የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ

ቴሌ ማኔጅመንቱን ፈረንሳዩ “ኦሬንጅ” ሰጠ

ሳምንታዊዎቹ “አዲስ አድማስ” እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተመው “ዘ ሪፖርተር” የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን (ቴሌ) አስመልክቶ ዜናዎችን ይዘው ወጥተዋል።

አዲስ አድማስ “የቴሌ ሥራ አስኪያጅ ከሐላፊነቴ ዝቅ ብዬ እሠራለሁ አሉ” በሚል ርዕስ ሥር የኮርፖሬሽኑ የሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አምሳሉ ከሐላፊነታቸው መነሳታቸውን ዘግቧል። ሰሞኑን በስብሰባ ላይ የሚገኘው ቴሌ ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ ሌሎች የክፍል ሐላፊዎችን ከሐላፊነታቸው ማሰናበቱን ጋዜጣው አትቷል።  የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ድብረጽዮን ገብረሚካኤል ሥራ አስኪያጁ ከቦታቸው መነሳታቸውን አረጋግጠዋል። “እኛ ሌላ ቦታ እየፈለግንላቸው ነበር። እርሳቸው ግን ዐሥራ አምስት ዓመት ከሠራኹበት መሥርያ ቤት ውስጥ እሠራለሁ በማለታቸው ቴሌ ውስጥ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ ቦታ እየተፈለገላቸው ነው” ሲሉ ለጋዜጣው ተናግረዋል።

የሥራ አስኪያጁ ከቦታቸው መነሳት የፈረንሳይ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ኩባንያ የኾነው “ኦሬንጅ” የቴሌን ማኔጅመንት ከመረከብ ጋራ የተያያዘ መኾኑን “ዘ ሪፖርተር” ጽፏል። “ኦሬንጅ” ለቴሌ ያዘጋጀውን አዲስ የመዋቅር ለውጥ ይፋ ማድረጉንም ጋዜጣው ዘግቧል።

ኢንጂነር ኀይሉ እና አቶ ቡልቻ የፖለቲካ ጫማቸውን ይሰቅላሉ

ሰንድቅ ጋዜጣ በረቡዕ ዕትሙ “የአንጋፋዎቹ ስንብት” የሚል ልዩ ጥንቅር አስነብቧል፡፡ የኦፌዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅስ እና የመኢአዱ ኢንጂነር ኀይሉ ሻውል በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ፓርቲዎቻቸው በሚጠሩት ጠቅላላ ጉባዔ በሌሎች ይተካሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢንጂነሩ የፓርቲ መሪነቱን ለማቆም ውሳኔ ላይ የደረሱት በዕድሜ መግፋት እና በጤና መታወክ ነው፡፡

ኢንጂነሩ የመልቀቂያ ደብዳቤ ሲያስገቡ በጓዶቻቸው እምቢ ቢባሉም እርሳቸው ግን በሐሳባቸው ጸንተዋል፡፡ ኢንጂነሩ በፓርቲያቸው “እንደ ግል ንጉሥ”  ይታዩ ነበር ይላል ጋዜጣው፡፡ አቶ ቡልቻ በበኩላቸው ከ2002 ምርጫ በፊት ፖለቲካ በቃኝ ማለታቸው ይታወቃል፡፡ ሕዳር 26 በሚካሄድ ጠቅላላ ጉባዔ አቶ ቡልቻ ፖለቲካን ይሰናበታሉ፡፡

እንደማቋርጥ አውቄ ነው ወደ ውድድሩ የገባኹትኀይሌ ገብረሥላሴ

በሰይፉ ፋንታሁን ተዘጋጅቶ የሚቀርበው “ታዲያስ አዲስ” ባለፈው ቅዳሜ ኀይሌ ገብረሥላሴን ሸገር ኤፍ ኤም ስቱዲዮ ጋብዞ ከአቅራቢዎቹ  እና ከአድማጮች ጥያቄዎች እንዲቀበል አድርጎ ነበር። ዕንቁ መጽሔት ጥያቄ እና መልሱ “ለማስታወሻ እና ለታሪክ ይሰፍር ዘንድ” በሚል ምክንያት ጥያቄ እና መልሱን አትሞታል።

