tessema-fifa-

እንዲደበዝዝ የተፈረደበት የይድነቃቸው ተሰማ ታሪክ

(ኤርሚያስ አማረ)

“የአባቴ መልካም ታሪኮች ብዙ ናቸው፤ ቢያንስ ጥቂቶቹ ሊነገሩለት እና በትክክለኛው መንገድ ሊቀርቡለት በተገባ …” ይህን ያሉት የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸው ናቸው። በደቡብ አፍሪካ የተዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ ምክንያት አድርጎ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋዜጠኛው እስክንድር ፍሬው ካቀረበላቸው ጥያቄዎች መካካል ለአንዱ ከሰጡት መልስ ላይ የተወሰደ ነው።

ይድነቃቸው ተሰማ ፎቶ ምንጭ http://pitchinvasion.net

መልካም ታሪካቸው ቢያንስ ሊነገርላቸው ይገባል የሚባልላቸው ታላቅ የእግር ኳስ ሰው ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ በሕይወት የሉም። ከ23 ዓመት በፊት ነሐሴ 14 ቀን 1979 ዓ.ም አልፈዋል። የተከሉት ስም ግን አላለፈም፤ አልሞተም። ስለ ኢትዮጵያ ኾነ ስለ አፍሪካ እግር ኳስ በተነሳ ቁጥር ይድኔ በዚያ አሉ። አስታዋሻቸውም ኾነ ዘካሪያቸው ብዙ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በቅርቡ ባሳተሙት “አገቱኒ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ክቡርነታቸውን ከስፖርትም ባሻገር የሽምግልና ካባ የተደረበላቸው ሲሉ ይገልጹዋቸዋል። በዚያው የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ “እርቅ እና ሽምግልና” በተሰኘው ክፍል አቶ ይድነቃቸው ዛሬ ውሉ ለጠፋበት እና ለጎደፈው ለኢት ጵያዊው የሽምግልና ባህል በሕይወት ባይኖሩም እንደሚመጥኑ ምስክርነት ተነግሮላቸዋል፤ ተጽፎላቸዋል። እውነት ነው፤ ይድነቃቸው ታላቅ ሰው ነበሩ። የስፖርት ብቻ ሳይኾን የነጻነት፣ የአንድነት፣ የፍትሕ እና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት መገለጫም ናቸው።

የኢትዮጵያን፣ የአፍሪቃን ከፍ ሲል ደግሞ የፕላኔቲቱን የእግር ኳስ ታሪክ ለመክተብ የሚዘጋጅ የትኛውም ብዕረኛ የይድነቃቸው ተሰማን በጎ ስም እና ሥራ ሳይጠቅስ ካለፈ ታሪኩ ግማሽ ሙሉ ይኾንበታል። እግር ኳስ በ1920ዎቹ በያኔዋ አዲስ አበባ መዘውተር ሲጀምር እነ ይድነቃቸው የተውኔቱ አንኳር ገጸ ባህርያት ነበሩ። በዝነኛው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ውስጥ በሚያስተምሩ የውጪ አገር ዜጎች አማካኝነት ከአዲስ አበባውያን ጋራ የተዋወቀው ተወዳጁ ስፖርት ቀስ በቀስ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ተሻግሮ በአቅራቢው ወደሚገኙ መንደሮች ዳዴ ማለት ጀመረ። በዚህ ጉዞው ላይ እያለ ከይድነቃቸው ጋር አራዳ ላይ ይገናኛል። መልካም እጅ ላይ የወደቀው እግር ኳስ ቀስ በቀስ በእነ ይድነቃቸው መሪነት ኢትዮጵያውያኑ እና ነጮቹ በአንድ መድረክ የሚፎካከሩበትን መንገድ እያበጀ መጣ። በአራዳ ልጆች ጆርጅ ዱካስ እና አየለ አትናሽ አስተባባሪነትም እንግሊዞችን፣ ግሪኮችን፣ ጣልያኖችን እና አርመኖችን ለመፎካከር የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ታኅሣሥ 28 ቀን 1928 ዓ.ም ተመሠረተ።

