አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከኦፌዴን አመራርነት ተሰናበቱ፤ ዶክተር ሞጋ ፉሪሳ በፕሬዚዳንትነት ተሾሙ

(ሙሉ ገ.)

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ፓርቲ ለስድስት ዓመት በፕሬዝዳንትነት የመሩትን አቶ ቡልቻ ደመቅሳን ከፓርቲው የበላይ አመራርነት በክብርና በምስጋና አሰናበተ፤ ምክትላቸው የነበሩትን ዶክተር ሞጋ ፍሪሳን ደግሞ በፕሬዝዳንትነት ሾሟል፡፡

እሁድ ህዳር 26 ቀን 2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ  ኢየሩሳሌም ሆቴል በተካሄደው የኦፌዴን 3ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የ80 ዓመቱ አንጋፋ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከባለቤታቸው ጋር በመገኘት በጠቅላላ ጉባዔው የተበረከተላቸውን የኦሮሞ ባሕላዊ የወንድና የሴት አልባሳት ለማስታወሻነት ተቀብለው ጡረታ የወጡ ሲሆን  የፓርቲው “የበላይ ጠባቂ”  የሚል ማዕረግና ኃላፊነትም ተሰጥቷቸዋል፡፡

“ከአሁን በኋላ ፓርቲው ከውስጥም ሆነ ከውጪ  ለሚገጥመው ፈታኝ ሁኔታ አስፈላጊ ሲሆን የበላይ ጠባቂ ሆኜ የፓርቲው አመራሮችን አማክራለሁ፣ ከፓርቲው አስታራቂ ሽማግሌዎች ጋር አብሬ እሰራለሁ” ብለዋል አቶ ቡልቻ። “ ከስድስት ዓመት በፊት ከአጋሮቼ ጋር የመሰረትኩት ፓርቲ የሕዝብ ሆኖ በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ “፡፡

በፕሬዝዳንትነት የተሾሙት የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ ፓርቲውን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩና ቀደም ሲል ከብርጋዴዬር ጄኔራል ታደሠ ብሩ ጋር በመሆን ለኦሮሞ ሕዝብ ትግል ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ዋና ጸሐፊው አቶ በቀለ ነጋ ገልጸዋል፡፡

ህዳር 26 ቀን 2003 ዓ.ም የተካሄደው የኦፌዴን ጠቅላላ ጉባዔ ከፕሬዝዳንት ሹም- ሽረት በተጨማሪ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ተስፋዬ ፉፋ እና አቶ ኡርጌሳ ዋኬኔን በምክትል ፕሬዝዳንትነት  ሾሟል፡፡

በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የኦፌዴን ጠቅላላ ጉባዔው አቶ በቀለ ነጋን በዋና ጸሐፊነት፣ አቶ ብርሃኑ እምሩን በረዳት ጸሐፊነት የሾመ ሲሆን፣ አቶ ሙላቱ ገመቹ፣ አቶ ጥሩነህ ገምታ፣ አቶ ረጋሳ በዳኔ፣ ዶ/ር በላይነሽ ይስሃቅ (ብቸኛዋ ሴት)፣ አቶ አብዱረዛቅ መሐመድ፣ አቶ ደምቦባ ቦኩ እና አቶ አክሊሉ ታደሰን የሥራ አስፈፃሚ አባል አድርጎ መሾሙን ፓርቲው  አስታውቋል፡፡

“በፓርቲው የአሰራር ደንብ መሰረት ከኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖችን ከሚወክሉ 35 የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባላት ውስጥ 13 አባላት ተመርጠው ኃላፊነቶችን በመያዝ የፓርቲውን የቀን ተቀን ሥራዎች ያከናውናሉ።” ያሉት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶበቀለ ነጋ  “የዘንድሮው 3ኛው ጠቅላላ ጉባዔ አቶ ጥሩነህ ገምታ፣ አቶ ረጋሳ በዳኔ እና አቶ አክሊሉ ታደሰ ን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥራ አስፈፃሚው አባላት ቀላቅሏል” ብለዋል።

በኦፌዴን ፓርቲ 3ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አንድ መቶ የኦሮሚያ ልዩ ልዩ ዞኖች ተወካዮች፣ የኦሮሞ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ የክልሉ ምሑራንና የመድረክ የአመራር አባላት በሙሉ የተገኙ ሲሆን የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም አሳልፎ ላለመስጠት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

3 Responses to “አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከኦፌዴን አመራርነት ተሰናበቱ፤ ዶክተር ሞጋ ፉሪሳ በፕሬዚዳንትነት ተሾሙ”

  1. Dear Obbo Bulcha, you are one of the few ppl in Ethiopian histroy of politics. I hope others would follow your foot step.

    I wish all the best for you and your party,
    Ewnetu

  2. by the way wikileaks published the first leaked cable of the US embassy in addis.why don’t you guys have some say regarding the leaks though you found them beyond your expectations/wishes?

  3. it is a lesson to EPRDF & the opposition PARTIES. bravoo obbo Bulcha!

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.