ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ! [ክፍል አራት፤የመጨረሻ]

መሐመድ ሰልማን

ፒያሳ ቅልብጭ ያለች ናት፤ እንደዚህ ጽሑፍ የተንዛዛች እንዳትመስልህ፡፡ “ችቦ አይሞላም” የተዘፈነለት የሴት ወገብ አይተህ  ወይንም ነክተህ ወይም ደግሞ አቅፈህ ታውቃለህ? እንደዚያ ማለት ናት ፒያሳ፡፡ ትርፍ ነገር አታይባትም፡፡

የፒያሳ ልጅም ቀልጠፍ ያለ ነው፡፡ አይዝረከረክም፡፡ እንደ ሱሉልታ ልጅ በኮት ላይ ሹራብ አይደርብም፡፡ የዶሮ ማነቅያ ለማኞች እንኳ ሳንቲም ከሰጠኻቸው አይቀበሉህም፤ ወይም ደግሞ አንድ ብር አድርገው ይመልሱልኸል፡፡ ሳንቲም ኮተት ነው፡፡ ፒያሳ አካባቢን የሚያዘወትሩ የታክሲ ወያሎችን አስተውለህ ከሆነ ሳንቲም አይሰጡኹም፡፡ እያጭበረበሩህ እንዳይመስልህ፤ ላንተው ኪስ አዝነው ነው፡፡

ለምን እንደኾነ አላውቅም ሌሎች የአዲሳባ ሰፈሮች እንዲሁ አንዳች ነገር እንደጎደላቸው ይሰማኛል፡፡ ለምሳሌ መርካቶን ውሰድ፤ አፍና አፍንጫው አይታወቅም፡፡ ኮልፌን ውሰድ- ሆድና ጀርባው አይታወቅም፤ ቦሌን ውሰድ-ሴቱና ወንዱ አይታወቅም፤ አራት ኪሎን ውሰድ-ምሁሩና መሀይሙ አይታወቅም፤ ሳሪስን ውሰድ ጫቱና ጫኙ አይለይም፤ ጨርቆስን ውሰድ – በርና መስኮቱ አይለይም፡፡ ፒያሳ ሂድ- ‹‹አሟልቶ አይሰጥ ፈጣሪ›› የሚለውን አገርኛ ቢሂል ከማስታወሻ ደብተርህ ትሰርዛለህ፡፡

ይህንን ጽሑፍ የምጽፍልህ አራዳ ላይ ሆኜ ቁልቁል ‹‹ማህሙድ ሙዚቃ ቤት››ን እያየሁ፣ የፒያሳ ወይዛዝርት ሽው እልም እያሉብኝ፣ ያዘዝኩት ማክያቶ እየቀዘቀዘብኝ-እያስሞቅኩኝ፣ ብእሬ ቆንጆ ገላን ባየ ቁጥር እየከዳኝ እንደሆነ ልትገነዘብ ይገባል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ ላይ አንዳንድ የቃላትና የሰዋሰው ግድፈት ቢያጋጥምህ ‹‹ቆንጆ ልጅ በ‹‹ማሃሙድ ጋ››አልፋ ነው›› እያልክ እለፈኝ፡፡

ይህ የፒያሳ ወግ እንደረዘመብህ ይሰማኛል፡፡ በነገርህ ላይ ሰፈሮች ለረዘመ ነገር ምላሻቸው ምን እንደሚመስል ታውቃለህ? መርካቶ ወሬ ካረዘምክ ዋጋ ይጨምሩብኻል፤ ቦሌ ወሬ ሲረዝም ራሳቸውን ያማቸዋል፤ ቦሌ መድኀኔዓለም ያጥወለውላቸዋል፤ ጨርቆስ ወሬ ካረዘምክ ‹‹49 ቁጥር ባስ ታመልጥኸለች›› ይሉኻል፤ የአብነት ልጆች ወሬ ካረዘምክባቸው በሹል ድንጋይ መሀል አናትህን ይፈነክቱኸል፤ የፒያሳ ልጆች ወሬ ስታረዝምባቸው ተጨማሪ ኬክ ያዛሉ፡፡ እጅግ ተናደውብኻል ማለት ነው፡፡

ተጨማሪ ኬክ ከማዘዝህ በፊት ይህንን ጫወታዬን እቋጫለሁ፡፡

የፒያሳ ቤርጎች

መቼ ለታ ማሃሙድ ጋ የመቀጣጠር ጥቅሞቹን ዘርዝሬልህ ሳበቃ፣ የፒያሳን ካፌዎችና ቆንጆ ተስተናጋጆቻቸውን በሚገባ ካስኮመኮምኩህ በኋላ ዶሮ ማነቂያ አስገብቼህ፣ በአላሙዲ አጥር አሻግሬህ፣ ዛሬ ቦታው የኮልኮሌዎች መዋያ እንደሆነ አርድቼህ፣ ጣይቱ ሆቴል አካባቢ አስመሽቼህ ነበር ጫወታዬን የገታሁት፡፡ አስታወስክ?

