Tedy and Dagmawi

ቴዲ አፍሮ በካምፓላ

ቴዲ ታዳሚውን ሞራል ያንሳል እያለ ሲያነሳሳ

ከጥቂት መንደሮች በስተቀር በሁሉም የካምፓላ አካባቢዎች ሐበሻ ማየት የተለመደ አይደለም። በታዋቂዎቹ የካባላጋላ እና የካንሳንጋ ጎዳናዎች ላይ ግን እስኪጠግቡ ድረስ ሐበሾችን ማየት ይቻላል። በኢትዮጵያውያን እና በኤርትራውያን ዜጎች የሚተዳደሩት ብዙ ሬስቶራንቶች የሚገኙት ካባላጋላ ከተባለው ስፍራ በመኾኑ ለአብዛኞቹ መገናኛም መተያያም ጭምር ነው። እዚህ ማንም በአደባባይ የኢትዮጵያዊነትን እና የኤርትራዊነትን ካርድ አውጥቶ አይዘባነንም። ሁሉም በፈካ መልኩ “ሐበሻ” ነኝ የሚለውን መጠርያ መጠቀም ይመርጣል፤ ይወዳል። አንድ ላይ ይሰበሰባል፤ በአንድ የምግብ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ ይበላል፤ ይጠጣል። በቋንቋ የመግባባት ችግር እንኳ ቢፈጠር ሦስተኛውን አማራጭ ይጠቀማል። በእንግሊዝኛ ይንተባተባል።

በካምፓላ ያለው ሐበሻ የሚሰባበሰበው በሬስቶራንት ብቻ አይደለም። በየዓመት በዐሉ ሞቅ ደመቅ ወደሚሉት ሬስቶራንቶች ይጓዛል። በዐል በዐል የሚሸቱትን የአማርኛ፣ የትግርኛ፣ የኦሮምኛ፣ የጉራጊኛ እና የደቡብ ሕዝቦች ዘፈኖች እያደመጠ ትከሻውን ይፈትናል፤ ወገቡን ያውረገርጋል። ለመተያያ የምትኾነውንም ጊዜ የሚያገኘው በዚህ ሰበብ አስባብ ነው። አንዳንድ ጊዜ ኤርትራውያን ከበዐል ጋራ አያይዘው ታዋቂ ድምፃውያንን ከምዕራብ አገር ያስመጣሉ። ኢትዮጵያውያኑም ከዓመታት በፊት ነዋይ ደበበን አስመጥተውት ነበር። የሚወዱትን ድምፃዊ በስደት አገር ኾኖ ማየት የሚሰጠው ስሜት እና ደስታ ወደ አገር ቤት ትዝታ እየመለሰ ስለሚያጫውት እና የቆየ ስሜትን እያከከ ስለሚኮረኩር ብዙዎች በስንት ጊዜ አንዴ ሊገኝ የሚችለውን አጋጣሚ ይናፍቁታል።

ይህንኑ ናፍቆት እውን ለማድረግ ከአንድ ወር በፊት በካምፓላ ባሉ የሐበሻ ሬስቶራንቶች ውስጥ የቴዲ አፍሮ ፖስተር በትልቁ መሰቀል ጀመረ። “ቴዲ አፍሮ በቅርቡ ሊመጣ ነው” ኮንሰርት ሊያቀርብ፤ ወሬው በእያንዳንዱ ሐበሻ ጆሮ ደርሷል። ማንም ግን እውነተኝነቱ ላይ ርግጠኛ አልነበረም። “ይመጣ ይኾናል” ይላል ሁሉም በግማሽ ልቡ። እውነት ኾኖ እስኪያየው የሚናፍቀው በዛ።

