Bulcha Demeksa, leader of the OFDM, addresses a news conference in Ethiopia’s capital Addis Ababa

ቡልቻ ደመቅሳ ይናገራሉ! ልዩ ቃለ ምልልስ

በአዲስ አበባ እምብርት ከሚገኘው አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጀርባ፣ ከዋናው አስፋልት ሁለት መቶ ሜትር ያህል ገባ ብሎ አንድ ቪላ ይታያል።  የግቢው ዙሪያ ገባ በጎስቋላ ደሳሳ ጎጆዎች እና ቤተክርስቲያኑን በተጠጉ ሰዎች  የተሟሟቀ ነው። በግቢው ውስጥ አፌዴንን የሚጋሩት ነዋሪዎች የሚጠቀሙበት አንድ ትልቅ የዲሽ ሰሃን፣ የተሰጣ ጌሾ፣ ጥራጥሬ፣ አሮጌ የሽቦ አልጋ እና የቤት ውስጥ ሠራተኞች እንቅስቃሴ ዐይን  የሚስቡ  ትዕይንቶች ናቸው። ሰባት ክፍሎች የኦፌዴን ቢሮ በነጭ ቀለም አሸብርቋል። ድባቡ የክሊኒክ ይመስላል፡፡ ግርግዳዎቹ ላይ የተለያዩ የቢሮ መጠቆሚያዎች በኦሮምኛ ቋንቋ ተለጠጥፈውበታል። የብርጋዴዬር ጄኔራል ታደሰ ብሩ አባባሎች በአማርኛ ተጽፈው በአራቱም የሳሎኑ አቅጣጫዎች ቀልብን እንዲገዙ ተደርገው ተለጥፈዋል፡፡ ሙሉ  ገ. ከአቶ ቡልቻ  ደመቅሳ ጋር  ቆይታ አድርጓል።

 • የኢሕአዴግን የሥልጣን መተካካት ሂደት እንዴት ታዘቡት?

ይኼ መንግሥት መቼም ትልቁ ድክመቱ ሕዝቡን መናቁ ነው። ሕዝቡ አይገባውም ብለው ነው የሚያስቡት። ሕዝቡ ግን በጣም ንቁ ነው።  ነገር ይገባዋል። ለመኾኑ የአቶ ስዬ አብርሃን መጽሐፍ አንብበኻል?

 • አዎን አንብቤዋለሁ፡፡

እዚያ ላይ የኢሕአዴግን የማታለያ መንገዶች ያመላክታል። የመተካካቱ ሂደትም ዜሮ “ኮንሰፕት” ነው፡፡ ዐየህ ንጉሥ ብቻ ነው በልጁ የሚተካው። ወይም እንደ ሰሜን ኮርያ ያለ አገር ነው ልጅ በአባቱ የሚተካው። አንድ ሰሞን የግብጹ መሪ ሑስኒ ሙባረክ ልጃቸው እንዲተካቸው አዝማሚያ አሳይተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ግን እንዲህ የሚያስቡ ይመስላሉ። ሕዝብ ሳይኾን ራሳቸው እንዳሻቸው ይወስናሉ። ሕዝብ ሳያማክሩ ይሾማሉ- ይሽራሉ፡፡ ይኼ ደግሞ የኮሚዩኒስት አካሄድ ነው። ምናልባትም አቶ መለስ እንደተናገሩት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሥልጣን የሚለቁ ከኾነ፣ ሕዝብ የሚመርጠውን መሪ ሳይኾን ለእርሳቸው የሚቀርባቸውን ሰው ለመሾም የተዘጋጁ ይመስላሉ። ይኼ ትክክል አይደለም፤ የዴሞክራሲ አሠራር አይደለም፡፡ የንጉሣውያን አሠራር ለወጥ ብሎ መጣ ማለት ነው።

 • ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ ነበሩ፤ በተለያዩ መድረኮች ቆይታዎ አሳዛኝ እና ብዙም ደስ የማይል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በፓርላማ (በተወካዮች ምክር ቤት) ቆይታዎ ምን አተረፉ? ምን የበለጠ አሳዘነዎት? ምንስ ተስፋ ሰጠዎት?

