የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?

አቶ ቡልቻ እና አስገራሚው ሕይወታቸው

ጋዜጠኛ ኤልሳቤጥ ዕቁባይ ባለፈው ሳምንት ሥልጣናቸውን ከለቀቁት የቀድሞው የኦፌዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ጋራ ስለ ግል ሕይወታቸው እና ተያያዥ ጉዳዮች ጥያቄ አቅርባላቸው ነበር። በዚህ ሳምንት የቅዳሜ የአዲስ አድማስ ዕትም።

ከተወለዱበት ጊምቢ አውራጃ በትሬንታ ኳትሮ ተንጠላጥለው በወቅቱ ገነት ተደርጋ ትሳል ወደነበረቸው አዲስ አበባ ዘለቁ። ትምህርት ቤት የሚያስገባቸው ሰው ስላጡ ለዘጠኝ ወር ሙሉ በትምህርት ሚኒስቴር ደጅ አድረዋል። “ከዕለታት አንድ ቀን ትምህርት ቤት ስለምትገቡ ፀጉራችኹን ተላጭታችኹ ጠብቁ ተባልን” ይላሉ አቶ ቡልቻ። “ተላጭተን ብንሄድም አልተሳካም” ሲሉም ያክላሉ። በመጨረሻም አቃቂ አድቬንቲስት ቦታ እንደተገኘላቸው እና እንደተማሩ ከዚያ በኋላም ለማስተርስ ትምህርት ወደ አሜሪካ እንደተላኩ ተናግረዋል።

የዘጠኝ ወር የጎዳና ቆይታቸው ጠንካራ እንዳደረጋቸው፣ ለመጀመርያ ጊዜ ፎቶ የተነሱት በዐሥራ አራት ዓመታቸው እንደነበር እና ከዚያ በፊት ፊታቸውን ዐይተውት ስለማያውቁ ማመን እንዳቃታቸው ተናግረዋል። ለመጀመርያ ጊዜ አውሮፕላን ሲሳፈሩ ካይሮ እስኪደርሱ ዐይናቸውን እንዳልገለጡም ተናግረዋል።

በዓለም ባንክ ውስጥ ይሰሩ በነበረበት ወቅት በቦርድ አባልነት ለአራት ዓመታት አገልግለዋል። እንዳልካቸው የእርሻ ሚኒስትር አድርጎ ሾሟቸዋል-ባይቀበሉትም። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአምባሳደርነት ማዕረግ አገልግለዋል። ጋምቢያ፣ ታንዜንያ እና ናይጄሪያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ካንትሪ ሪፕረዘንታቲቭ” ኾነው ሠርተዋል።

አዋሽ ባንክን 50 ሚልዮን ብር አሰባስበው ላይ ታች ብለው ከአጋሮቻቸው ጋራ አቋቁመዋል። ለዐሥር ዓመት የባንኩ ፕሬዝዳንት ኾነው አገልግለዋል።

ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት የአንድ ወር ደሞዛቸው 72 ሺሕ ብር ነበር። “ከአስፕሪን አንስቶ ለዘመዶቼ እልካለሁ” የሚሉት አቶ ቡልቻ በአካባቢያቸው 130 የሚኾኑ ወጣቶችን በእርሳቸው ርዳታ ለትምህርት ወደ አሜሪካ እንደላኩ ተናግረዋል። “እግዜአብሔር ይመስገን እኔ እና ልጆቼ አንራብም” ይላሉ።