ጃንኾይ/ኀይለሥላሴን ሲዘፍን

ቴዲ ወዳጁ ብዙ ነው። በዘፈኖቹ በሚያስተላልፈው መልእክት ምክንያት የሚወክላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው። አብዛኞቹ ምናልባትም አገር ቤት ሳሉ ቴዲን በኮንሰርት የማየት ዕድል አልገጠማቸውም። በካምፓላ ያሉ ስደተኞች እና ለሥራ የመጡ ሐበሾች ለቴዲ ያላቸው ፍቅር እና አድናቆት የሚመነጨው በተለያየ ምክንያት ነው። ለአንዳንዶቹ የስደተኝነት ሕመማቸውን በዜማ እንዲያስታምሙ ያደርጋቸዋል። ለሌሎቹ ደግሞ ፖለቲካዊ ተቃውሟቸውን ከ97ቱ ምርጫ በፊት ስንኝ ቋጥሮ የተረከ ብቸኛ የጥበብ ሰው ነው። በዚሁም ምክንያት ለእስር እስከመዳረግ ደርሷል ብለው ይሟገቱለታል። ጥቂቶች ስለ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ለመዝፈን ወኔ ያለው ድምፃዊ ነው ብለው ያስባሉ። ቴዲ ትርጉሙ ብዙ ነው፤ እንደየሰዉ።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካካል የተፈጠረውን መለያየት “ዳህላክ ላይ ልሥራ ቤቴን” በሚል ቀጭን መሥመር ለማገናኘት የሚጥር ዜመኛ ነው ብለው የሚያወዱስትም ጥቂት አይደሉም። የሐይማኖት ልዩነቶችን አቻችሎ ለማስቀጠል ከፖለቲከኛም ከሐይማኖት አባትም በላይ ግድ ብሎት ግጥም የጻፈ፤ ዜማ ያንቆረቆረ የሚል መወድስ የሚያዘንቡለትም ቁጥራቸው ሕልቆ መሳፍርት ነው። ይኼ ሁሉ ውይይት እና የሐሳብ ልዩነት እንዲሁም ድጋፍ የተሞላበት ጭቅጭቅ የሚካሄደው በአዲስ አበባ እና በአሥመራ አይደለም። በካምፓላ የሐበሻ ሬስቶራንቶች፤ በሐበሾች መካከል ነው።

ቴዲ እየመጣ ነው

ሊመጣ ነው አሁን ተቀይሯል። መምጣቱም ርግጠኛ ኾኗል። በዩጋንዳ ሽልንግ 60 ሺሕ ግድም (500 የኢትዮጵያ ብር ይጠጋል) የሚያስከፍለው የመግቢያ ቲኬት መሸጥ ጀምሯል፤ በየሬስቶራንቱ። ታኅሳስ 2 ቀን 2003 ዓ.ም ተናፋቂ ምሽት ወደ መኾን ተሸጋግራለች። ሁሉም ግን በመግቢያ ገንዘቡ መናር እየተበሳጨ ነው። ካምፓላ ውስጥ የሚኖረውን ሐበሻ ከግንዛቤ ያልከተተ ነው የሚል ሐሳብ ከአንዱ ቡድን ተሰምቶ ሳያበቃ “መቶ እና ሁለት መቶ ዶላር እየተመጸወተ ለሚኖር የኢኮኖሚ እና የፖለቲከኛ ስደተኛ ይህ ያህል ብር መጫን ምን ማለት ነው” የሚለው ይከተላል። ዋጋውን ቀነስ ቢያደርጉት ኖሮ ተሳታፊውን ማብዛት ይችሉ ነበር የሚሉም አልታጡም። ዋናው ግን ቴዲ ሰዓቱን ጠብቆ በቦታው ላይ መገኘቱ ነው። አንዳንድ ለአዘጋጁ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንዳረጋገጡት ከኾነ ቴዲ ኢንቴቤ የደረሰው አርብ ዕለት ከሌሊቱ ሰባት በኋላ ነው። ቅዳሜ ምሽት ከሁለት ሰዓት ተኩል ጀምሮ ለሚያቀርበው ኮንሰርት ሌሊቱን ገብቶ አድሯል።

እጅግ አድናቂ ለኾኑት ከሌሎቹ ቀናት ሁሉ ቅዳሜ የማይመሽ እና የረዘመ መስሏቸዋል፤ ኾኖባቸዋል። በመግቢያ ቲኬቱ ላይ ኮንሰርቱ የሚጀምረው ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እንደኾነ ቢጠቁምም በስፍራው ለተገኙ ግን ሰዓቱ መራዘሙ ተነገራቸው። በዚያ ቅጽበት ቀኑ ከመርዘሙ በላይ ወደ ምጥ የተቀየረባቸውም ነበሩ። ከዚህ በፊት በነዋይ ኮንሰርት ላይ ልምድ ያላቸው ግን “እኩለ ሌሊት ላይ ልክ እንደ ነዋይ ከች ይላል፤ አታስቡ” በሚል ያጽናኑዋቸዋል።