ዛሬ ትንሽ ጋደም ብለን እናውጋ፤ በፒያሳ ቤርጎዎች፡፡ ለኢትዮጵያ የመጀመርያውን ቤርጎ (በዘመናዊው አጠራር ሆቴል) ያበረከተችው ፒያሳ ናት፡፡ ጣይቱ ሆቴል፡፡ ይህን በልቦናህ ይዘህ ወደ ዝቅተኛ ማደርያዎች ስታማትር ሰራተኛ ሰፈርን ታገኛለህ፡፡

በፒያሳ ማደርያ በሁለት ይከፈላል፡፡ በኮንቦርሳቶና በግድግዳ፡፡ ለምሳሌ በዶሮ ማነቅያና በሰራተኛ ሰፈር ያሉ ማደርያዎች ዋጋቸው ከሀያ እስከ 40 ብር ሲሆን ከቀጣዩ ጎረቤትህ የሚለይህ ግን ኮምቦልሳቶ የሚባል ቀላል “ቴክኖሎጂ” ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ከጎንህ ያለውን የቤርጎ ተከራይ ገመናዎችና በእንቅልፍ ልቡ የሚጫወታቸውን ቀላል የትንፋሽ መሳርያዎች ለመስማት ትገደዳለህ፡፡ ጫን ያለው የሚያንኮራፋ ቤርጎ ተከራይ ሲመጣ ደግሞ የምትሰማው ሙዚቃ ወደ ጃዝ ከፍ ይላል፡፡ ከሁሉም የከፋው ግን ጎረቤትህ ሴት ይዞ የገባ ከሆነ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የሚሰማህ ሙዚቃ የጣልያን ኦፔራ በኦርኬስትራ ታጅቦ ሊሆን ይችላል፡፡

ሠራተኛ ሰፈር በቤርጎ ብቻ ሳይሆን በሕጻናትና ወጣቶችም እየተጥለቀለቀ ነው፡፡ በሰፈሩ ያለውን የሕጻናት ብዛት ስታይ የዚህ ሰፈር አባቶች እና እናቶች ማታ ማታ ምን ያህል ጠንክረው እንደሚሠሩ ይገባኻል፡፡ የትኛው ልጅ የየትኛው ቤት አባል እንደሆነ የሚለየው በሚያሰማው የአለቃቀስ አይነት ነው እየተባለ ይቀለዳል፡፡ የሠራተኛ ሰፈር አባወራዎችና እማወራዎች እነዚህን ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሕጻናት ለማሳደግ ታድያ ለፒያሳ የውድቅት ሰለባዎች አልጋ ያከራያሉ፡፡ ችግሩ አልጋ ተከራይ ሲጠፋ በዚያው በሚከራይ አልጋ ላይ ሌላ ልጅ ሠርተው ያድራሉ፡፡ ሠራተኛ ሰፈር!!!

ፒያሳ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቱሪስቶች አልጋዎችን ታከራያለች፡፡ ‹‹እቴጌ ጣይቱ››እና ባለቤታቸው ከዓመታት በፊት ያባረሯቸው ፈረንጆች የ‹‹እቴጌ ጣይቱ››ን ረከስ ያለ አልጋ ፍለጋ ዳግም ፒያሳን አጥለቅልቀዋታል፡፡ ፒያሳ ጥልያን በጣልያን ሆናለች፡፡ በፒያሳ ከምትገምተው በላይ ፀጉረ ልውጥ በዝቷል፡፡ ለፒያሳ ጩሉሌዎችም አዲስ የሥራ እድል ተፈጥሯል፡፡ ጣይቱ ማዶ ያሉ ሰፈሮች በሙሉ ወደ ኢንተርኔት ካፌ የተለወጡት ወደው አይምሰልህ፡፡ ፈረንጅ በዝቶ ነው፡፡ ከሰሞኑ አንድ አባት አርበኛ በዚያ ጋር አልፈው ምን አሉ መሰለህ፡፡ ‹‹ጥልያንን አባረነው አልነበረም እንዴ?!››

‹‹ዉጥማ ሆቴል››፣ ‹‹ባሮ መኝታ››፣ ‹‹አንኮበር እንግዳ ማረፍያ›› ሁሉም ከጣይቱ ጀርባ የሚገኙ ፈረንጅ ተኮር መኝታ ቤቶች ናቸው፡፡ አንተም እገባለሁ ካልክ ቆዳህን ማድማት አይጠበቅብህም፡፡ ኪስህን እንጂ፡፡

