abba

የአክሊሉ ሀብተወልድ ታሪክ ሌላ የኀዘን ትዝታ

“… ለምሳሌ በ1938 እኤአ የእንግሊዝ ንጉሥ እና የእንግሊዝ ንግሥት በኦፊሺያል ግብዣ ለጉብኝት ፓሪስ መጥተው ተሌሎች አምባሳደሮች ጋር እኔም ተጠርቼ ሔጀ ነበር። በፕሮቶኮሉ ደምብ የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጉዳይ ፈጻሚ አቀማመጣቸው ጎን ለጎን ስለነበረ፤ አጠገቡ በምኾንበት ጊዜያት ጣሊያኑ በጣም ሲቆጣ እኔም ኀይለቃል ስለተናገርኩት ሁሉም ጭቅጭቁን ሰምተው፤ የፕሮቶኮሉ ሹም ሌላ የውጪ ጉዳይ ፈጻሚ /ኤጀንት/ በመካከላችን አስቀመጠ።”

አገር የቁርጥ ቀን ላይ ደርሳለች። ግማሹ በዱር በገደል ሕይወቱን ይሰዋል። ሌላው በዲፕሎማሲ ሥራም በጽሑፍም የመጣውን መቅሰፍት ለመቀልበስ ይኾናል የሚለውን ያደርጋል። በአንድዬ ቤት አቅጣጫ ከወደላይ መጥቶ መርዝ የሚያዘንበው የጠላት አውሮፕላን የፈጣሪን መኖር እስከመጠራጠር ያደረሳቸውም “አለህም እንዳንል እንዲህ ይደረጋል” እያሉ ሰቆቃቸውን ይገልጣሉ።

ለወጣቱ አክሊሉ የደረሳቸው ግን ዲፕሎማሲው ነው። ገና በ19 ዓመት እድሜአቸው ትምህርታቸውን ዳር ለማድረስ ደፋ ቀና ሲሉ አገራቸውን በዲፕሎማሲያዊ መድረክ የማገልገል እጣው ወደቀባቸው፤ ያውም በዚያች የቁርጥ ቀን። ወቅቱ የፈጠረባቸውን ሀዘን እና ቁጣ ባገኙት የዓለም አቀፍ መድረክ ሁሉ እየገለጹ አገራቸውን ከደረሰባት ችግር ለመታደግ ያቅማቸውን ጥረት አድርገዋል። የእድሜአቸው ትንሽነት ሳይገድባቸው ከሀያላኑ መንግሥታት ባለሥልጣናት ጋር መጋፈጥ የጀመሩት አክሊሉ በአገልግሎታቸው ዘመን በኤርትራ፣ በሶማሊያ፣ በጂቡቲ እና በጋምቤላ ጉዳይ ላይ መፍትሔ ለማግኘት ያደረጉትን ጥረት እና ያገኙትን ውጤት የምናደንቅበት ሌላ አጋጣሚ ተፈጥሮልናል።

“እኛን በመግደል ኢትዮጵያን ከድህነቷ የምትታደጓት ከኾነ፤ ድርጊታችሁን እንደ በረከት እንቀበለዋለን” በሚል አሳዛኝ የመጨረሻ ቃል የሕይወታቸውን ምዕራፍ አጠቃለው ከ60ዎቹ የአጼ ሀይለሥላሴ ባለሥልጣናት ጋር የተረሸኑት የጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፤ ከፊል የህይወት ታሪክ (memoir) ታትሞ ለገበያ በቅቷል። መጽሐፉ የተጻፈበት ሁኔታ በራሱ ለጸሐፊው የሚኖረንን ክብር የሚጨምር ነው። ጸሐፊው ይህንን ጽሑፍ እንዲያቀርቡ የታዘዙት በአብዮቱ ወቅት የእነዚህን እስረኞች ጉዳይ እንዲያጣራ ለተቋቋመው “መርማሪ ኮሚሲዮን” ለተባለው ተቋም ነው። (አንባቢያን ከዚህ ጽሑፍ ጋር ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማሪያም ስለዚሁ ኮሚሲዮን በቅርቡ በወጣው መጽሐፋቸው “አገቱኒ” ውስጥ ያስቀመጡትን ታሪክ ቢያነቡት አጋዥ ይኾናቸዋል) ጸሐፊው ይህንን ጽሑፍ በሚጽፉ ጊዜ በእስር ላይ ነበሩ። ከዚህም በሁዋላ ነጻ ወጥተው በሰላም ለመኖር አልታደሉም። ይህን ጽሑፍ ባቀረቡ በሳምንቱ ከጓደኞቻቸው ጋር ተረሽነዋል። አክሊሉ ግን በጽሁፋቸው ከሞት ጋር መፋጠጣቸውን የሚጠቁም ፍንጭ እንኳን አያሳዩም። ዘና እንዳሉ በፖለቲካው ውስጥ የነበራቸውን ሚና ያብራራሉ፤ የቃል ትረካ በመሰለ ቅላጼ።