ጠያቂው እንዴት ኀይሌ ጋዜጠኞች ፊት ሩጫን ለማቋረጥ እንደወሰነ ጥያቄ አቅርቦለት ነበር።  ኀይሌ ሲመልስ ፦

“እንደማቋርጥ አውቄ ነው ወደ ውድድሩ የገባኹት። ያን ያህል ኪሎ ሜትር መሄዴም ለራሴ ገርሞኛል። ወደ ፊኒሺንግ መሄድ አለብህ አሉኝ። እኔም መሄድ እፈልጋለሁ። ግን እዚያ ምንድን ነው የማደርገው?…ስለዚህ ወደ ፕሬስ ኮንፈረስ ግባ አሉኝ፤ ገባሁ። ጋዜጠኞች ሞልተዋል። አሁን ሰበብ አለቀ። የትኛውን ሰበብ እሰጣለሁ? ድንግጥ ነው ያልኩት። በፊት አመመኝ ብዬ ወጣሁ፤ አሁን ደግሞ አይ ከእንግዲህ ሩጫ ማቆም ነው የምፈልገው አልኩ። እኔ ብዙ ጊዜ እንደሚታወቀው መሳቅ ነበር የምችለው። ያን ዕለት ግን ምን እንደኾነ አላውቅም፤ አለቀስኩ።

“አቆማለሁ” ብለህ ከአንደበትህ ቃሉ ሲወጣ እንባህ ቀደመህ ማለት ነው? ጠያቂው ቀጠለ

“አዎ ያስፈራል። ከሦስት ቀን በፊት ተዘጋጅቻለኹ፣ ላሸንፍ ነው ብለህ በሦስተኛው ቀን ምን መጣ? ምንድነውስ ትላለህ?

ጠያቂው ኀይሌን አልለቀቀውም። በነገር ጎንተል የሚያደርግ ጥያቄ አስከተለ።

ስለዚህ ያለው አማራጭ ማልቀስ ነበር?

ማልቀስ አይደለም፤ አማራጩ ያንን ውሳኔ ማስተላለፍ ነው።

አቆምኩ ካልክ በኋላስ ያለው የጋዜጠኞች ጥያቄ እንዴት ነው…? አንድ የውጭ ጋዜጠኛ “የፖለቲካ ተጽዕኖ ነው…” ብሏል?

ይህ የሰውየው ፍላጎት መሰለኝ። ቢኾን እና ቢጽፍ ኖሮ 999 ሰዎች ያልጻፉትን አንዱ ከየት አመጣው? ሌሎቹ ለምን አልጻፉም? የእኔ ኤጀንት እንዴት ለ999ኙ አልነገራቸውም?…

የኀይሌ  ጠያቂዎች ግላዊ ጥያቄዎችን አንስተውለት ነበር።

በውሳኔው ዕለት የልጆችህ እና የባለቤትህ ኹኔታ ምን ይመስል ነበር?

በሁለት ተከፈሉብኝ። አንደኛዋ ልጄ በጣም ተናዳ መጣች። ጓደኞቿ “አባትሽ አርጅቷል” አሏት። አንዷ ደግሞ “ማቆም የለብህም” ስትለኝ፣ ትልቋ ልጄ ደግሞ “እንደፍላጎቱ ነው ማድረግ ያለበት” አለች። ባለቤቴ ብዙ ነገር ለማግባባት ጣልቃ ገብታ ነበር። አንደኛ የእኔን ውሳኔ ኹሌ ትቀበላለች። የሕዝብን ግፊት እና ስሜትም ታያለች። እሷም ወደፊት ሯጭ መኾኗ አይቀርም።

ቲቪ ሾው ለመጀመር ሐሳቡ አለህ?