የፒያሳ ጣእም

ፒያሳን በካፌዎቿ እንጂ በምግብ ቤቶቿ የሚያውቃት ሕዝብ እምብዛም ነው፡፡ ይህ ግን ድንቁርና ድህነት ያመጣው ጣጣ እንጂ የፒያሳ ችግር አይደለም፡፡ እመነኝ፡፡ በከተማችን ትልቁ፣ ዝነኛውና ውዱና ተወዳጁ ምግብ ቤት የሚገኘው በፒያሳ እንደሆነ የፒያሳ ልጆችም አንዳንዴ ይዘነጉታል፡፡ የከተማችን ዲፕሎማቶች፣ ባለ ሀብቶች፣ ባለሟሎች ዘናጭ ምግብ መብላት ሲሹ የት የሚሄዱ ይመስልኻል፡፡ ቦሌ እንዳትለኝና እንዳልስቅ፡፡ ፒያሳ ነው የሚመጡት፡፡ ካስቴሌ፡፡

ካስቴሌን ጥቂት ሰው ነው የሚያውቀው፡፡ ምግብ ቤቱ በተፈጥሮው ድምፁን አጥፍቶ ነው የሚሰራው፡፡ ስታየው ምግብ ቤትም አይመስል፡፡ ከማህሙድ ሙዚቃ ቤት በስተቀኝ አምስት እርምጃ አይርቅም፡፡

ካስቴሌ እንደማንኛውም ምግብ ቤት መስሎህ ዘለህ ዘው እንዳትል፡፡ ለነገሩ ዘበኛው ወዝህን አይቶም ቢሆን ይከተልኻል፡፡ የዚህ ቤት ዘበኞች ‹‹ሽሮ-በል››ና ‹‹ስጋ-በል›› ዜጎችን በፍጥነት እንዲለዩ ተደርገው የተገሩ ናቸው፡፡

እዚህ ቤት መብላት ካማረህ ብዙውን ጊዜ አስቀድመህ በስልክ ቦታ አሲዘህ ነው መሄድ ያለብህ፡፡ ደግሞ ተኳኩለህ፣ ዘንጠህ ብትሄድ ይመከራል፡፡ አልያ እጅህን ልጥታጠብ ስትነሳ ተስተናጋጆች አስተናጋጅ መስለሃቸው ‹‹ሄሌ !ማነህ! እዚህ ጋ እስኪ የዳቦ ክሬም ጨምር›› ይሉኸል፡፡ በዚህን ጊዜ ከፍተኛ የሞራል ኪሳራ ደርሶብህ በልቼ እወፍራለሁ ያልከው ሰውዬ ከስተህ ትመለሳለህ፡፡

ዘወትር ምሳ ሰዓት ላይ ‹‹ቪ ኤይት››፣‹‹ፌራሪ››፣‹‹ሀመር››፣‹‹ኤስካሌድ››፣‹‹ኤክስ ፋይቭ››፣ ‹‹ሬንጅሮቨር››፣ ‹‹ኢንፊኒቲ›› የመሳሰሉ የሚሊዮን ብር መኪናዎች በካስቴሌ ምግብ ቤት በር ላይ እንደቀልድ ተሰድረው ታያለህ፡፡ ጠርጣሪ ከሆንክ ደግሞ ትጠረጥራለህ፡፡ አንዳች ባለጸጋ የፒያሳን ምድር ረግጧል ስትል፡፡ አልተሳሳትክም፡፡ በካስቴሌ መናኛ ሰው አይገባም፣አይበላም፡፡ ደጅ የቆሙ መኪናዎችን ግን እንዲጠብቅ ሊፈቀድለት ይችላል፡፡ ከዚህ ቤት በር መኪና ጠብቀህ የሚሰጥህ ‹‹ቲፕ›› ዶሮ ማነቅያ ውስጥ ምን የመሰለ ቅቅል ታዝበታለህ፡፡

የምትወዳት ፍቅረኛ ካለችህ ግን ምን ታደርግ መሰለህ፤ ከየትም እንዴትም ብለህ ብር አጠራቅም፡፡ ፒያሳ ማህሙድ ጋ ቅጠራት፡፡ ፒያሳ ካስቴሌ ምሳ ጋብዛት፡፡ ምን አለ በለኝ ትጋባላችሁ፡፡

የፒያሳ ቡቲኮች

የሆነ ሰፈር ልብስ ልትገዛ ገብተህ ይሆናል፡፡ ሻጩ እንዲህ ይልኸል፡፡ ‹‹አባዬ፤ ይሄን ጃኬት ፒያሳ 800 መቶ ብር ይሉኻል፡፡ እኛ ላንተ ብለን ነው…ባገር ዋጋ ልበሰው…ትከሻ አለህ፤ ሄዶብኻል! (አንተ የትከሻህን ገለባነት ስለምታውቀው ሳቅህ ይመጣል) አታውልቀው ያምርብኻል!  እኔ ለናቴ ልጅ አልሸጠው…!!! ምትገዛበትን ንገረኝና እንስማማ…››