በሕንዳውያን የሚተዳደረው ዲዲስ እየተባለ የሚጠራው የሕፃናት መጫወቻ ስፍራ ልጆቹን ሁሉ ወደ ቤታቸው ከከተተ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ተወዳጅ የኾነውን ድምፃዊ መምጣት ይጠባበቃል። ሐበሾች ተጠራሩ፤ ሚኒ ስከርት ያደረጉት ቆነጃጅት በሰፊው እና በጠንጣለለው የዲዲስ ግቢ ውስጥ እንደ ጨረቃ ምሽቱን ማድመቁን ተያያዙት። በምንም አጋጣሚ ተያይተው የማያውቁ ዕድሉን አገኘን በሚል በዐይን መደባበስ ቀጠሉ። ዐየሁሽ ለየሁሹ እየጦፈ ነው። ሚጢጢ አዲስ አበባ ተፈጠረች። ትንሽዬ አሥመራም እንዲሁ። የሐበሻ ቆንጆ ሴቶች እና መልከ ቀና ወንዶች “ይኼ ሁሉ የት ነበር እስከ ዛሬ?” ይባባላሉ እርስ በርሳቸው እየተጎሻሸሙ። በየቡድን ኾነው ያወጋሉ፤ ዐይን ለዐይንም ይጋጋሉ። ቴዲ የተዘጋጀለት ስፍራ በቅርቡ በግቢው ውስጥ የተሠራው ትልቅ ሲኒማ ቤት ነው። ከሁለት ሺሕ ሰው ያላነሰ የሚያስተናግደው ሲኒማ ቤት ውስጥ ገባ ወጣ የሚለው በዛ።

4፡00 ሰዓት ከምሽቱ፤ ቴዲ የለም። “አይመጣም ወይ?” ይላል አንዱ። “የቴዲ መምጫ እንደ ክርስቶስ የማይታወቅ ስለኾነ ታጥባችሁ ታጥናችሁ ጠብቁ መባሉ ስለገባው መስሎኝ ይኼ ሁሉ ሐበሻ ሽክ ብሎ የተገኘው።” የሚል መልስ ከሌላኛው በኩል ይሰማል። የሰው ሁሉ ጉጉት እየጨመረ ነው። “የካምፓላ ስደተኛ በነበርኹት ዘመን ቴዲ አፍሮ ሲመጣ እኔም ነበርሁ” የሚለውን ታሪክ የታሪካቸው አንድ አካል ማድረግ የሚፈልጉ ሊነጋ ሲል ቢመጣም አይደንቀንም በሚል ተስፋ እየጠበቁት ነው። ሰዓት ማረሳሻ  ሁሉም ባላ ቆርቆሮውን ሃይነከን ቢራ በሦስት ሺሕ የዩጋንዳ ሽልንግ (ኻያ አምስት ብር) እየሸመተ ይጎነጫል። ሽር ብጥስ የሚሉትን ጭናቸው የተጋለጠ እና ቆዳቸው እንደ ብርቱካን የተላጠውን የሐበሻ ሴቶች ከቢራው ጋራ የሚያወራርዱት የሐበሻ ወንዶች ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። በሰዓቱ መርፈድ ከሚበሳጨው እና ከሚቆጣው ይልቅ የሲኒማ ቤቱን ዙሪያ ገባ እየተሽከረከረ በማይገኘው ዕድል የሚደሰተው ብዙ ነበር። በስደተኝነት ዘመን የተሰባሰበ ሐበሻ ለማግኘት የሚችልበት ዕድሉ ጠባብ ነው።