ከምሥረታው ከሁለት ወራት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀሉት ይድነቃቸው በአዲስ አበባ እግር ኳስ ዙሪያ ያላቸው ተሳትፎ እየተጠናከረ መጣ። ትኩረታቸው እንደ ልጃቸው በሚቆጥሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ያነጣጠረ ቢኾንም፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጣልያን ወረራ በኋላ በይፋ ሲመሠረት ይድኔ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በጦርነቱ ዘመን መጠሪያውን ወደ ሊቶሪዮ ውቤ ሰፈር አራዳ ለመቀየር ሲገደድ ይድነቃቸው እና ጓደኞቻቸው ለቡድኑ የነበራቸው ፍቅር አልቀነሰም፤ ጭራሽ እየጋለ መጣ እንጂ። ከድል በኋላ ቡድኑ መጠነኛ የአደረጃጀት ለውጥ ይዞ ብቅ ሲል ይድነቃቸው የማልያ ቀለም በመምረጥ እና እስከዛሬ ድረስ መዝለቅ የቻለውን የቡድኑን የ”ቪ” ዓርማ ጽንሰ ሐሳብ ከፈረንሳይ ክለቦች በመዋስ ሳን ጆርጅ በተሻሻለ ጎዳና እንዲራመድ ትልቁን በር ከፍተውለታል።

የፉክክሩ ጥንስስ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በአምስቱ የጣልያን ወረራ ዓመታት በውጪ አገር የኮሚዩኒቲ ቡድኖች ላይ ባስመዘገበው ድል የተነሳ በእንጦጦ፣ ስድስት ኪሎ እና ቀበና ሰፈሮች መሰል እና አገርኛ ቃና ያላቸው ቡድኖች እንዲቋቋሙ ፋና ወጊ ኾነ። ኾኖም ጠላት ድል ከተደረገ በኋላ አብዛኞቹ የስድስት ኪሎ እና እና የእንጦጦ ወጣቶች ወደ ጦር ሠራዊት በመግባታቸው ቡድኖቹ ፈራረሱ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን አመራሩን ለጆርጅ ዱካስ እና ለይድነቃቸው ተሰማ በመስጠት ይበልጥ ተጠናከረ። በታኅሳስ ወር መጨረሻ 1928 ዓ.ም የተቋቋመው አንጋፋው ቡድን ከምሥረታው ጀምሮ ባሉት ዐሥራ ሁለት ዓመታት አመራር ሲቀበል የኖረው ከተጫዋቾቹ ነበር። ሥራ አስኪያጅ፣ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና ፀሐፊ የሚባል ነገር በጊዮርጊሶች ዘንድ አይታወቅም። በ1940 ዓ.ም ግን ሳን ጆርጅ በተጫዋቾች መተዳደሩን አቁሞ በአዳዲስ አመራሮች መመራትን አሀዱ አለ። አቶ ገብረሥላሴ ኦዳ (የአቶ ገ/መስቀል ኦዳ ወንድም እና የአቶ አብነት ገ/መስቀል አጎት ናቸው) የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ኾነው ተሾሙ። በምክትል ፕሬዚዳንትነት አቶ ተፈሪ ሻረው እና አቶ ጌታሁን አየለ ሲሰየሙ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የዋና ፀሐፊነቱን ቦታ ተረከቡ። ይድነቃቸው ከዋና ፀሐፊነታቸው ባሻገር በአሠልጣኝነት እና በተጫዋችነት ያገለግሉ ነበር።

አቶ ገብረሥላሴ ኦዳ በፕሬዝዳንትነት ቢሾሙም የቅዱስ ጊዮርጊስ እስትፋንስ ግን ይድነቃቸው ነበሩ ማለት ይቀላል። ተጫዋች ይመለምላሉ፤ አሠልጣኝ ያማክራሉ፤ ራሳቸውም ያሠለጥናሉ፤ ቡድኑ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኝበትን መንገድ ይፈልጋሉ፤ ጠንከር ያሉ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችንም በግላቸው ያሳልፋሉ። በዘመኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከይድነቃቸው፤ ይድነቃቸውን ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥሎ ማስቀመጥ ፈጽሞ የሚከብድ ነበር። የአንጋፋውን ክለብ ውስጠ ምስጢር ጠንቅቀው የሚያውቁ ግለሰቦችም በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና በአቶ ገብረሥላሴ ኦዳ ወገኖች መካከል ለዓመታት የዘለቀው የፉክክር ስሜት የተጠነሰሰው ያኔ መኾኑን አስምረው ያስረዳሉ።

የአሁኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገ/መስቀልም ይህን የፉክክር መሥመር በመከተል ዛሬ የይድነቃቸው ታሪክ ከአጎታቸው በላቀ መነገሩ ስለሚያማቸው በይድነቃቸው ዝና ላይ ውኃ የመቸለስ ሥራ የሚሠሩ ናቸው። አቶ አብነት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሐላፊነት በ1993 ዓ.ም ከመጡ በኋላ በሸራተን አዲስ ከወዳጆቻቸው ጋራ በሚያከናውኗቸው ኢ-ወጋዊ የምሽት ውይይቶች ይህንኑ ስሜት የሚያንፀባርቅ እና የሚያጠናክር አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ የነበሩ ባለሞያ (ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል) ተመሳሳይ አስተያየቶች ከአቶ አብነት አንደበት ሲወጡ እንዳደመጡ መስክረዋል፤ “አቶ ይድነቃቸው የአጎቴን ታሪክ አላግባብ ተሻምቷል” ሲሉ ።

ዘመነ አብነት

በ1980ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን በአንድ ትልቅ የመወያያ አጀንዳ ተወጥሮ የሰነበተበት ጊዜ ነው። በበላይነት ከሚያስተዳድረው የቢራ ፋብሪካ ጥላ ወጥቶ ራሱን ይቻል ወይስ በፋብሪካው ሥር ቀጥሎ በኮሚቴ ይመራ በሚሉት ሁለት ጽንፎች ደጋፊው ሲያወዛግብ ከርሟል። ክለቡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ሥር በኮሚቴ ሲተዳደር ከፍተኛ አመራር ከነበሩት መካከል አቶ ገዛኸኝ አመጠ አንዱ ነበሩ። አቶ ገዛኸኝ በአንድ ወቅት የጊዜውን ኹኔታ ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል፦ “የእግር ኳስ ክለቡ የሚተዳደረው ከድራፍት በርሜል በፐርሰንት በሚሰበሰብ መጠነኛ ገንዘብ ነው። ቀደም ሲል የሚሰበሰበው ገንዘብ ለተጫዋቾች ደመወዝ እና ቦነስ፣ ለምግብ፣ ለሆቴል እና ለልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ወጪዎች ይብቃቃ ነበር። እንደ ቡና ገበያ ያሉ ተፎካካሪ ክለቦች ለተጫዋቾች ፊርማ እየከፈሉ ሲመጡ ግን ከድራፍት የሚሰበሰበው ገንዘብ የእኛን ተጫዋቾችም ኾነ አዲስ ለማስመጣት ያሰብናቸውን የሚያማልል ሊኾን አልቻለም። ጭራሽ አዲስ ትጥቅ መቀየር ሁሉ ተሳነን። በአንድ ወቅት ሙሉጌታ ከበደ እና ገ/መድኅን ኀይሌ የተቀደደ ማልያ ሰፍተው ወደ ሜዳ መግባታቸውን ሁሉ አውቃለሁ። እነዚህ ኹኔታዎች የግዴታ ክለቡ ከፋብሪካው ሥር መውጣት እንዳለበት አሳሰቡን። በዚህም የአቶ አብነት ገ/መስቀል ወደ ክለቡ መምጣት መልካም አጋጣሚ ፈጠረልን። አደጋ ላይ የነበረው ቡድናችን አንገብጋቢ ከነበረው የፋይናንስ ቀውስ ተላቀቀ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አቶ ገዛኸኝ ሽግግሩን በዚህ መልክ ቢያስቀምጡትም ጥቂት የማይባሉ ዕውቅ የቡድኑ ደጋፊዎች ግን “ቅዱስ ጊዮርጊስ አምባገነናዊ እና ለግል ጥቅማቸው ባደሩ ግለሰቦች እጅ ውስጥ የወደቀበት ውሳኔ” ሲሉ የአቶ አብነትን ሹመት እና  ካቢኔ በበጎ አያነሱትም። በብሔራዊ ቴአትር በ1993 ዓ.ም የተደረገው የባለቤትነት ሽግግር ቅዱስ ጊዮርጊስን “ራሱን የቻለ” የስፖርት ማኅበር ቢያስብለውም በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ግን በቢራ ፋብሪካ ሥር በኮሚቴ ሲመራ ከነበረበት ዘመን ባልተሻለ አስተዳደራዊ የዝቅጠት ዘመንን እንዳሳለፈ ያሳላፋቸው ክስተቶች እና ስንክ ሳሮች ምስክርነት ኾነው ይቀርባሉ።