ፒያሳ ዋጋ ይቆለላል፡፡ ሌላ ቦታ 300 ብር የምትገዛውን ልብስ ፒያሳ እጥፉን ትጠይቅኻለች፡፡ ለውድ አፈሯ ግብር መሆኑ ነው፡፡ ምናለ ብትከፍል?! “ከፒያሳ ነው የገዛሁት” ስትላት ሴት ጓደኛህ ትመካብኻለች፡፡ እመነኝ፡፡ ከዚያ በኋላ “መች ነው የምንጋባው?” ትልህ ይሆናል፡፡ ልብስ ጫማ ከገዛህ ከፒያሳ ግዛ፡፡ ዝናህ ለጉረቤት ይተርፋል፡፡ የጨርቆስ ልጅ ከሆንክ ደግሞ ዝናህ በሰፈሩ ይናኛል፤ ኪሎ ስጋ የገዛህ ይመስል፡፡

ሲኒማ  ላ ፒያሳ

ስማኝማ! ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኒማ የት እንደተጀመረ ታውቃለህ? ፒያሳ ነው፡፡ ካላመንክ ሂድ ቴዎድሮስ አደባባይ፡፡ ‹‹ሰቫስቶፖል›› አፍንጫውን ወደቀሰረበት አቅጣጫ ተመልከት፡፡ ሰይጣን ቤትን ወይም ሸይጣን ቤትን ታገኛለህ፡፡ ካላመንከኝ የታሪክ መጸሕፍትን ፈትሽ፡፡ እኔ የነገርኩህን ይደግሙልኻል፡፡ በዚህ ቦታ ‹‹ዋልታ›› ረዥም ፎቅ ሊሰራበት ነው፡፡  ፎቅ ሳይቆምበት ቶሎ እየው፡፡ ታድያ ስትገባ አማትበህ፣ አልያም ‹‹ቢስሚላህ፣አኡዙ ቢላህ›› ብለህ ግባ፡፡ ሰይጣን ቤት መሆኑን አትርሳ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ ሲኒማ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከ 85 በመቶ በላይ የሚገኙት በፒያሳ እንደሆነ ማን በነገረህ፡፡ ፒያሳ የኢትዮጵያ ሆሊውድ ልትላት ትችላለህ፡፡‹‹ሰይጣን ቤት››፣‹‹ሲኒማ ኢትየጵያ››፣ ‹‹ማዘጋጃ ቤት››፣ ‹‹አገር ፍቅር››፣‹‹ሲኒማ አምፒር››፣ ‹‹እስክስታው ቤት››፣ እንዲሁም አገር በቀል የዶሮ ማነቅያ ቪዲዮ ቤቶች ወዘተ ሁሉም ፒያሳ ነው ቤታቸው፡፡

ድሮ ‹‹ሲኒማ ኢትዮጵያ›› አልሳም ያለችህን ፍቅረኛ ወስደህ በፊልም አሳበህ የከንፈር ዳር ድንበሯን የምትጋፋበት ቤት ነበር፡፡ ሆኖም እጣህ ሆኖ ሴት ጓደኛህን ይዘህ የገባህ እለት የህንድ ፊልም ከከፈቱብህ አለቀልህ፡፡ ጓደኛህ ከህንዶቹ እያየች አልሳም ትልኸለች፡፡ ለማፏጨትም ለመሳምም ያልተመቸ ሲኒማ ምኑን ሲኒማ ነው?!

እኔም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይኸው ‹‹ሲኒማ ኢትዮጵያ›› የምሄደው ከደጁ የሚሸጡትን የእንግሊዝኛ መጽሔቶች ለመግዛት ብቻ ሆነ፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል?

የባቅላባ ፍቅር

ፒያሳን የምወድበት ሌላው ምክንያት ባቅላባን ስላስተዋወቀችኝ ነው፡፡(አንዳንዶች ‹‹ቫቅላባ›› ነው የሚባለው ይላሉ፡፡ እኛ ምናገባን፣ ባቅላባውን እንጂ ሆሄያቱን አንበላቸው፡፡)

ትዝታ ገብረትንሳኤ ወመኮንን ባር፡፡

“መኮንን ባር” የፒያሳ አድባር ነው፡፡ ይህ ቤት የማን ነው? የሕዝብ ይመስለኛል፡፡ ባለቤቱን አይቼው አላውቅም፡፡ ደግሞ ባለቤት ያለውም አይመስለኝም፡፡ እንዴት በእኔ እድሜ እንኳ አይታደስም? እነዚያ በሕጻናት መዋያ ትምህርት ቤቶች ያሉትን ወንበሮች የሚመስሉ ትንንሽ ቡናማ መቀመጫዎች፣ ባቅላባ ከሚያካክሉ ትንንሽ ጠረጴዛዎች ጋር አሁንም አሉ፡፡ እንደነበሩት፡፡ ወደፊትም የሚኖሩ ይመስለኛል፤ ከማይደበዝዘው ግርማ ሞገሳቸው ጋር፡፡