ከምሽቱ 6፡00 ሰዓት። የመምጫው ሰዓት ቀርቧል እና ሲኒማ ግቡ! ማንም ያንን መለከት የሚነፋ አልነበረም። በድንገት ግን የኢትዮጵያ ሙዚቃ መሰማት ጀመረ። ተናፋቂው መጥቷል። እርሱ ግን ገና መድረኩን አልያዘውም። የግሩም መዝሙር እና የዳግማዊ ዐሊ የጊታር የሙከራ ድምፅ ነው ጥሪውን ያስተጋባው። ጥቂት ቆይቶ የተስተካከለ ድምፅ መሰማት ሲጀምር “ሰላም ነወይ” አለ ከጎሬው ያልወጣ አንድ ድምፅ። ለዚህ ድምፅ የተሰጠው ምላሽ በጩኸት እና በሪታ የታጀበ ነበር። ለቴዲ ከአካል በፊት ድምፅ ይቀድማል። ራሱን በመድረክ ሳይገልጥ በፊት የመጥቻለሁን የምሥራች ለአድናቂዎቹ ደጋግሞ ሲያበሥር የአድናቂዎቹ ጩኸት ያጅበው ነበር። ባለ ጥቁር ጃኬቱ፣ ባለ ጂንስ ሱሪው እና አረንጓዴ ስኬቸር ያደረገው ፈገግተኛው ድምፃዊ ብቅ አለ።

የሲኒማ ቤቱ መቀመጫ ደግሞ ከእርሱ መገለጥ ጋራ ባዶ ኾነ። በመድረኩ እና በወንበሮቹ መካከል ያለው መተላለፊያ ለመርፌ መጠያ በሚያሳጣው የሐበሻ ልጆች ማንነት ተሞላ፤ ተጠቀጠቀ። ቴዲ መድረኩ ላይ ይዘላል። ስፍራው አነሰኝ የሚል ይመስላል። አንድ ቦታ ተረጋግቶ አይቆምም። ካሜራ ማኖች የእርሱን ምስል ለማስቀረት አብሮት የሚሮጥ ካሜራ መያዝ ነበረባቸው። ቴዲ የሚነበብበት ደስታ እና ለታዳሚዎቹ ታማኝነቱን ለማሳየት አንድ ጊዜ ወደ ግሩም ሌላ ጊዜ ዳግማዊ ዐሊ ይሄዳል። አብሯቸው ከጊታሩ ጋራ ይዘናፈላል። የካምፓላ ሐበሾች ደስታ የሚገድላቸው ሰዎች መስለዋል። በግምት 1000 የሚኾነው ሐበሻ ናፍቆቱን በዝላይ እና በጭፈራ እየገለጸ ነው። ቴዲ በመጀመርያው ዙር አራት ዘፈኖችን ካስደመጠ በኋላ ከ25 ደቂቃ በኋላ እንደሚመለስ ተናግሮ ወደ ውስጥ ዘለቀ።

የድምፅ ምጠና ያለህ

ቴዲን ለአድናቂነት እና ለናፍቆት ሲባል ካልኾነ ከመድረክ ለሚመጣው ያልተመጠነ ሙዚቃ ሲባል ማድመጥ የማይታሰብ ነበር። የዘወትሩ የሐበሻ በመድረክ ላይ ያለ የድምፅ መጣኝ ባለሞያ ችግር ካምፓላ ድረዝ ተከትሎት መጥቷል። አንዳንድ ጊዜ ቴዲ ያለውን እንኳ መስማት በማይቻልበት ደረጃ የሳውንድ ሲስተሙ በሙሉ ከመውረድም በላይ የተበላሸ እና የቴዲን ዝና እና ስመኝነት የማይመጥን ነበር። የድምፅ ምጠና ያለህ እስኪያስብል ድረስ። ይህን ጉዳዬ ብለው የሚከታተሉ ግን ቅንጡዎች እና አገር እና ቴዲ ያልናፈቋቸው የሚል ስያሜ ሊሰጣቸው ይችላል። ካምፓላ ግን እንዲህ ዐይነት የወረደ የድምፅ ምጠና ችግር ዐይታ የምታውቅ አትመስልም። የ2010ን የፈረንጆች አዲስ ዓመት ለማክበር ሌሊቱን በሙሉ እየተዘዋወረ ሲመለከት የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በተዘዋወረባቸው ቦታዎች ሁሉ ምድር የሚነቀንቁ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ተመልክቷል። “ከድምፃቸው ግዝፈት የተነሳ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጠጉርህ ሊንጡህ እና የኩላሊትህን ሥራ እንድታዳምጥ ሊያስገድዱህ ይችላሉ፤ እንደዚህ ግን ጆሮህን ብቻ ለይተው አይጠልዙህም።” ይላል።