መጽሐፉ በአማርኛው 10 ክፍሎች ያሉት ነው። የመጽሐፉ 92 ገጾች ጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሀብተወልድ ከልጅነታቸው ዘመን የትምህርት ቤት ታሪክ አንስቶ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኾነው እስከተሾሙበት የአጼ ኀይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ማብቂያ ድረስ ያለውን የሥራ ዘመናቸውን ታሪክ ይተርካል። አሳታሚው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ለዚሁ የአክሊሉ ሀብተወልድ መጽሐፍ የእንግሊዘኛ ትርጉም እንዲኖረው እና አብሮ እንዲጠረዝ አድርጓል። ከአማርኛው ሥራ በተለየም እንግሊዘኛው ብዙ ጠቃሚ የኾኑ ነገሮችን አካቷል።

ጸሐፊው ከመገደላቸው በፊት እንደተናገሩት አቶ ከተማ ይፍሩ ያስታወሱት አባባል፣ የተርጓሚው የዶክተር ጌታቸው ተድላ መቅድም፣ የጸሐፊውን ታሪክ በአጭሩ የሚያስረዳ መግቢያን አካቷል። ይህም መግቢያ ጸሐፊውን የሚያውቋቸው የተለያዩ የውጪ አገር ሰዎች በነበራቸው የዲፕሎማሲ ሚና ዙሪያ የሰጧቸውን ምስክርነቶች የሚያጠቃልል ነው። እነኚህ ነገሮች በአማርኛውም የመጽሐፉ አካል ተካተው ቢገኙ ለአማርኛ አንባብያን የበለጠ ጠቃሚ እንደሚኾኑ ግልጽ ይመስላል። ለአሳታሚዎቹ ባይታያቸውም።

ጸሐፊው ለሚጠቅሷቸው አንዳንድ ጉዳዮች እንደዋቤ የሚያስታውሷቸው ሰነዶች የሚያጓጉ ናቸው። በተማሪነት ዘመናቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ አስመልክቶ ለፈረንሳይ አንባቢያን የጻፏቸው የጋዜጣ ጽሑፎች፣ በእርሳቸው እና በቀዳማዊ ኀይለሥላሴ መካከል እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የተጻፉ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ የኾኑ ደብዳቤዎች፣ ውሎች እና ስምምነቶች እንዲሁም ጸሐፊው በተደጋጋሚያነሱት “ፕሮሲቨርባል” የመጽሐፉ መጠን እስከፈቀደ ድረስ ቢካተቱ የበለጠ ጠቃሚ መረጃን ይሰጡ ነበር። ጸሐፊው እነኚህ መረጃዎች መኖራቸውን እና አንዳንዶቹንም ያሉበትን ቦታ ሳይቀር ያስታውሳሉ። በመግቢያውም ላይ መጽሐፉን በጻፉበት ኹኔታ አስቸጋሪነት ምክንያት እነኚህን መረጃዎች ለመጥቀስ በማያስችል ኹኔታ እንደጻፉት ይገልጻሉ። በመኾኑም ከጠቅላላ እውነታ ውጪ ያሉ ዝርዝር ጉዳዮች ከእነዚህ አስፈላጊ መረጃዎች ጋር እንዲገናዘቡም ያሳስባሉ።

በወቅቱ በጉዳዩ ላይ ሥልጣን የነበራቸው ሰዎች ይህን ጽሑፍ ካጻፏቸው በኋላ ምን ያህል ይህን መረጃ እንደተጠቀሙበት ግልጽ አይደለም። ያም ቢኾን ብዙም ጥቅም እንዳልነበረው ከጸሐፊው ሞት በመነሳት መረዳት አያዳግትም። ከጸሐፊው የሕይወት እና የሥራ ታሪክ አረፍ ብለንም የአገሪቱን አሳዛኝ እጣ በድጋሚ በጸጸት እንድናስታውሰው የምንገደደውም እዚሁ ላይ ነው። ከሌለ ጥሪቷ አሟጣ በውድ ዋጋ እንዲማሩላት ያደረገቻቸው ልጆቿ እንዲሁ እንደዘበት እንዳለቁ እንድናስብ እንገደዳለን። ጸሐፊው አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ ከጠንካሮቹ ኀያላን ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው የአገሪቱን ድንበር የተከበረ እና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ለማድረግ ያደረጉትን ጥረት እናደንቃለን። ወዲያውም እንዲህ ያሉትን ሰዎች ሆ ብሎ የሚበላ አገር ታሪክ አካል ስለኾን እንሰቀቃለን። እንደ አክሊሉ ሁሉ በዚሁ የአብዮት ወላፈን ያለቁትን ለቁጥር የሚታክቱ የተማሩ ሰዎች ለማሰብ እንገደዳለን። እርሳቸው ተከራክረው ያስመለሷቸው ድንበሮች ተመልሰው በተወሰዱበት በዚህ ወቅት።

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email