እርግጥ ነው በፓርላማ አምስት ዓመት ቆይቼ ነው የወጣኹት። በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ ያየኹትና የተገነዘብኩት ይህን ያህል ተስፋ ሰጪ ወይም አደፋፋሪ አይደለም።  የኢሕአዴግ ሰዎች ምንም አይጠይቁም። ምንም አይነጋገሩም።  ጥያቄ የለም፤ መልስ የለም፤ በቃ ቁጭ። እጅ አውጡ ሲባሉ እጅ ያወጣሉ። ተናገር ተብሎ የታዘዘው  እና ተጽፎ የተሰጠው  ሰው ይናገራል። የቀረው በሙሉ ቁጭ ብሎ እጅ ማውጣትን ይጠባበቃል።

ሰዎቹ ምን እንደምትናገርም አያውቁም። ለመቃወም ብቻ የምንናገር ይመስላቸዋል። ኢሕአዴግም ይህን ይነግራቸዋል። እነዚህ የሚቃወሙ ሰዎች ነገሩን አምነውበት አይደለም፤ እኛን በመጥላት ብቻ ነው። እነርሱ የሚሉትን አትስሙ ይሏቸዋል።  ስለዚህ እኛ የምንናገረው በባዶ ሜዳ ላይ ነበር ማለት ይቻላል።

እነርሱ እኛ የምንለውን እንደ ጠላት ንግግር ነው የሚቆጥሩት፤ አያደምጡም፤  ብዙ ጊዜ ድምፅ መስጠት ያለባችኹ ለኢሕአዴግም ለራሳችሁም ሳይኾን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለኅሊናችኹ ነው እላቸዋለሁ፡፡ ግን ገና እኔ ስናገር ይስቃሉ።

ይኼን በማየት ምንም ያደረግኹት ተስፋ የለም። በጣም አዝናለኹ። አሁን መቼ ነው በአገራችን ተመርጦ የሚመጣ ሰው እውነተኛ የፓርላማ አባል ኾኖ በሰው ሳይኾን በራሱ በግል አስተሳሰቡ የሚመራው እና ሞቅ ያለ የሐሳብ እና የርዕዮት ትግል የሚያደርገው እያልኩ አስባለሁ። ጊዜው መቼ እንደሚኾንም አላውቅም፡፡ ምክንያቱም ይኸው አገርን የመሰለ ትልቅ ነገር አንድ ፓርቲ ኻያ ዓመት ሙሉ አፍኖ ይዞ አቆየ፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ምን ያህል ጊዜ እንደምንቆይ አናውቅም። ኢሕአዴግ እንደኾነ ከገጠር ምንም የማያውቁ ባላገሮችን አምጥቶ ነው ፓርላማ የሚከተው። አሁንም የሚቀጥለው እርሱ ነው። በፓርላማ ቆይታዬ በእውነቱ ጠቀምኩም፤ ተጠቀምኩም የምለው ነገር የለም። እንዲህ ዐይነት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነበር የሚሰማኝ።

 • ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ በይፋ የገቡት ኦፌዴን ፓርቲን ከመሠረቱ በኋላ ነው፤ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ጠብቀው  ነበር? ምንስ አገኙ?

ወደ ፖለቲካው ዓለም ስገባ ምንም የጠበኩት ነገር የለም። ለመታገል ነው ወደ ፖለቲካው የገባኹት። በነገራችን ላይ መጀመርያ ኦሮሞን ለመምራት የፈለገው ኦነግ ነው። ኦነግ እና ኢሕአዴግ አብረው ሊሠሩ አልቻሉም። ኦነግ በጣም ከፍተኛ ጭቆና ከደረሰበት በኋላ ከአገር ወጣ። ይኼ ተጨባጩ ሁኔታ ኾኖ እኔ እና ጓደኞቼ፣ ሌሎችም ኦሮሞዎች ይኼ ነገር በጦርነት አይኾንም በሰላም ነው መኾን ያለበት ብለን ተስማማን። የሚዋጋው ጠላት እና ጠላት ነው እንጂ የአንድ ሕዝብ አንድ ክፍል ሌላውን ሊወጋ አይገባም። እኔ የምወክለው እንደዚህ የሚያስቡትን ሰዎች ነው። ስለዚህ እኔ ወደ ሰላማዊ ትግሉ ስገባ ምንም አልጠበቅኹም፡፡ በጦር ለመዋጋትም ሳይኾን በቃላት እና በሐሳብ ፍጭት ለመታገል ነው የፖለቲካውን ዓለም የተቀላቀልኩት። ግን በኢሕአዴግ በኩል እውነታው የፖለቲካ እና የሐሳብ ፍጭት ሳይኾን የጠመንጃ እና የሰው ጉልበት ብቻ ነው የሚገዛው። ስለዚህ ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው ያለው።