አንጀቴን የሚበሉ አስተናጋጆች ያሉበት ቤት ነው፤ መኮንን ባር፡፡ ከቤቱ ጋር ያረጁ፣ ያጎነበሱ ውድ አስተናጋጆች፡፡ ቲፕ ባልተለመደበት ዘመን ሥራ ጀምረው እንጂ እስከዛሬ እነርሱም ባለ ባር በሆኑ ነበር እላለሁ፤ በሆዴ፡፡ ለማንኛውም ለረዥም ዓመት ስላስተናገዳችሁኝ እጅ እነሳለሁ፡፡ ከልቤ፡፡

ባቅላባ ቤት የወንበርን ጥቅም ያወቅኩበት ቤት ነው፡፡ ወንበር ከያዝክ የሚታዘዝህ ይመጣል፡፡ ውሀ ይቀርብልኻል፤ ባቅላባህ ይመጣልኻል፤ ስትጨርስ ጠረጴዛህ ይጸዳልኻል፡፡ ወንበር ከሌለህ ግን ሄደህ፣ ተሰልፈህ፣ ከፍለህ፣ ባቅላባ ለመውሰድ ሌላ ሰልፍ ይዘህ፣ ሹካና ማንኪያ ለማግኘት ደግሞ ሌላ ሰልፍ ይዘህ፣ ውሃ ለማምጣት ደግሞ ሌላ ሰልፍ ጠብቀህ፣ ሰርተህ ትበላለህ፡፡ ወንበር ጥሩ ነው፡፡ ግን ደግሞ ለቀጣይ ትውልድ መልቀቅም ይገባል፡፡ አገኘኹ ብለህ 20 ዓመት በባቅላባ ወንበር ላይ መወዘፍ የለብህም፡፡ ይህች ዓረፍተ ነገር ፖለቲካ መሰለችብኝ ልበል? ግን ንጹሕ ነገረ ባቅላባ ናት።

ባቅላባ ዛሬም አለ፡፡ እስከ ስምንተኛው ሺህ ይኖራል፡፡ ዋጋው ስምንት ብር ደርሷል፡፡ ሰልፉም እንደዚያው፡፡ ሌላ ትውልድ በተራው እየበላው ነው፡፡ በእነዚያው አስተናጋጆች፡፡

ዳላስ ሙዚቃ ቤት

ፍቅረኛህን ‹‹ማሃሙድ ጋር ጠብቂኝ›› ስትላት ተሳስታ ተሻግራ ከጠበቀችህ እድለኛ ናት፡፡ ካንተ በላይ የሚያስደስቷትን ሙዚቃዎች እየሰማች ነው ማለት ነው፡፡ ከዳላስ ሙዚቃ ቤት፡፡ ይህ ቤት የየመን ዝርያ ባላቸው ሐበሾች የተያዘ ነው፡፡ ከፒያሳ ፍቅር እንዲይዝህ ከሚያስችሉ አዚሞች አንዱ ነው፤ ዳላስ፡፡

እጅግ የቆዩ የሚጣፍጡ ሙዚቃዎችን ዛሬም ድረስ ያስኮመኩማል፡፡ ከዚህ ቤት የሚደመጡ ሙዚቃዎች ዘፋኞቹ በህይወት የሌሉ ወይም ደግሞ ዘፋኞቹ ራሳቸው የረሷቸው ሙዚቃዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ‹‹ኦልዲስ-በት- ጉዲስ››፡፡

አንድ አንባቢዬ ዳላስን እንዴት ገለጸው መሰለህ፤ ‹‹The soundtrack of Piassa››፡፡

ዘላለማዊ የሆኑ ዘመን የማይሽራቸው የሱዳንና የአገረሰብ ሙዚቃዎች በዚህ ቤት ይዘወተራሉ፡፡ በቲቪ የምታውቀው ጀማሪ ዘፋኝ እዚህ ዳላስ ሙዚቃ ቤት አካባቢ ሲያንዣብብ ካየኸው አንድ ነገር ጠርጥር፡፡ ሊከትፍ ወይ ሊመነትፍ ነው፡፡

የፒያሳ ጭንቅላት

የፒያሳ ሆድ ካስቴሌ ነው። የፒያሳ ሀብት ወርቅ ቤቶቿ ናቸው፡፡ የፒያሳ ጆሮ ዳላስ ነው፤ የፒያሳ አይን ሲኒማ አምፒር ነው፤ የፒያሳ መልክ ውብ ሴቶቿ ናቸው፡፡ የፒያሳ ራስ ቅል ማዘጋጃ ቤት ነው፡፡ የፒያሳ ጭንቅላት ማን ነው?