አቶ ቡልቻ ስለ አቶ መለስ

በግል በፍጹም ተገናኝተን አናውቅም። በምርጫ 97 ወቅት ፕሮፌሰር በየነ፣ ዶ/ር መረራ እና እኔ ኾነን የአሜሪካ አምባሳደር ከአቶ መለስ ጋራ አገናኙን። “ስንት ልጆች አለዎት፣ ዕድሜዎ ስንት ነው” ብለው ጠየቁኝ እንጂ ከፓርላማ ውጭ ተገናኝተን አናውቅም። አንድ ቀን “ፓርላማ የሽማግሌ የአስታራቂ ሐሳብ ነው ያላቸው” ሲሉ ሰው የምንገናኝ መሰለው። በፍፁም። በርግጥ የጋራ ወዳጆች አሉን። እርሳቸውን ያስተማሩ የእኔ ጓደኞች የኾኑ ናቸው፤ በኦሮሚያ ባለው ኹኔታ እንደማዝንና እንደምቆጣ ያውቃሉ።

ገመና ድራማ የአገርቤት ሚዲያን እያመሰ ነው

“ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከተወለደ እንደ ገመና የሕዝብ ንቅናቄን የፈጠረ ድራማ አላቀረበም” ይላሉ የአገር ቤት ጋዜጦች። ሁሉም የአገር ቤት ጋዜጦች እና መጽሔቶች ስለዚሁ ድራማ የኾነ ነገር ሳይዙ ለኅትመት አልበቁም። በድራማው 300 ተዋንያን የተሳተፉ ሲኾን ኢቲቪ ጥቂቶቹን ለመሸለም ከኢትዮ-ቴሌኮም በሁለት መቶ ሺሕ ብር የድምፅ መስጫ ቁጥር (800) ገዝቷል።  በዚህ ስልክ ቁጥር አንድ ተዋናይ ለመምረጥ ቁጥሩን ሲጫኑ ሁለት ብር ይቆረጣል። እስከ አሁን ድረስ 358 ሺሕ ሰው ድምፅ ሰጥቷል። ኢቲቪ በአንደኛው ዙር ብቻ 700ሺሕ ብር ለመሰብሰብ ችሏል።  ቁም ነገር መጽሔት ነው የዘገበው።

ብርሃኑ ተዘራ እና ማዲንጎ አፈወርቅ ከከባድ የመኪና አደጋ ተረፉ

ሮዳስ መጽሔት እንደዘገበው ብርሃኑ እና ማዲንጎ ሲዊድን እና ኖርዌይ የሙዚቃ ዝግጁት ለማቅረብ በተጓዙበት ወቅት በስዊድን ኖርዌይ በመኪና በመጓዝ ላይ ሳሉ መኪና ተገልብጦ ብርሃኑ እግሩ ላይ ማዲንጎ ከንፈሩና አገጩ ላይ ጉዳት ገጥሟቸዋል። “ከስዊድን ተነስተን 120 ኪሎ ሜትር እንደነዳን ነው ማክኖዶናልድ ገዝተን እረፍት በማድረግ ከመነሳታችን ኩርባ ላይ ስንጠመዘዝ መኪናው ተገለበጠ” ብለዋል ለሮዳስ ጋዜጠኛ። ማዲንጎ ቀበቶ ባለማሰሩ አገጩ ላይ እና ከንፈሩ ላይ ጉዳት ደርሶበታል።

ሚካያ 100ሺሕ ብር ካሳ ተከፈላት

ናሆም ሪከርድሰ ያለ እኔ ፈቃድ ለናሙና የሰጠኹትን ሁለት ሙዚቃዎቼን “ባላገሩ ቁጥር 3” በሚል ኮሌክሽን አካቶ አሳትሞብኛል በሚል ክስ የመሠረተቸው ድምጻዊት ሚካያ ኀይሉ ፍርድ ቤት መቶ ሺሕ ብር ካሳ ወስኖላታል። ከአራት ዓመታት በፊት “ሸማመተው” የተሰኘ አልበሟን በሁለት መቶ ሐምሳ ሺሕ ብር ለናሆም ሪከርድሰ ከመሸጧ በፊት ለዚሁ አሳታሚ በናሙና መልክ የሰጠቻቸው ደረጃቸውን ያልጠበቁ ሥራዎቿ ከአልበሟ አንድ ዓመት ዘግይተው ከባላገሩ ኮሌክሽን መውጣታቸውን ተከትሎ ሚካያ ክስ መመሥረቷን የእንግሊዝኛው ሪፖርተር ዘግቧል።