 • ባለፉት አምስት ዓመታት የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ በምን ኹኔታ ላይ ይገኛል? የኦሮሞ የፖለቲካ ጥያቄ ወደ ፊት ተራምዷል ወይስ ባለበት ቆሟል?

የኦሮሞ ሕዝብ ከኦነግም፣ ከእኛም አሁን ካለነው ፓርቲዎች ከሌሎቹም ብዙ ነገር ተምሯል። አንደኛ የኦሮሞ ሕዝብ ከማንም እንደማያንስ፣ ተመርጦ አገሩን ሊያስተዳድር እንደሚችል ግንዛቤውን መጀመርያ ከኦነግ ቀጥሎ ዛሬ ከምንቀሳቀሰው የኦሮሞ ፓርቲዎች ተረድቷል። እውነቱን ለመናገር የኦሕዴድም ቃሉ ሳይኾን ሥራው አንቅቶታል። መጻሕፍትን በኦሮምኛ ቋንቋ ተርጉሞ በየትምህርት ቤቱ ማዳረስ መቻላቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር ላልቻሉ ኦሮሞች መፍትሄ ሰጥቷል። ይህም የኦሮምኛ ቋንቋ እንዲጠናከር፣ እንዲስፋፋ፣ እንዲበረታ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብዬ አስባለኹ። (ምን አልባት ይኼ ለእኔ የመጀመሪያዬ ነው ስለ እነርሱ አዎንታዊ ቃል ስናገር) ምክንያቱም እኛ በተቃዋሚ ጎራ ያለነው ብቻ ሳንኾን ኦሕዴድም ለዚህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ለምን ቢባል የኦሮሞን ፍላጎት እና ሥነ ልቡና (ሳይኮሎጂ)፣ አስተሳሰቡን፣ ማንነቱን አውቆ ወደ ፊት እንዲገሰግስ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያ ኹኔታ ያገባኛል ብሎ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ለመሳተፍ እየጠየቀ ነው። መሬቱን ዝም ብሎ አያስነጥቅም፤ ይከራከራል።  ይኼ ለእኔ አንድ ትልቅ ተስፋ ይሰጠኛል።  ስለዚህ በኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ባሉበት አልቆሙም። ትንሽ ወደ ፊት ተራምደዋል ማለት እችላለኹ። ዛሬ እኮ ባላገር እንኳ ሄደህ ኦሮሞችን ብታነጋግር ስለመብታቸው ያውቃሉ። መሬቴን የመያዝ እና የመጠበቅ፣ የመጠቀም መብት አለኝ ብለው ይነግሩኻል። በቋንቋዬ ለመጠቀም፣ ትምህርት ለመማር መብት አለኝ ይሉኻል። ታዲያ ይኼ ወደ ፊት ፈቀቅ አላለም?

 • ኦህዴድ የኦነግን እና የአንዳንድ የኦሮሞ ፖለቲካ ቡድኖችን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እየቀማና እየመለሳቸው ነው የሚል አመለካከት አለ፤ (እንደ ምሳሌ በቋንቋ መጠቀም፣ የፌዴራሊዝም የመንግሥት መዋቅር፣ ባሕልን ማስተዋወቅ፣ ኦሮሚያ የምትባል አንድ ወጥ ክልል መፍጠር) ይኼን ይስማሙበታል?