ከስቴዲየም ግንባታ አንስቶ ክለቡን በሁለት እግሩ እስከሚያቆሙት የፋይናንስ እና የገበያ ማስፋፊያ ሥራዎች ድረስ ያሉት ዐበይት ክንውኖች በዐሥር ዓመታት ውስጥ “ከውዝፍ ፋይልነት” ነቅነቅ ማላት አለመቻላቸው በቀዳሚነት ለትችት ከሚያጋልጡት ውስጥ ይመደባሉ። ደብረዘይት ላይ ይገነባል ተብሎ ብዙም ያልተራመደው የሕፃናት ማሠልጠኛ አካዳሚ ጉዳይም ሌላው በአቶ አብነት አስተዳደር ላይ የሚነሳ አንድ ድክመት ነው። በይበልጥ ደግሞ ክለቡን በመውደድ እና በማፍቀር ስም ከሼሑ የሚፈሰውን ንዋይ ለግል ጥቅማቸው ማበልጸጊያ የተጠቀሙ እና የሚጠቀሙ ግለሰቦች መበራከታቸው ሌላው የአቶ አብነት እና የካቢኔያቸው ጥቁር ነጥብ ኾኗል። በወቅቱ አመራር ዙሪያ የተዘረዘሩት አሉታዊ ነጥቦች በየአቅጣጫው ቢበረክቱም ቡድኑ በሜዳ ላይ ባለው ውጤታማነት ዘመነ-አብነት ገደኛ ዘመን ነው ብለው የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። “ይድነቃቸው በአጎታቸው ላይ የወሰዱትን የበላይነት ለመቀናቀን አብነት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፤ በተለይ ደግሞ ከውጤት ጋራ በተያያዘ። በየትኛውም መንገድ ዋንጫ ወደ ቢጫማዎቹ ካዝና ቢመጣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፕሬዝዳንት ፍፁም ደስተኛ ናቸው” ይላሉ ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ ከአቶ አብነት ጋራ የቅርብ ግንኙነት ፈጠሩ አንድ ሰው።

ጣጣው ለይድኔም ተርፏል

ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ዕድሜው ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ ታሪካዊ ቡድን ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብቻ ሳይኾን ለነጻነት በተደረገው ትግል እንደ ምልክት የሚወሰድ ክለብም ነው። በእነዚህ የከፍታ እና የዝቅታ ዓመታት ስሙን ከአንዴም ሁለቴ ለመቀየር ተገዷል። የአድሃሪያን አፍቃሪ በሚል ደርግ እንዲፈርስ ፈርዶበታል። ነፍጠኛውን የሚወክል ተብሎ በዘመነ ኢሕአዴግ ግልጽ የአስተዳደር  በደል አድርሶበታል። የቅዱስ ጊዮርጊስን ድንቅ ታሪክ ያለው ወይም የነጻነት ምልክት መኾኑን የማይቀበሉ አሊያም ለመሻር የሚሞክሩ ቡድኖች እና መንግሥታት የይድነቃቸው ተሰማንም ታሪክ እየደፈጠጡ የራሳቸውን ለመጻፍ ሞክረዋል፤ እየደፈጥጡትም ናቸው። ይድነቃቸው በሕይወት ሳሉ አጥብቀው የሚያራምዱት የኢትዮጵያ አንድነት መርኅ በጊዜው በትግል ላይ ከነበሩ ነጻ አውጪዎች ሳይቀር የቀዘቀዘ ትከሻ እንዲሰጣቸው ምክንያት ኾኗል። ዛሬ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት አመራር ላይ ያሉ ቱባ ባለሥልጣናትም ይህን ቀዳዳ ተጠቅመው አንድም የግል ፉክክራቸውን፤ አሊያም የገዢው ቡድን አጋርነታቸውን ለማሳየት የይድኔን ድንቅ ታሪክ እንዳልነበር ወደ መቁጠር ደርሰው ገሸሽ አድርገውታል። “ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም” እንዲል!!

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email