አዎ፤ ግን ምን ልጀምር? ሁሉም የሚከታተለውን አንድ ነገር እጀምራለሁ። እንደ “ገመና” ሁሉም ሊያየው የሚችል ዐይነት ማለቴ ነው። (“ገመናበኢትዮጵያ ቴሌቬዥን 52 ሳምንታት በሁለት ሲዝን ተከፍሎ የታየ ተከታታይ ድራማ ነው።)

25 ዓመታት የኢቲቪታላቅ ፊልምአቅራቢ

መዓዛ ዘውዴ ትባላለች፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት በኢቲቪ ውስጥ ታላቅ ፊልም አቅራቢ ናት፡፡ ከውጭ የፊልም ካምፓኒዎች ፊልም ትገዛለች፣ ትደራደራለች፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እየቆራረጠችም ቢኾን ታቀርበዋለች፡፡ አድማስ ከዚህች ሴት ጋራ ጉደኛ ቃለ መጠይቅ አስነብቧል፡፡

መዓዛ ፊልም በምትመርጥበት ወቅት በደርግ ጊዜ አይዲዮሎጂ ያስቸግራት እንደነበረ አሁን ደግሞ ልማታዊ ፊልም ዉለጂ እንደምትባል ትናገራለች፡፡

“ኢሕአዴግ እንደገባ ‘ሰሮጌት ማዘር’ የሚባል ፊልም አስተላለፍኩ፡፡ በፊልሙ ውስጥ የአንድ ጭሰኛ ልጅ ታረግዛለች፡፡ ፊልሙ ላይ ክብረ ንጽሕናዋ ሲወሰድ የሚያሳይ ክፍል ተላልፏል፡፡ ተመልካች ይደገም አለ፡፡ አለቆቼ ተቆጡ፡፡ ያኔ የመምሪያ ሐላፊ የነበሩት አቶ አማረ አረጋዊ (የቀድሞው የሕወሓት ታጋይ እና የአሁኑ የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት ናቸው)ለምን አስተላለፍሽ ብለው አፋጠጡኝ፡፡ ከጃፓኖች የበለጠ ወግ አጥባቂ አይደለንም ብዬ መልሼ ሳፈጥባቸው ዝም አሉኝ፡፡” ትላለች መዓዛ፡፡

የአስቴር አወቀ አዲስ ካሴት እየተጫረተ ነው

እንቁ መጽሔት አንደዘገበው የአስቴር አዲሱ ካሴት ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ እየተጫረተ ነው፡፡ ኤልያስ መልካ እና ጓደኞቹ ያቋቋሙት “በገና አሳታሚ” ለአስቴር አዲሱ ሥራ 1.3 ሚሊዮን ብር ያቀረበ ሲኾን ዝነኛው ኤሌክትራ ደግሞ 1.4 ሚሊዮን አቅርቦ እየተደራደረ ነው፡፡

የኤሊያስ መልካ “በገና አሳታሚ” ከማሳተም በተጨማሪ አልበሞች በአዟሪዎች እንዲቸረቸሩ ከማድረግ ይልቅ በሱፐረማርኬቶች እና ሕዝብ በስፋት በሚገበያይባቸው ስፍራዎች የመሸጥ ዕቅድ አለው። “በገና” ይህን አሠራር በአስቴር ሙዚቃ ለመጀመር እንዳሰበ መጽሔቱ ጽፏል።

የኢትዮፒካሊንክ ውስጥ አዋቂ ፕሮግራም ላልተወሰነ ጊዜ ታገደ- ኢትዮ ቻናል

በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ላይ በሚቀርበው የኢትዮፒካሊንክ የመዝናኛ ዝግጅት አንድ አካል የነበረውን እና ዘወትር ቅዳሜ ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ይደመጥ የነበረው የ“ውስጥ አዋቂ” ፕሮግራም ከሕዳር 18 ጀምሮ መቋረጡን ኢትዮ ቻናል ዘግቧል። ፕሮግራሙ የተቋረጠው ፋና ኤፍ ኤም  የ“ውስጥ አዋቂ” አዘጋጅ በኾነው ግዛቸው እሸቱ ላይ ዕገዳ በመጣሉ ነው።

ለዕገዳው መንስዔ የኾነው በጣቢያው የፕሮግራሞች መምሪያ ሐላፊ የኾነው ብሩክ ከበደ የአንድ ድምፃዊን የዘፈን ሲዲ እንዲያጫውት ለግዛቸው ሲሰጠው ግዛቸው አልቀበልም በማለቱ ነው። ግዛቸው “እንዲህ ዐይነት አሠራር የለንም። ቀድመን ያዘጋጀነው ፕሮግራም አለ” የሚል ምክንያት ቢሰጥም ከመምሪያ ሐላፊው በኩል ስድብ የተቀላቀለበት ምላሽ መሰጠቱን እና ጭቅጭቅ መፈጠሩን ጋዜጣው የጣቢያውን ምንጮች በመጥቀስ አስነብቧል። ጣቢያው ጉዳዩን አጣርቶ ግዛቸውን ጨምሮ በዕለቱ ተረኛ በነበሩ የጥበቃ ሠራተኞች እና የቴክኒሽያን ሐላፊ ላይ ቅጣት ጥሏል።