አዎን ሙከራው ይኼ ነው። እንደዚያም ኾኖ እኔ ለሠሩት ሥራ እውቅና ሰጥቻለሁ። ምክንያቱም የኦሮሞን መንፈስ አልገደሉም። የኦሮሞን ምኞት እና ፍላጎት አላጠፉም። የኦነግን፣ የኦፌዴንን፣ የኦሕኮን አጀንዳ በመንጠቅ እኛን ለማንኳሰስ ሞክረዋል። ነገር ግን ሕዝቡ ደግሞ ዐይን አለው ያያል፣ ጆሮ አለው ያደምጣል። እኛ የምንናገረውን እና የምንሠራውን ያያል። እነርሱ ከኢሕአዴግ ጋራ ኾነው ምን እንደሚሠሩት ያውቃል። እኛ ከኢሕአዴግ ጋራ አንስማማም። ታዲያ የቱ ነው ትክክል? ከኢሕአዴግ ጋራ ኾኖ በኢሕአዴግ ተገዙ የሚለው ነው ወይስ የለም ፍትኀዊ አይደለም አትገዙ የሚለው?

እንደ እውነቱ ከኾነ የኦሮሞ ሕዝብ ብዙ ኾኖ ሳለ ለምንድን ነው ከትግራይ የመጣ አንድ ሰው ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ኾኖ ብዙ ዘመን የሚቆየው? በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ሁሉ እኩል ናቸው ቢባልም ማነው የአንበሳውን ድርሻ ይዞ ሁሉንም ክልሎች እና የመንግሥት መዋቅሮች የሚቆጣጠረው? ይኼን ለሕዝባችን በግልጽ እንነግራቸዋለን። ኦህዴድ ግን ደፍሮ አይነግራቸውም። እንዲያውም ሰጥ ለጥ ብለው እንዲገዙ ነው የሚመክራቸው። ይኼን ደግሞ እነርሱ ያውቁታል።

 • ኦነግ አሁን ላለው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ነባራዊ ኹኔታ አግባብነቱን (ሬሌቫንስ) እያጣ ነው የሚል አመለካከት ከአንዳንዶች ወገን ይሰነዘራል።  ይህን አስተሳሰብ ይጋሩታል?

ይህን አመለካከት በግማሽ ነው የምጋራው፤ በሙሉ አይደለም። አንደኛ ኦነግም ስኅተት አድርጓል። መጀመርያ ቀጥ ብሎ ከኢሕአዴግ ጋር ይሠራ ነበር። ያንን ሥራ መቀጠል ነበረበት። ቀጥሎ በገታራ ፖለቲካ ሳይኾን በለስላሳ ፖለቲካ ከእነርሱ ጋር እየሠራ ሕዝቡንም እያስተማረ፣ አሁኑኑ ኀይል ልውሰድ ሳይል ቀስ እያለ መሥራት እና ሕዝቡን ከኋላው ማሰለፍ ነበረበት። ይኼን ሳያደርግ አኩርፎ ወጣ። ልብ አድርግ እኔ እዚህ ላይ ደግሞ እናገራለኹ። ኦነግ ከኦሮሞ ሕዝብ አእምሮ ወጣ ማለት አይደለም። እስከ አሁን ድረስ በሚያስገርም አኳኋን የኦሮሞ ሕዝብ ኦነግ፣ ኦነግ እያለ ነው።  ሕዝቡ አልጠላቸውም፣ አልናቃቸውም። ለብዙ ዘመን ስለታገሉ በዓለም ላይ የኦሮሞ ተሟጋች፣ የኦሮሞ ተከራካሪ ተብሎ የታወቀ ድርጅት ነው። ስለዚህ ምንጊዜም ቢኾን የኦሮሞ ሕዝብ ኦነግን የሚረሳው አይመስለኝም።  ነገር ግን እነርሱ ጥፋት ሠርተዋል። የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ትንተና ጥናት ባይሠራ ነው እንጂ ሊሠራ ቢችልና ምን ላይ ነው የተሳሳቱት ብሎ ማሰብና መተንተን ቢችል ስኅተት እንዳደረጉ ይገነዘባል። አሁን ግን ስኅተት እንዳደረጉ አልተገነዘበም። እኔ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ኦነግን ነው ቀድመው የሚያነሱብኝ። የኦነግ ሬሌቫንስ አሁንም አልጠፋም።