በ25ቱ ደቂቃ የእረፍት ጊዜ የቴዲ የመድረክ ብቃት ተደነቀ፤ ካላየነው አናምንም የሚል ጽኑ አቋም ለነበራቸውም ቴዲ ገና በመጀመርያው ዘፈን ጃኬቱን አውልቆ በአረንጓዴው ቲሸርት “እነኾ እኔ” ብሎ ስለመጣላቸው በደስታ ሰክረዋል። ደስታቸው በምንም እንዲበረዝባቸው ያልፈለጉ ደግሞ ረባሹን የሳውንድ ሲስተም ዐይተው እንዳላየ፤ ሰምተው እንዳልሰማ ማለፍን መርጠዋል።

ቴዲ ሁለተኛውን ዙር ሲጀምር የ“ሰላም ነወይ” የጥሪ መልእክቱን ከመጋረጃ ጀርባ ኾኖ ዳግም ላከው። የሺሕዎቹ ድምፅ አፀፋውን አሰማ። ቴዲ አሁን አረንጓዴ አልለበሰም። አረንጓዴ አልተጫማም። “RAS TEFRAI” የሚል ቢጫ ቲሸርት እና ቢጫ ስኬቸር አድርጎ ተከሰተ። ከሬጌ ዘፈኑ ጋራ። በሬጌ “የጃንኾይ/ኀይለሥላሴ” ዘፈን እጆች ወደ ሰማይ ተሰቀሉ። የቴዲን እጆች እየተከተሉ ብዙዎች ተወዛወዙ። ጨፈሩ። ቴዲ ግን “አላረካችሁኝም” ይላል በየመሀሉ። “ሞራል” የላችኹም እያለ አድናቂዎቹን ይከሳቸዋል። ድምፃችኹ አይሰማኝም ይላቸዋል። ጭብጨባ እና ሞራል እንዲህ ነው እያለ የያዘውን ማይክ ብብቱ ውስጥ እየከተተ ለጭብጨባ ያነቃቃቸዋል። መድረኩ የእርሱ ብቻ ሳይኾን የእነርሱም ጭምር መኾኑን ለማሳየት “የሞራል” የላችሁም ክሱን ይደጋግምባቸዋል። ያኔ ላንተ ያልኾነ ሞራል እና ጭፈራ፣ ላንተ ያልኾነ ጩኸት እና እልልታ ገደል ይግባ በሚል ስሜት አዳራሹን በሚሞላ ጭብጨባ እና እሪታ ይከተሉታል።

ቴዲ ደስተኝነቱ ይጨምራል። በዘፈን ላይ ዘፈን ይደርባል። በመሀል ከጊታር ተጫዎቾቹ፣ ከድራመሩ እና ከኪቦርድ ተጫዋቹ ጋራ የየግል ችሎታቸውን የሚያሳዩበትን ዕድል እየፈጠረ መድረኩን ያደምቃል። በዚህ ሁሉ ግን በካሴት ውስጥ በጥራት የሚደመጠውን የቴዲን የኮለለ ሙዚቃ እና ድምፅ ለምን አልሰማውም ብሎ የሚጠይቅ የለም። አገሩን የናፈቀ እና ቴዲን በመድረክ እያየ ወደ ትዝታው ለመመለስ የተዘጋጀው ስለሚበዛ ያን ዓለም መቀማት አይፈልግም። አሁን ሰዓቱ የመደሰቻ ብቻ ነው።

ግሩም መዝሙር ቤዚስት

“ሞራሊስቱ ቴዲ”

ከአገሩ ከወጣ 20 ዓመት የኾነው አንድ ኢትዮጵያዊ “እኔ በአገሬ ላይ ቴዲን ለማየት ባልችል ወደ “አገሬ/ዩጋንዳ” ሲመጣ እንኳን ደህና መጣህልኝ ብዬ ለመቀበል ነው የመጣኹት። ዛሬ ሁሉም ዘፈን ቀርቶብኝ አንድ ዘፈን እንዲዘፍንልኝ እፈልጋለሁ። በቅርቡ የለቀቀውን “አልሞላውም ኪሴን” የሚለውን። እሱን ካልዘፈነ እናደድበታለሁ።” አለ። በዚህ ዘፈኑ ቴዲ ሞራሊስት መኾኑን እንዳረጋገጠለት ይናገራል። “እንደ ማኅበረሰብ ከፍተኛ የኾነ የሞራል ልሽቀት ውስጥ መኾናችንን በደንብ እየሳየን ነው። ለገንዘብ ስንል ማንነታችንን ጥለናል። እሴቶቻችን ረስተናል። ስግብግብ እና ቀጣፊዎች፣ ሌቦች እና ቀማኞች ኾነናል። በዚሁ ማንነታችንም ደስታን አጥተናል። ይሉኝታ እና ኅሊና ቢስ ከመኾን ይልቅ ማጣትን እመርጣለሁ እያለ ነው።” ይለዋል ለሞራሊስትነቱ ምክንያት ሲደረድር።