ሐምሳ ሜትር ርዝመት ያለው ኬክ ሐዋሳ ከተማ ላይ ተቆረሰ

ሐዋሳ 50ኛ ዓመቷን እያከበረች ነው፡፡ የከተማዋ መሥራች ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም፣ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ፣ኀይሌ ገብረሥላሴ እና ሌሎች ታላላቅ ባለሥልጣናት በጋራ የቆረሱት ኬክ 50 ሜትር ርዝመት አለው፡፡ 96ሺሕ ብር ተከስክሶበታል፡፡ “ኬኩ በረዥምነቱ ከአፍሪካ አንደኛ ነው” ብሏል-አዲስ አድማስ ጋዜጣ፡፡ 4500 እንቁላሎች፣ ሦስት ኩንታል ስኳር፣ 50 ኪሎ ክሬም እንደፈጀም ዘግቧል።

ቢጂአይ ኢትዮጵያ በቀን ሁለት ሚሊዮን ብር ግብር ይከፍላል

የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የካስትል አማራጭ የኾነው ቢጂአይ የወይን ፋብሪካ ግንባታ ሊጀምር ነው፡፡ ቢጂአይ ፋብሪካውን የሚገነባው በዝዋይ ከተማ ሲሆን 150 ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ በአዋሳ እያስገነባ ያለው ሦስተኛው ፋብሪካ አንድ ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የሚገመት ሲኾን ሐምሳ በመቶ ተጠናቋል፡፡ ድርጅቱ ከተለያዩ የታክስ ዐይነቶች በቀን ለመንግሥት ሁለት ሚሊዮን ብር ገደማ ገቢ ያደርጋል ሲሉ ቻናል እና አድማስ ጽፈዋል፡፡

የአገር ቤት ምርቃት

 • “በመገናኛ አደባባይ ባለ ሦስት ተደራራቢ መንገድ ሊሠራ ነው” ሪፖርተር
 • “መረጃ የሚከለክሉ ባለሥልጣናትን በሕግ እጠይቃለሁ” የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጋዜጠኞች ኅብረት
 • “የባለሥልጣናት የሀብት ምዝገባ የአቶ መለስን ሀብት እና ንብረት በመመዝገብ ይጀምራል” ሰንደቅ
 • “ኢዴፓ አዲስ አመራሮችን ሊመርጥ ነው” አድማስ
 • “አድባራት እና ገዳማት ዕዳ ይቀነስልን አሉ” አድማስ
Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

5 Responses to “የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ”

 1. ቴሌ ማጅመንቱን ለፈረንሳዩ ኦሬንጅ መስጠቱ የሚበረታታ ጅምር ነው፤ በዚህ አካሔድ የፌደራል አቃቤ ሕግም ማኔጅመንቱን ለኦሬንጅ እንደሚሰጥ ተስፋ አለን፡፡ ለፈረንሳዩ ኦሬንጅ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊቷ ኦሬንጅ፡፡ ይህ ማኔጅመንትን ለውጭ ድርጅቶች አሳልፎ የመስጠት አሰራር ግን ንዙም አይዋጥልኝም የምንኖረው በምኒልክ ዘመን አይደለም፡፡ አሁን ማን ይሙት ቴሌን ቀጥ አድርጎ መያዝ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ጠፍተው ነው? ለተበላሸ አመራር መፍትሔው ማኔጅመንትን ለውጪ ድርጅቶች መስጠት ከሆነ የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የመጀመሪያው መሆን ነበረበት፡፡ ለየትኛውም ብሔር የማያደላ ገለልተኛ የሆላንድ ማጅመንት… ኪ ኪ ኪ ኪ.