ወዳጄ ኾይ! በፒያሳ ውብ ጫማና ልብስ ብትሽቀረቀር፣ ካስቴሌ ሄደህ ከርስህን ብትሞላ፣ አምፒር ሴት ሸጉጠህ ኋላ ወንበር ላይ ብትወሸቅ፣ ፒሳ ኮርነር ብትነጠፍ፣ በባቅላባ ጣእም እጅህን ብትቆረጥም፣ በኤንሪኮ ኬክ ብትንሳፈፍ፣ ማህሙድ ጋ ልጅቱን ጥበቃ በጭንቅላትህ ብትተከል፣ በዳላስ ሙዚቃ ብትመሰጥ፣ በሰንሻይን ሻምፓኝ ብትራጭ፣ የዶሮ ማነቂያን ቁርጥ ብትዘነጥል፣ ጭንቅላት ባዶ ከሆነ ምን ዋጋ አለው?

ጭንቅላትም ልክ እንደሆድህ ምግብ እንደሚፈልግ ታውቃለህ። ለዚህ ፒያሳ ብሪትሽ ካውንስል አለልህ፤ ነበረልህ፡፡ ዛሬ ስልጣን መሰይጠን ነው ብለው በስደት ሆነው አገርህን በእውቀት ከሚያሾሯት ኢትዮጵያውያን የሚበዙት ጭንቅላታቸውን የት የኮተኮቱት ይመስልኻል? በብሪትሽ ካውንስል ቤተ መጻሕፍት ነው፡፡ ብሪትሽ ካውንስል ደግሞ የፒያሳ የእውቀት አድባር ነው፡፡ የዚህን ቤት ውለታ የምታውቀው እውቀት ጠገብ ከሆኑ ሰዎች ጋር በፒያሳ ካፌዎች በአንዱ ቁጭ ብለህ የማውጋት እድል ከገጠመህ ነው፡፡ ብሪትሽ ካውንስል ዓለምን አሳይቷቸዋል፡፡ ጭንቅላታቸውን ትራንስፎርም አድርጎላቸዋል፡፡ የጭንቅላታቸው ትራንስፎርመር እንዳይቃጠል ረድቷቸዋል፡፡ ገና ድሮ፤ የትራንስፎርሜሽንና የምናምን እቅድ ሳይጠነሰስ፡፡ ጠንሳሾቹም ሳይጠነሰሱ፤ ሳይጠነስሱም፡፡

በዚህ ቤት ኢትዮጵያውያን በሼክስፒርኛ ተቀኝተዋል፣ በፕላቶኛ ተፈላስፈዋል፣በመጻሕፍት ባህር ተንቦራጭቀዋል፡፡ በየምእራብ አገራቱ ፈረንጅ ያቃተውን ሳይንስ የሚፈትሉት እኒህ ጥቂት ኢትጵያውያን የብሪትሽ ካውንስል ቡቃያዎች ናቸው፤ የብሪትሽ ካውንስል ውለታም አለባቸው፡፡ አፋቸው በእንግሊዝ አፍ ለማሰልጠን መሄጃ ያጡ ብቅ የሚሉት እዚህ ነበር፤ ለልጆቻቸው መጻሕፍት የሚዋሱ ወላጆችን ማየት ብርቅ በነበረበት ዘመን በብሪቲሽ ካውንስል በሽ ነበሩልህ። ለማትሪክ ዘመቻ የሚዘጋጁ ጮሌዎችም ለንባብ ሲንጋጉ ታያቸው ነበር።

ምን ዋጋ አለው ታድያ፡፡ ይህ የፒያሳ ጭንቅላት ዛሬ ራስ ቅሉ ብቻ ነው ያለው፡፡ በውስጡም ጸረ ሰላም እና ጸረ ልማት የሆኑ እርኩሳን የኤንጂኦ መናፍስትን እያስጮኹ የሚያስወጡ የባህል መድኀኒት አዋቂዎች ተቀምጠውበታል፡፡ ብሪትሽ ካውንስል፣ ነፍስ ይማር!