ስለዚህ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ ተነጋግሮ አንድ መፍትሄ ፈልጎ በማግኘት፣ ወይም ደግሞ ከእኛ ጋራ ተቀላቅሎ አገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ በጋራ ቢሠራ በጣም የተወደደ ይመስለኛል። አንድ አገር ከሌላ አገር ጋራ ሊዋጋ ይችላል። በአንድ አገር ውስጥ ግን ሕዝቡ ለሁለት ተከፍሎ ሲዋጋ ምንጊዜም ሰላማዊ አይኾንም። ለምሳሌ ከኤርትራ ጋራ አንድ አገር ነበርን፣ ተገንጥላ ሁለት አገር ስንኾን እየተፈጠረ ያለውን ችግር ተመልከት። የኤርትራ ሕዝብ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ እና ጎረቤት አገሮች ይሰደዳል። አብረን ብንኾን ኖሮ ችግሩን እንካፈለው ነበር።

 • ከኢትዮጵያ ነጻ የኾነች ኦሮሚያን አስበው ያውቃሉ?

እኔ አሁን ብቻ ሳይኾን ገና ድሮ ኦነግ ሸፍቶ ወደ ሱዳን ከሄደበት ጊዜ ጀምሮ በፍፁም ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ ነጻ እንድትወጣ የሚወራውን ወሬ፣ የሚነገረውን ንግግር ጭራሽ የማልቀበለው ሰው ነበርኩ፤ አሁንም ነኝ። ጥቂት ጎጥ ሊገነጠል ይችላል። አገር እና ሕዝብ ግን አይገነጠልም፤ መብቱን ለማስከበር፣ ዴሞክራሲን ለማስፈን ይታገላል እንጂ። እኛ ኦሮሞች በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሕዝብ ነን። የፖለቲካ ኀይል አግኝተን መብታችንን እንጠይቃለን፣ እናስከብራለን። እኔ በመገንጠል አላምንም። የተገነጠሉት ምን አተረፉ?

የምንታገለው ለእኩልነት፣ ሐሳብን በነጻነት ለመግለጽ፣ ለነጻ ፖለቲካ፣ በነጻነት ለመሰብሰብ፣ ለኢኮኖሚ ነጻነት፣ ለተሻለ ኑሮ እና በአገራችን ላይ እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንድንኾን ነውጂ ለመገንጠል አይደለም። ደግሞስ ከማን ነው የምንገነጠለው? ኦሮሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረ እውነተኛ የአፍሪካ ሕዝብ ነው። በዚህ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድሮ ጀምሮ አብሮ ተደጋግፎ የኖረ ሕዝብ ነው። እኛ የምንታገለው ሥርዐቱን ነው። አሁን ወደ ኋላ ተመልሰን እገሌ ከውጭ መጣ፣ እገሌ ዘሩ እንዲህ ነው ማለት አንችልም። ኢትዮጵያውያኖች፣ ኢትዮጵያውያኖች ናቸው። ሁሉም በሕግ ፊት እኩል መብት አላቸው። ነገር ግን የኦሮሞ ሕዝብ ለብዙ ጊዜ ይኼን መብቱን ተገፎ ስለኖረ ነው እኔም እዚህ ትግል ላይ ከሌሎች ኦሮሞች ጋራ ተደርቤ ለኦሮሞ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ለመታገል የመጣኹት እንጂ ለመገንጠል አይደለም።

 • ስለ ኢትዮጵያ ሕልውና ሰግተው  ያውቃሉ ?