  ›ኢንጂነር ሐይሉን ቀሪ ሕይወትዎ የስኬት፤ በሐብት ላይ ሐብት የሚጨምሩበት፤ ላፍቶ ብለው አንድ እንዳሉ ሲኤምሲ፤ አየር ጤና፤ ኦልድ ኤየር ፖርት እያሉ ሲኒማ ቤቶችን እና ዘመናዊ ስፖርት ቤቶችን በማስፋፋት የልማት ድሎችን የሚያረጋግጡበት ይሁንልዎ በሉልኝ፡፡ ለአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ቆቤን በአክብሮት አንስቻለሁ፡፡

  ›ሐይሌን የምር አከብረዋለሁ! በዛ በበጋ የሚለውን መዝሙር ለልጆቹ ካስተማረ ደግሞ ይበልጥ አከብረዋለሁ! በድጋሚ ታዲያስ አዲስ ላይ ከቀረበ የቤተሰቡ ውዝግብ የተስተናገደው በአማርኛ ነበር ወይስ በእንግሊዘኛ የሚለውን ጥያቄ ቢመልስልን ደስ ይለናል፡፡

  ›መዓዛ ዘውዴ አሁንም በስራ ላይ ካለች “Прийти навестить” የተሰኘውን የሩሲያ ፊልም ከየትም ብላ ብታገኘው ለሚቀጥሉት 5 አመታት ፊልም ፍለጋ መንከራተቷ ያበቃል! የፊልሙ አርዕስት ወደ አማርኛ ሲመለስ “መጥታችሁ እዩ” እንደማለት ሲሆን በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልማቱን በብረቱ አይናቸው አይተው እንዲመሰክሩ የማድረግ ሃይል አለው፡፡ አቶ መለስም ይወዱታል፡፡

  ›ኢትዮፒካሊንክን በተመለከተ… በጣም የሚያስቅ ዜና ነበር፡፡ ለመሆኑ ድምፃዊው ማን ነበር? ዝም ብዬ ስገምት ወይ ሰለሞን ተካልኝ፤ አልያም… መጣ መጣ ሲሉኝ መንግስቱ ነው ብዬ… መጣ መጣ ሲሉኝ መላኩ ነው ብዬ ምናምን… እያለ የሚዘፍነው ሰውዬ (ስሙ ደምሳሽ ይመስለኛል)፤ ካልሆነ ደግሞ “ወዲ አፍሮ” ( “ብርኒሂጎ”) ይመስለኛል፡፡ መቼም ቴዲ አፍሮ ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡

  ›የአዋሳው ኬክ ግርማዊነታቸው 50 አመት የንግስ በዓላቸውን ለማክበር ከፈረንሳይ አስመጡት የሚባለውን ኬክ አስታውሶኛል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከኬክ ጋር ምን ያህል እንደተቆራኘ አያችሁ? አይገርምም? ኬክ! 50 ሜትር! አጀብ ነው. . .! የት ነበር የተጋገረው?

  ›የባለስልጣናቱን ሐብት የሚቆጥረውና የሚመዘግበው ዝነኛው ኮሚሽን (ፀረ ሙስና) ነው እንዳትሉኝና በሳቅ እንዳልፈነዳ፤ አስተያየት መስጠት የሚቻል ከሆነ ስራው የመብራትና የውሃ ቆጣሪዎችን ቤት ለቤት እየሄዱ ለሚያነቡት ባለሞያዎች ቢተው ጥሩ ይመስለኛል፡፡

  ›ኢዴፓ አመራሮችን ሊያስመርጥ ነው መለታቸው ነው? …አልገባኝም፡፡ ኢዴፓ አመራሮቹን ራሱ ነው እንዴ የሚመርጠው?

  ለማንኛውም አዲስ ነገርን እናመሰግናለን፡፡

 2. ከሶስት ቀን በፊት ተዘጋጅቻለሁ ላሸንፍ ነው ብለህ,,,,እና,,,,
  እንደማቋርጥ አውቄ ነው ወደ ውድድር የገባሁት ,,,ሀይሌ የትኛውን እንያዝለት?

 3. Girazmach you really are very funny. The last remark says it all. Indeed does EDP elect its leaders or is it done for them by the central committee of you know who.

 4. Hi GraZzmach
  well articulated comment
  keep it up!

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.