ቴዲ በመድረክ ላይ ኾኖ እንዲህ አለ፦ “እኔ እውነት ልናገር፤ ቆይ አንድ ጊዜ አድምጡኝ፤ እኔ እስከ አሁን ገና መዝፈን አልጀመርሁም። ግን ሞራል የላችሁም። እኔ እናንተን ለማስደሰት ነው የመጣሁት።” የኮንሰርቱን ግማሽ ያህል ከሄደ በኋላ ወደ ማብቂያው ልጓዝ ነው የሚል የመሰላቸው በንግግሩ ብርታትን አገኙ። “በመጀመርያ ላምባዲናን፣ ከዚያ ቀጥሎ ወደ አገር ቤት፣ ከዚያ ቀጥሎ  . . . ማነው ወደ እስር ቤት ያለው? ማነው?” ብሎ ማይኩን ዘረጋላቸው። “ማንም” የሚል የብዙዎች ድምፅ አስተጋባ። እርሱም በቃሉ ሳይኾን በእጆቹ ምልክት አሳየ፤ “እስር ቤትን እዚያው በሚል ዐይነት።”

ቴዲ ላምባዲናን እያዜመ ነው። ላምባዲና የሚለው ዘፈኑ ከመቼውም ጊዜ በተለየ የማይረሳ ትዕይንትን ፈጠረ። ብዙዎች ከመድረክ ጥበቃዎቹ እያመለጡ ቴዲን ለማቀፍ ጥረት አድርገዋል። አንዳንዶች ሊስሙት ተመኝተዋል። ክልከላውን እና ወከባው ግን ሳይደርሱበት አስቀርቷቸዋል። ጥቂቶች ተሳክቶላቸዋል። ከአድናቂዎቹ መሀል ግን ላምባዲናን ሲዘፍን በነበረበት ወቅት ከመድረኩ ላይ ለመውጣት የፈለገ ማየት የተሳነው ሰው ነበር። ዘፈኑ እና ልጁ ተገጣጥመዋል። ቴዲ ይህን ልጅ ከመድረክ እንዲያወርዱት አላደረገም። አቀፈው፤ ተገርሞ እያየ ትክሻው ለትከሻ ገጥመው “ላምባዲናን” አብረው አዜሙ። በካምፓላ ልዩ ትዕይንት “ላምባዲና” እውን የኾነ መሰለ። ብዙዎች በግጥምጥሞሹ ደስ ተሰኙ። ማየት የተሳነው ስደተኛ ከመድረኩ በጥበቃዎች ታጅቦ ሲወርድ ቴዲ ሮጦ ተከተለው። አቅፎ በጆሮው የኾነ ነገር ሹክ አለው። እሱና ልጁ ብቻ ተነጋገሩ፤ ምን እንዳለው ማን ያውቃል? ‘ሌላ ላምባዲና ሰጠኸኝ ብሎት ይኾን’?

ሰው ግን አንድ ጥቄ አለው። የ20 ዓመቱ ስደተኛ የሚፈልገውን ዘፈን ይፈልጋል። ቴዲ አላሰበውም። በአንድ ድምፅ “አልሞላውም ኪሴን” አሉት።  ይህን ዘፈን ከለቀቀው ጀምሮ በመድረክ ላይ እስከ አሁን እንዳልዘፈነው እና የመጀመርያው እንደኾነ ተናገረ። ካምፓላውያን ስደተኞች የመጀርያዎቹ አድማጮች በመኾናቸው ደስታቸውን ገለጡለት። የ20 ዓመቱ ስደተኛም የሚፈልገውን አገኘ።  ቴዲ ወደ ሙዚቀኞቹ ዞሮ ምልክት ሰጣቸው።