አዎን! ይኼ ስጋት ውጪ አገር ዛምቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ የተባበሩት መንግሥታት ወኪል ኾኜ  በነበርኩበት ጊዜ በየጊዜው ይሰማኝ ነበር፤ በተለይ ኤርትራውያኖች በሚዋጉበት ጊዜ። ያኔ ምናልባትም ይኼ ጥያቄ የኤርትሪውያኖች ብቻ ላይኾን ይችላል፤ ሌሎቹም እንደዚሁ መብታችንን እንጠይቃለን ብለው ሊነሱ ይችላሉ ብዬ እሰጋ ነበር። ለምሳሌ ሲዳሞዎች፣ ሶማሌዎች፣ በዚህ ላይ የእስልምና እና ክርስትና ጉዳይ አለ። እነዚህ ተዳምረው ስጋት ውስጥ የከተቱኝ ወቅት ነበር።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሥት ለብዙ ዘመናት ጠንካራ ነበር። ጠንካራ ስንል ደግሞ ከመከላከያ የዘለለ ጥንካሬ አልነበረውም። ኢትዮጵያ ከድሮ ጀምሮ የመከላከያ ኀይሏን ለመገንባት ሁልጊዜ እንደሞከረች ነው። ኢትዮጵያ ሁል ጊዜ ስላለችበት አካባቢ እና ኹኔታ ንቁ ናት። ያለንበት ጂኦፖለቲክስ በጣም ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ዘወትር መከላከያዋን ትገነባለች። እናም ከታች ከቆላው የሚመጡትን ጠላቶቿን በቀላሉ ትከላከላለች። ይኼን፣ ይኼን ተስፋ በማድረግ፣ ታሪክ በማንበብ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደማትበታተን የተረዳኹበት ጊዜም ነበር።

 • ጄኔራል ታደሠ ብሩን ያውቋቸዋል? ተገናኝታችኹ በኦሮሞ ሕዝብና በኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ተወያይታችሁ ታውቁ ነበር?

እኔ ጄኔራል ታደሠ ብሩን አውቃቸዋለኹ፤ ብዙ ጊዜም አግኝቻቸዋለሁ። ግን ብዙ ዘመን አብረን አልኖርንም። እኔ ከአሜሪካን አገር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ የመጣሁት በ1953 ዓ.ም ነበር፤ በመንግሥቱ ነዋይ ግርግር ጊዜ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እኔ ገንዘብ ሚኒስቴር ገባኹ። የመንግሥት ሠራተኛ ስለኾንኩኝ እንዲሁ ከእርሳቸው ጋራ እንገናኝ ነበር። ከዚህ ተነስቶ በኋላ እርሳቸው ሜጫና ቱለማ የሚባል የኦሮሞ ማኅበራዊ ድርጅት አቋቁመው እዚያ ውስጥ እንገናኝ ነበር። ታደሠ ብሩ በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ያላቸው ቦታ ትልቅ ነው። ለኦሮሞ ሕዝብ ትግል እስከ ሞት ድረስ የተሰዉ። የፊደል ሠራዊት የሚባል የትምህርት እና የንቃት ፕሮግራም በመንግሥት ወጪ አዘጋጅተው ፕሬዝዳንት በመኾን ወደ ገጠሩ የኦሮሞ ክፍል ይጓዛሉ።

በጠቅላላው በኦሮሞ ወደ ኋላ መቅረት ተቆጭተው ኦሮሞ ራስ ገዝ ይኹን፤ ራሱን ይግዛ ነው እንጂ ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ይገንጠል የሚል ሐሳብና አቋም አልነበራቸውም። የእርሳቸው አስተሳሰብ እንደ ፌዴራል አስተዳደር ማለት ነው። ታደሠ በጣም ጀግና፣ ደፋርና ቆራጥ ሰው ናቸው። ካላመኑበት ማንም ሊያስፈራራቸው አይችልም። ኦሮሞችንም ስለመሩ ታላቅ መሪ ናቸው ነው የምለው። በዚያ ወቅት ብዙ የኦሮሞ ወጣቶች ተነቃቁ፣ ተነሱና ተነቃነቁ። ግን መሣርያ ስለሌላቸው ማንንም ሊወጉ አይችሉም። ማንንም ሊያስገድዱ አይችሉም። እና የታደሠ የመጨረሻ ፍልስፍናቸው ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል አይደለም።