ፋንታሁን ሸዋንቆጨውና ዳንኤልን ጋሻው ኮበለሉ

የብሔራዊ ቴአትር የሙዚቃ መምርያ ሐላፊ ፋንታሁን ሸዋንቆጨው እና የሬድዮ ፋና የስፖርት ጋዜጠኛ እና የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት የነበረው ዳንኤል ጋሻው ሰሜን አሜሪካ ለእረፍት በሄዱበት እንደኮበለሉ ቁም ነገር ዘግቧል። አርቲስት ፋንታሁን ሸዋንቆጨው ከሁለት ዓመት በፊት 16 አባላት ያሉት የሙዚቃ ቡድን ሲያትል በመሪነት ይዞ ተጉዞ የነበረ ሲኾን ወደ አገር ቤት የተመለሰው ግን ሁለት አባላቱን ብቻ ይዞ ነበር ይላል ቁም ነገር። ቴአትር ቤት አካባቢ ከቢፒአር በኋላ ደስተኛ እንዳልነበረ የዘገበው ቁም ነገር ለመቅረቱ ምክንያቱ ከደረጃው ዝቅ ተደርጎ በመመለሱ ሊኾን እንደሚችል ገምቷል።

አስቴር እና ሆላንድ ካር ተጣምረዋል

ሆላንድ ካር በኢትዮጵያ መኪና ገጣጥሞ በመሸጥ የመጀመርያው ድርጅት ነው። በዚህ ሳምንት ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው ሆላንድ ካር አባይ እና አዋሽ የተሰኙ መኪናዎችን ለደንበኞቹ በጊዜ ለማድረስ እያቃሰተ ነው። በደንበኞች ብዛት እየታመሰ ያለው ሆላንድ ካር መኪናዎቹን ለመግዛት የሦስት ወራት ወረፋ ያስጠብቃል። ኾኖም ሐምራዊ መጽሔት ቅዳሜ ዕለት እንደዘገበው መኪናዎቹን ወደ ሆላንድ አገር ኤክስፖርት ለማድረግ ሙከራ ላይ ነው።  ለዚህም ሆላንድ ካር ከአስቴር አወቀ ጋራ በመኾን የሙዚቃ ኮንሰርት በሆላንድ ከተማ ዲሴምበር 23 ያቀርባል። የአስቴር ሙዚቃ በሚቀርብበት ዝግጅት ሆላንድ ካር አንድ መኪና ለታዳሚዎቹ በዕጣ ያበረክታል።

ከአስቴር ጋራ በተያያዘ ሐምራዊ የዘገበው ሌላኛው ነገር አዲሱን አልበሟን በመግዛት በገና ሰቱዲዮ ማሸነፉ ተሰማ ብሎ ጽፏል። ሐምራዊ መጽሔት ታድያስ አዲስ የተሰኘን የሬድዮ ፕሮግራም ጠቅሶ ቅዳሜ ዕለት እንደዘገበው ኤልያስ መልካ፣ ጆኒ ራጋ ሚካኤል በላይነህ፣ አበጋዝ ክብረ-ወርቅ እና ዳግማዊ ዐሊ ከሌሎች ባለ ሀብቶች ጋራ በመጣመር የመሠረቱት በገና ስቱዲዮ የአስቴርን አዲስ አልበም ገዝቶ አዝዋሪዎች እጅ ሳይገባ የሚከፋፈልበትን መንገድ እያመቻቸ እንደነበር ይታወቃል።