“ነፍሴ እጅ እንዳትሰጭው ለኪሴ፣

ታጣይኛለሽ ከራሴ፣” እያለ ቀጠለ። ኪሱን እየገለበጠ ዘፈነ። ሞራሊስቱ ቴዲ።

ቴዲ ከጀርባ ዳግማዊ ዐሊ

ቴዲ መድረክ መቆጣጠር ይችላል። ከታዳሚው የሚወረወርለትን በባንዲራ መልክ የተሠራ ስካርፍ ለብሶ ይዘፍናል። የሚወረወርለትን ባንዲራ በክብር ይቀበላል። “ወደ አገር ቤት” የሚለውን ዘፈኑን ከመዝፈኑ በፊት “አገራችሁን የምትወዱ እና የናፈቃችሁ አይመስለኝም” ብሎ ቆሰቆሳቸው። የሰው ቁስል መነካካት ይችላል። እንደሚናፍቁም፤ እንደሚወዱም፤ እነደሚንገበገቡም ጠንቅቆ ይረዳል። እነዚህን ቃላት መሰንዘር የሚፈጥረው ስሜት ግን በደንብ ገብቶታል። ገንፍሎ የሚወጣው ስሜት ላይ “ወደ አገር ቤትን” ሲክለስበት ጨዋታው እንደሚደምቅ ጠንቅቆ ተረድቷል።

አገር አቋርጬ፣ ተጉዤ ተጉዤ

ታዲያ እንዴት ልመለስ

እግር እና እጄን ይዤ . . . .አገሬ . .እያለ የስደተኝነትን የተከፈለ ልብ ያባባዋል። ምንም ሳይዙ በመመለስ የተጠፈረን ማንነት ያሳያቸዋል። የኢኮኖሚ ስደተኝነትን ፈተና ኖሮ እንዳለፈበት ሰው ኾኖ ይተርክላቸዋል። ስቃያቸውን ያዜምላቸዋል። ስሜቱን የሚረዳለት፣ የልቡን የሚያውቅለት ዜመኛ ያገኘ ታዳሚ ደግሞ ሌላ የሚያይበት ዐይን የለውም። ካምፓላም ያሳየችን ያንን ነው።

በትዝታ ወደ አገር ቤት የወሰደውን ታዳሚ አልለቀቀውም። የነዋይን ዘፈን ያክልለታል። “የዜማ የቅኔ የቀሳውስት አገር” እያለ። “የሐይማኖት የታሪክ ሀብታም፤ ወገን ይዤ እኔ አልረታም” እያለ፤ እያባበለ አገሩን ያስቃኘዋል። ብዙዎች ካምፓላ መኾናቸውን ለመርሳት ይሞክራሉ። ናፍቆቱ የባሰባቸው፣ የጋራ እና ሸንተረር ትዝታ የታወሳቸው፣ የባህሉ እና የሐይማኖቱ አውድ ከአድማስ ማዶ ኾኖ በሐሳብ የሚታያቸው፣ ከሲኒማ ቤቱ ወንበር ላይ ቆመው ጩኸቱን እና ጭፈራውን ያስነኩታል። ከእነዚህ መካከል ልባሳቸውን የጣሉም ነበሩ።

ቴዲ ወደ መጨረሻው ዘፈን ሲጓዝ ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ኾኖ ነበር። ማሳረጊያው ደግሞ “እንዲያው የምሩ” የሚለው ነበር።

አሜሪካን ዐየን ከእግር እስከ ራሱ

ዩሮፕን ዐየነው ከእግር እስከ ራሱ

ሁሉንም ዐየነው ከእግር እስከ ራሱ

ዩጋንዳን ዐየነው ከእግር እስከ ራሱ

መቼም ደስ የሚለው አዲስ ላይ ሲደርሱ

አሥመራ ሲደርሱ።

አሥመሬዎችም አዲስ አበቤዎችም በጩኸት ቤቱን ሞሉት። ቴዲም ወደ መጣበት እነርሱም ወደ ስደት ዓለማቸው ተመለሱ። ካምፓላ ላይ ተገኛኙ፤ ካምፓላ ላይ ተለያዩ።

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email