለት ሰዓቱ በሚቀርበው ዜና ላይ ሰበር ዜና በሚመስል መልኩ አቅርቦታል፡፡ “ዝርዝሩ እንደደረሰን እናቀርባለን” ብለው

የአገር ቤት ምርቃት

 • “ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና የካቢኔ አባላት በቀጣዩ ሳምንት ሀብታቸውን ያሳውቃሉ” ሰንደቅ ጋዜጣ
 • “ንጉሣዊ ቤተሰቦች ዋቢ ሸበሌ ሆቴልን ለመረከብ ክፍያ ፈጸሙ” ፎርቹን
 • “አግዚም ባንክ አንድ ቢሊዮን ብር ለሚፈጀው ከቦሌ እስከ መስቀል አደባባይ ሊሠራ ለነበረው መንገድ ብድር አልለቀቀም” ሰንደቅ
 • “ከእንግዲህ ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን?” መሰናዘርያ ጋዜጣ ፊት ገጹ ላይ ስለ ጁልያን አሳንጅ ለጻፈው መጣጥፍ የሰጠው ርእስ
 • “የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ሊሰጥ ነው፡፡” ሰንደቅ
 • “አልጋ ጥሩ አልጋ ነው የሚባለው ሰው ተዝናንቶ የሚተኛበት ሲኾን ነው፤ ተዝናንቶ እስከተኛበት ድረስ ጥሩ አልጋ ነው፡፡” አቶ መለስ ዜናዊ ለዘመን መጽሔት ስለ ፌዴራሊዝም ምቾት የተናገሩት
 • “ሰው ካረጀ በኋላ እኮ ምንም አይሠራም፤ አንድ መጽሐፍ ግን ጀምሬያለሁ፤ my public service የሚል፡፡” አቶ ቡልቻ ለመሰናዘርያ ጋዜጣ
 • “የመንግሥት በጀት ስታየው 40 በመቶ አካባቢ በውጭ ርዳታ እና ብድር የሚሸፈን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ደካማ መንግሥት ነው ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል፡፡ በዚህ ደረጃ ነገሩ ምንም የሚያከራክር አይደለም፡፡” አቶ ክቡር ገና ለሰንደቅ ጋዜጣ
 • “አቶ ስዬ ሞክሮኛል፣ መልስ ሰጥቼዋለሁ፤ መልስ ከሰጠሁት በኋላ ፀጥ ብሏል፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ በግለሰብ ደረጃ ሞክሮኛል፣ መልስ ሰጥቼዋለሁ፡፡ ፀጥ ብሏል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ሞክረውኛል፤ እንዲህ ዐይነት ሰዎችን የሚመጥናቸው እንዲህ ዐይነት ቋንቋ እንደኾነ ገብቶኛል፡” አቶ ልደቱ አያሌው ተናገሩ ብሎ ዘመን መጽሔት እንደጻፈው፡፡
 • “100 ሚልዮን ዶላር ቢከፍሉኝ እንኳ የመጠጥ ማስታወቂያ አልሠራም፡፡” አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ የኀይሌን የውስኪ ማስታወቂያ መሥራት በመቃወም የተናገሩት
 • “አባይ ወይስ ቬጋስን በቀጥታ በቴሌቪዥን ሥርጭት ለማስተላለፍ 99ሺሕ ብር ከፍያለሁ፡፡” ቴዎድሮስ ተሾመ ለአድማስ ጋዜጣ
 • “ከቢዮንሴ ይልቅ ብርቱካንን የሚያደንቁ ወጣቶችን ማፍራት እንፈልጋለን” አቶ ኀይሉ ከፈኔ ለአውራምባ ታይምስ
 • “መድረክ ላይ ስወጣ ማበድ ብቻ ነው የሚታየኝ” ትእግስት ወይሶ ለጎግል
 • “ተመስገን አፈወርቅ እና መስታወት አራጋው በአሜሪካ አገር ይጋባሉ” አርሂቡ መጽሔት
 • “እግዚአብሔር ያክብርህ ብለው ቢመርቁት ይሻል ነበር፡፡” ሠራዊት ፍቅሬ ለኀይሌ የተከፈለው የ100ሺሕ ዶላር ክፍያ ትንሽ መኾኑን ለመግለጽ የተናገረው
 • “የጳጳሱ ሐውልት መቆም እና መፍረስ እኔን አይመለከተኝም፤ እኔን የሚመለከተኝ የወንጌል አገልግሎት ጉዳይ ብቻ ነው፡፡” ዲያቆን በጋሻው ደሳለኝ ለአርሂቡ መጽሔት
 • “የድምፃዊት ሐይማኖት ግርማ ባለቤት ታሰረ፡፡”  ጎግል ጋዜጣ
 • “የአስቴር እና የበገና ስቱዲዮ ውል ስምምነት ፈረሰ፤ “ጨጨሆ” የተሰኘው አልበሟ በቀጣይ ሳምንት በኤሌክትራ በኩል ለአድማጭ ይደርሳል፡፡” አርሂቡ መጽሔት
Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

3 Responses to “የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?”

 1. ሳንድሮስ 20 December 2010 at 7:42 pm

  ሃይሌ ብር ካገኘ እንኻን የዉስኪ ማስታወቅያ ቀርቶ ሌላ ይሰራል….ያትዮጵያን ህዝብ የከዳና ወያኔን ያፈቀረእኮ ነው!!!

 2. Sandros,

  Who are you to judge Haile? Haile is much better than many Ethiopians, in many respects,,, including those who claim to be politicians and human rights advocates.

  Concerning the reconcilation process being going within Andinet party,, I would say that it is still far from being lauded as an achievement. All political oppositions parties have yet to tackle their nonsense divisions. For any sane person, there is no any reason for having different parties such as EDP, UDJ, AEUP other than power mongering and egotic adventure. Who will take them for serious while they are still playing stupid bigotry games in the name of politcs? I rather surrend to the repression of Woyane, than indulge in the amusement play of reckless and disillusioned power mongers who are lost in an ego trip.

  My gratitude and respect for the ‘Fitih Newspaper’!!!!

  It looks that so much attention was given for the ‘Gemena’ TV series. I wish someone gave a good analysis and critic of the social and political impact of this drama series!! Then we can understand the other side of the coin.

  I am realy surprised about the unchaste appetite of Ato Tsegaye, much more dismayed by its reporting on a newpaper. There should have been some judgement or restraint by Newspaper editors whenever they publish such strange stories, in view of the cultural values of the Ethiopian society. It will also save the Newspaper from being an instrument to anti-Ethiopian cultural campaign (though they know nothing about it)

 3. I just love this format.It is funny,brief and well articulated.But from the source it refering,it seems the right source for a new outlet should be from tabloids and privately owned news papers.As to me the true journalism ethics should side with one side of the story rather it provides information from different views and opinions…please give us the informations just like what you are doing here from Addis Zemen, Herald, Woyin, Abiyotawi Democracy and the like and leave the judgment for the reader….but please keep up the good work.

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.