ማሰርያ አንቀጽ

ፒያሳ እንዲህ ያወጋሁህን ያህል ብቻ አይደለችም። ምኑን ነካሁትና?! ፒያሳ በሕይወት የተሞላች ብትሆንም ብዙ ሲባልላት ባለመስማትህ ግነ ተገርመህ ይሆናል። አትገረም።  “ለእነ እንትና ተዘፍኖ ለፒያሳ ሳይዘፈን ይቅር?” ብለህም ይሆናል። አትቆጭ። ምክንያቱ ወዲህ ነው፤ ፒያሳን ለመግለጽ ቋንቋም ወኔ ይጎለዋል። ቋንቋን ራሱን በፒያሳ ሕይወት ተመስጦ ልታገኘው ትችላለህ። ፒያሳን ለመግለጽ ከመሞከር ይልቅ ፒያሳን መኖር የበለጠ ሐሴት ይሰጣል፤ የስጋም የነፍስም። ይሄው ስንት ዓመታችን ፒያሳን ስንኖራት። የፒያሳ ልጆች ፒያሳን አብረሃቸው እንድትኖር ጋብዘውሃል። ወደ ግብዣው ስትሄድ ግን እስካሁን የሰጠሁህን ምክር በልብህ ያዝ፤ አለበለዚያ የእንትን (የፈለከውን ሰፈርና ከተማ ስም እዚህ ጋ ማስገባት ትችላለህ) ልጅ ነው ብለው ይጥሉሃል። ፒያሳ፤ ማሃሙድ ጋ እንገናኝ።

ተፈጸመ።

ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ! [ክፍል ሦስት]

ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ! [ክፍል ሁለት]

ማሃሙድ ጠብቂኝ! [ክፍል አንድ]

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

27 Responses to “ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ! [ክፍል አራት፤የመጨረሻ]”

 1. Mame…what can I say…breath taking…no maybe funny…oh oh…amazing…I mean extremely extraordinary…I have no words to thank you for describing PIASSA in such a way…well you have no idea how many time i check ANO just waiting this article…am a little bit mad it ended…but everything has an end…even piassa…which is the statue of Menelik if we are going up…MEGA if we are using Churchle road…Ras mekonen if we are using the adewa godana…and eri bekentu if we are going down to aratkilo…so its ok to finish the article…but if it is possible would you write a book about it…because I want my child to know where i grew up (PIASSA)…and i promise i would even by 10 copies my self…the way you write is amazing…even it would make a great name for you…so please think about it…I think you have special gift…so please use it to put one of the most extra ordinary place in Ethiopia for the sake of history…if possible i would love to hear from you on my comment…but if not at least think about it…and finally i would like to thank you for such…I don’t know what to call it…but amazing article…and I will be expecting more of your articles on ANO…thank you.

 2. Muhammed I cann’t wait use some of your tips about piasa. BTW, is piasa for Men only, our sisters will be mad at you as seemd to address it to men only. Thank you anywasys, I enjoyed it.

  • man haven’t u the previous parts, he was talking about them like hell … if not please find it and read it …it will take you to another planet

 3. Weyne, Yecherqos lij balhone, noro!
  Betam Adenkih neber.

  I would like to see your articles compiled as a coplete book, Amazing writing skill, Thank You

 4. … አንጀቴን የሚበሉ አስተናጋጆች ያሉበት ቤት ነው፤ መኮንን ባር፡፡ ከቤቱ ጋር ያረጁ፣ ያጎነበሱ ውድ አስተናጋጆች፡፡ “ቲፕ ባልተለመደበት ዘመን ሥራ ጀምረው እንጂ እስከዛሬ እነርሱም ባለ ባር በሆኑ ነበር እላለሁ፤ በሆዴ፡፡” ለማንኛውም ለረዥም ዓመት ስላስተናገዳችሁኝ እጅ እነሳለሁ፡፡ ከልቤ፡፡

  Sort of funny!!!

 5. One of the most interesting articles I have read in a long long time! It is just brilliant. What can I say? I have followed all the IV parts and let me tell you – this guy is a stroke of genius.

  WOW – word of winner. You deserve many wows. You are a fascinating author. I was struck by the flow of his words. I, myself, have lived it. Its been ages since I left Ethiopia but this paper which exactly mirrors the reality on the ground helps me to connect with my folks.

  I pledge to you that I will be the first to buy your book on amazon the day you released it.

  You are just awesome!

  Thank you very so much.

 6. this is an amazing article written by so many intersting words and attractive way. You are so great and thank you so much for writing this piece. I was really opening my mouth from the begining to the end of the article as it was very touchy, toughtful and immpresive.

  but one thing we have to know is that the piece is more attractive and touchy for those who live around piassa and know piassa from in and out. As a result, as a person who was born and raised around piassa, i found it very sensentioanl and attractive as I admire the writer for his entire portray of piassa using awesome approach.

  thank you so much and please write some more as i am very attracted.

  great job!

 7. Selamawit Bahta 10 December 2010 at 9:07 pm

  Well, the comments are super positive…:) And as a result I’m requesting you kind readers to post/comment some information about the author. So that we can create a fan page on facebook… She/he definitely deserves that…

  Admin, please let us communicate with this gentleman/lady directly so that she/he can tweet us a scoop about our Piassa. Let her/his brand-new fans unite!!

  This could be her/his breakthrough (if she/he is unknown yet)….