 • የኢሕአዴግ ካድሬ የነበረው ተስፋዬ ገብረ አብ ለሁለተኛ ጊዜ ያወጣው (የደራሲው ማስታወሻ) መጽሐፍ ላይ እንደገለጸው ጄኔራል ታደሠ ብሩ በኦሮሞነታቸው ቁጭት ውስጥ የገቡት በኀይለ ሥላሴ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አክሊሉ ሐብተወልድ ጋራ እንደዋዛ ስለኦሮሞ ሕዝብ ሲነጋገሩ ጠ/ሚ አክሊሉ ታደሠ ብሩን አማራ አድርገው ይቆጥሩ ስለነበር ይኼን ባህር የኾነ የኦሮሞ ሕዝብማ አስተምረን ራሳችን ላይ ጠንቅ መፍጠር የለብንም ብለው በመናገራቸው ከዚያች ቅጽበት በኋላ ታደሠ ብሩ ልባቸው ሸፈተ ይለናል። ለነገሩ ካለዎት ቅርበት የተነሳ ይኼን ነገር ያምኑበታል?

እኔ ይኼን በርግጠኛነት ላምን አልችልም። የእርሱ መጻሕፍት ሌላ ሞቲቭ አላቸው። እኔ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድን በደንብ አውቃቸዋለኹ። ብዙ አብሬያቸው ሠርቻለኹ። እርሳቸው እንዲህ ዐይነት ሰብዕና እና አስተሳሰብ ያላቸው ሰው አይደሉም። በጣም የተማሩ እና ሥልጡን ሰው ናቸው። በርግጠኝነት እርሳቸው እንዲህ ሊሉ አይችሉም። ሌላ ሰው አለ ቢለን እንኳን በየዋህነት ልንቀበለው እንችል ነበር፤ በየዋህነት። ስለዚህ ይኼን በእርሳቸው ተነገረ የተባለውን አሉባልታ ለማመን ችግር ገጠመኝ።

አንብበኸዋል መጽሐፉን፤ እርሳቸው አሉ የሚለን (እንዴት እንደዚህ ዝም ብለህ ታያለህ፣ ትምህርት ቤቱ ሁሉ በኦሮሞ ሲወረር እንዴት እንዴት ፖሊስ ኦሮሞ ኾነ ወዘተ) አሉ እየተባለ ነው ወሬው የተነዛው። ግን ይህ ለእኔ ስኅተት ነው፤ ውሸት ነው። የተስፋዬ መጽሐፎች የጋዜጠኛው ማስታወሻ ያለውንም በፋክት አንጻር ብታያቸው ውሸት ናቸው። የሚመስሉ ውሸቶች። ጥቂት እውነት- ብዙ ወሸት የታጨቀበት። ብዙ ኹኔታዎችን ይፈጥር እና እያስመሰለ ይጽፋል፤ ልክ እንደ ልቦለድ።

 • የአፄ ምኒልክ የጦር አበጋዝ ራስ ጎበናን እንዴት ያስታውሷቸዋል?

እንደሚታወቀው ኦነግ “አንተ ጎበና” ካለህ ገደለህ ማለት ነው። ጎበና መኾን በኦነግ ዘንድ እንደመሞት ነው። ለምን- አገራችንን ሸጠ ነው የሚሉት። እኔ ግን እንዲህ አላስብም። በዚህ መንገድም አላስብም። ከኦነግ ባለሥልጣናት ጋራ ተከራክሬያለኹ። አሁንም ቢኾን ለመከራከር ዝግጁ ነኝ። ራስ ጎበና ትልቅ ሰው ናቸው። መጀመርያ ላይ የገቡበትን ቃል የሚያከብሩ ትልቅ ሰው ናቸው። ዐፄ ምንሊክ ሁሉም ቦታ ሲልኳቸው አንድም ጊዜ ሳያወላውሉ ሄደው ተዋግተዋል። እርሳቸው የቅኝ ጉዳይ አያውቁም። የሲዳሞን፣ የወላይታን የኦሮሞን አገር ቅኝ ላድርግ ብለው አይደለም። ንጉሡን እንደ አንድ አገር ንጉሥ፣ አገሪቷን ደግሞ እንደ አንድ አገር ነበር ያዩት።