ቁም ነገር መጽሔት እና የውስጥ ሽፋኑ

የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ታምራት ኀይሉ የጋብቻ ቀን ከሳምንታት በፊት ነበር። ሮዝ መጽሔት የሠርጉን ቀን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ዘግቦታል። ቁም ነገር በራሱ መጽሔት፣ በቅዳሜ ዕትሙ የሠርጉን ሂደት የሚያሳዩ ፎቶዎችን ለኅትመት አብቅቷል። በታምራት ሠርግ ላይ ቴዲ አፍሮ ተገኝቶ መዝፈኑ በሚዲያ ሰዎች ዘንድ መነጋገርያ ኾኖ ሰንብቷል።

የአገር ቤት ምርቃት

 • “በአንድ ብሩ ምክንያት ይኼ ነው ተብሎ የተከፈለኝ አንድም ብር የለም።”  የአንድ ብር ኖት ላይ ምስሉ የሚታየው ምኅረት ተፈሪ ለኢቦኒ መጽሔት።
 • “አሁን ፊቴን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማቱ እና ስፖርት መልሻለሁ።” ፊጣ ባይሳ በ15 ዓመት የትዳር አጋሩ ላይ ፆታዊ ጥቃት ፈጽሞ ከእስር ከተፈታ በኋላ ለሮዳስ መጽሔት ከሰጠው ቃለ ምልልስ።
 • “በአቋራጭ በብሔር ብሔረሰቦች ዘፈን መታየት የሙዚቃ ሰው አያሰኝም።” ከባህል ማሳያነት ይልቅ ዝና ማግኛ እየኾኑ ስለመጡት የብሔር ብሔረሰብ ዘፈኖች ቁም ነገር መጽሔት በርእስ አንቀጹ የጻፈው።
 • “አንድ ሰዓት በእግሬ እየተመላለስኩ ነው የተማርኩት፤ አሁንም የተለወጠ ነገር የለም። ለዚህም ነው ፓርላማ ውስጥ የሰው ኑሮ አልተሸሻለም የምለው።” አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለአዲስ አድማስ
 • “አልበሜን በጣም ስሜቴን እየነካኝ ነው የሠራሁት። ወደ መጨረሻ ላይ እንዲያውም እምባዬ እየመጣ ነው የሠራሁት።” ትእግስት ወይሶ ስለ አዲሱ አልበሟ ለሮዳስ መጽሔት ከተናገረችው።
 • “እኔ ሥልጣን ካለቀቅኩኝ የእኔ ተተኪ እንዴት ሥልጣን ይይዛል?።” አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለአዲስ አድማስ
 • “የሚያሰጋ ነገር ካለ ድረ ገጾች የማይዘጉበት ምክንያት የለም።” የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ደብረ ጽዮን ለአውራምባ ጋዜጣ
 • “የመረጃ ነጻነት ሕጉ ተግባራዊ የሚኾንበት ጊዜ እንዲራዘም ጥያቄ ቀረበ።” ሰንደቅ ጋዜጣ
 • “የአንድነት ፓርቲ አባላት ደም ሊለግሱ ነው።” ፍትህ ጋዜጣ
 • “አንድ ባለሥልጣን 100 ሚልዮን ብር ሀብት ለማስመዝገብ ቢመጣ እንዴት ታስተናግዱታላችኹ?” ሰንደቅ ጋዜጣ ለሀብት ምዝገባ ዳይሬክተር ያቀረበው ጥያቄ።
 • “በርግጠኝነት ከሐላፊነቴ እለቃለኹ፤ ተተኪውን አላውቅም።” አቶ ልደቱ አያሌው ለአድማስ
Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

4 Responses to “የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?”

 1. This is really good.It gives info on what is going on home. I like it.

 2. Hey guys, this is the best thing you can give us. Thank you.

 3. Hi Addis Neger
  Well done! Take Five!!!!!!!!!!!!!

 4. ግራ የምገባ ነገር እኮ ነው፡ ፊጣ በይሳ ከ15 ዓመት የትዳር አጋሩ ስባል፡ እድሜዋ ነው ወይስ የጋብቻ ዘመናቸው?

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.