  I know Abiye and ANO have their own pages on facebook…. This author has to come out of the closet…

  I loved it! I re-read 3X. …. And yes, I’m a girl from Piassa. I know lots of Ethiopian women don’t duel on a diaspora-political-oriented sites but this article since part one garbbed my attention.

  J’aime cet article!

 8. A classic piece. A bit influenced by sibhat g/egzihabeher though.

  • A classic piece indeed. The writer must be young not to include places like King George Bar, Centro and Trianon also. How about the great Cinema Adua? Moscob Cinema was there across Singer too. Oh! Piassa! I remember the Cave, Menafesha and Addis aba shai biets. When I got old enough to go to a real bar I remember hanging around Black Lion and shooting Carambola at Aroghitua Biet. And lunch at Dehab, oh! Some may remember Samuel Suk too where we used to get our Wanglers. I am sorry to comments by 4Kilo, must be green wioth envy, …but I don’t thing there is anything wrong with being influenced by a great writer like Sebhat.

 9. You don’t have to grow in PIAZZA to appreciate this piece. Millions passed through or hung around PIAZA. We all love an article describing PIAZZA. It is a well put and fascinating article. It can be expanded to be a short “libweled tarik” or included as a spice to a larger novel revolving around some issue.

  I say, thank you for this wonderful work.

 10. wow!
  I read the article in such a rapture. I love Piassa, and I was amazed the whole time, because you were feeling me, and I feel like we have been in many places of together, and danced to same tunes, sitting side by side, but never had the chance to be talk. I hope that we will have a Machiato in Piassa some day. I know that you are going to publish this somewhere sometime. It was one fine piece. keep up the good work, Mo

 11. I grow up in Piassa, and left Ethiopia for the U.S. some forty years ago. Piassa as described here, has been that way then too. It hasn’t changed a bit. I loved your articles. I hope to go back and reconnect pretty soon. Your articles has urged me to do so.
  Thank you

 12. I am partly from Piassa and partly from Sululta, yes, from…I have enjoyed this piece so much I have forgiven your remark about how those of us from Sululta are not that fashion savvy…! Great piece!
  P.S Wearing shirts with sweaters is very fashionable… just ask yebole lijohc!!lol

 13. A brilliant and well written article. the words used and the sentence structure are superp.

  the only downside is that it is about piassa not merkato. what a shame! you probably have not heard the saying: ‘yetem teweled merkato edeg’.

  • man so wrong…YETEM TEWELED ARADA EDEG…srry man that is the fact…and will always be…can’t help it

 14. Derese Getachew 11 December 2010 at 3:26 am

  Mohammed!!!

  Simply superb!!!!!!!!!

 15. This is speechless. You left me with no words. Awesome

 16. I was recommended by my friend to read this article and I read it all. I like it very much as I was a student of English language, long time ago,in Piassa. It reminds me a lot of things. I really like your article and I promise will visit Piassa soon.Thank you,Muhammed.

 17. Ejig betam konjo tsihuf!!! Ke aratum kifloch ejig betam mirtu yihe new!!! Temesasay tsihufochin wodefit endeminkomekum tesfa aregalehu!!!

 18. Casteli ከማህሙድ ሙዚቃ ቤት በስተቀኝ አምስት እርምጃ አይርቅም ? Is casteli on the right from mehamoud muzika bet? mame ye piassa lij adeleshm or mehamoud ga gena alkomekem,,,lol

  fine writing though

 19. Wow!
  It is breathtaking. I am amazed by the words, phrases and short discriptive sentences you have used in your beautiful Piassa ‘painting’. I have enjoyed the way you compared Piassa with other Addis Ababa areas, and the funny and creative discriptions you have used.
  Keep up the good work.

  Thanks

 20. Very amazing how you described Piazza on your writing. I felt that I am watching Piazza on a 3D screen. I can say that this piece worth a thousand pictures.

 21. ወድጄዋለሁ:: አሁን ደግሞ አራቱንም ክፍሎች አንድ ላይ ጠርዛቸው፣ በተባዕት ፆታ የተተረከውን በብዙ ቁጥር አድርገው፣ የሌሎች አንጋፋ ሰፈሮችንም ገጽታ በሌላ ርዕስ ጨምርበት እና አሳትመው:: ታሪክን በዘመነ ታሪኩ ቋንቋ ይሉሃል ይሄ ነው:: (ምክር እንዳይመስልህ፣ ትዕዛዝ ነው::)

 22. wondem betam teru new bezihu ketel

 23. እነዚያ በሕጻናት መዋያ ትምህርት ቤቶች ያሉትን ወንበሮች የሚመስሉ ትንንሽ ቡናማ መቀመጫዎች፣ ባቅላባ ከሚያካክሉ ትንንሽ ጠረጴዛዎች ጋር አሁንም አሉ፡፡ Mo… you made me laugh like crazy…awsome explanation…. dink wenberoch.

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.