ራስ ጎበና ከዳተኛ ዐይነት ሰው አልነበሩም፣ ታማኝ ሰው ናቸው፡፡ የተሰጣቸውን ተግባር በታማኝነት ፈጽመዋል። እርሳቸው ዘመናዊ ሰው አልነበሩም። ፈሪ አይደሉም። ጀግና ናቸው። መጨረሻ ላይ እስኪታመሙ ድረስ አንድም ቀን ሳያወላውሉ ወለጋን፣ ሸዋን፣ ጉራጌ አገር፣ አሩሲን በከፊል ሄደው ወግተው በመያዝ ሰዎቹን አንድ አድርገዋል። እርሳቸው አንድ ባያደርጉ ኖሮማ እንዲህ ዐይነት ትልቅ አገር አይኖርም። አገር ከሌለ ደግሞ ተበጣጥሶ መኖር ለማንም አይመችም። እና ምናልባት ዐፄ ምኒልክ እና ራስ ጎበና አንድ አገር ባያደርጉን ኖሮ ከዚያ በኋላ በዚያኑ ጊዜ ፈረንጆች እየመጡ ቮልካናይዜሽን ማለትም እንደ ጅቡቲ፣ ቬትናም፣ ሲንጋፖር ይገዙን ነበር። ኢትዮጵያን ይቀራመቷት ነበር። እናም ለእኔ ትልቅ ሥራ ነው የሠሩትነው የምለው። አንድ ጠንካራ አገር ሠርተው አስረክበውናል። ይህቺ አገር ዛሬ የእኛ ናት። እንደፈለግን ልናደርጋት እንችላለን። ስለዚህ ዐፄ ምኒልክ እና ራስ ጎበናን የማከብራቸው ሰዎች ናቸው።

 • ኢትዮጵያዊ መኾንና መባል ትርጉም ያጡበት ጊዜ ነበር?

እኔ ብዙ ጊዜ ውጭ አገር ስለምኖር ለእኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ውድ ነው። አገር ያስፈልገኛል፤ ያለአገር አይኾንም። አገር ስታጣ “ስቴትለስ” ነው የምትኾነው። እኔ አገር ያጣ መኾን ስለማልፈልግ ሁልጊዜ ኢትዮጵያዊ የሚለው ኮንሰፕት በአእምሮዬ ውስጥ ተቀረጾ እንዳለ ነው። አገሬ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ነች። እንደ ኢትዮጵያዊ እንከራከራለን። ኢትዮጵያ መኖር አለባት። ሁላችንም የኢትዮጵያ አባል መኾን አለብን ብዬ ነው የማስበው።

አንድ ጊዜ አንድ የኤርትራ ሰው ጓደኛ ነበረኝ። አሁንም አለ። የዛሬ ሠላሳ- አርባ ዓመት ኢትዮጵያ ብትንትኗ ነው የሚወጣው አለኝ። ብትንትኗ አይወጣም ብዬ ለአንተ የነገርኩህን ምክንያት ነገርኩት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ኀይለኛ ነው። መንግሥት ከኾነ ከወላይታም፣ ከኦሮሞም፣ ከአማራ ከትግሬም ከሁሉም ስለሚቀጥር፣ ደግሞም ሁሉም መካፈል ስለሚፈልግ፣ መዋጋት ስለሚፈልግ ዋናው መንግሥት እስካለ ድረስ ኑና ተዋጉ ይላል። ወጥተው ለአገራቸው ዳር ድንበር ይዋጋሉ። ስለዚህ እንዴት አድርጋ ትበታተናለች አልኩት። መጀመርያ ኤርትራ  ትገነጠላለች አለኝ። ቀጥሎ …እያለ ቀጠለ። ነገር ግን ዛሬ እነርሱ የባህር በራቸውን ተማምነውና የጣልያን ቅኝ ግዛት ጠባሳዎቻቸውን ይዘው ከአንድነቱ ቢወጡም የሕዝቡን አንድነት ሊፍቁት አይችሉም። ሕዝቡ ሁሉ ልቡ ያለው አንድ ላይ ነው። አብሮ መኖር፣ አብሮ ማደግ ይፈልጋል። ስለዚህ መቼም ቢኾን ኢትዮጵያዊ መኾንና መባል ፋይዳ አለው ባይ ነኝ።

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email