ivans cafe

ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ! [ክፍል ሦስት]

መሐመድ ሰልማን

ይህንን ጽሑፍ ስንጀምር እንደብዙዎቹ የጂኦግራፊ ትምህርቶች በ“ዴፊኒሽን” ስላልጀመርኩልህ ይቅርታ እጠይቅኻለሁ፡፡ ፒያሳ የሚለው ቃል የመጣው ከአውሮፓ አህጉር፣ ከጣልያን አገር ሮም ከሚባል ሰፈር ሲሆን ትርጉሙም ‹‹አደባባይ›› ወይም ‹‹ማእከል›› እንደማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በአገራችን የትግርኛ ተናጋሪዎች ዘንድም እንደሚታወቅ ስነግርህ በታላቅ ኩራት ነው፡፡ ለምሳሌ ደርባባ ትግሪያዊ እናት ቆንጆ ልጃቸውን ‹‹ጓለይ ማዕረይ   ብፒያሳ አይትኺዲ›› ብለው ቢቆጡ ‹‹ልጄ ማሬ በአስፋልት አትሂጂ›› ለማለት ፈልገው እንደሆነ ትረዳለህ፡፡ ስለሆነም ከእኛው ትግርኛና ከ‹‹ጥልያን›› ባዕድ ቋንቋ ያገኘናቸውን ትርጉሞች በማዳበል ‹‹ፒያሳ›› የሚለው ስርወ ቃል ተፈጠረ፡፡ ትርጉሙን ስንፈታው ደግሞ የሚከተለውን ማለት ሊሆን ይችላል፤ ፒያሳ፤ የቆነጃጅት ማዕከል፣የውቦች አደባባይ፣ ዉበት የሚንዠቀዠቅበት፣ በየአስፋልቱ…በየካፌው!!!

Ivans cafe

እንግሊዝኛ፣ ጣልያንኛና ህልም እንደፈቺው ነው ይላሉ በጣልያን ጊዜ አርበኛ የነበሩ አበው ሲተርቱ፡፡ እውነት ብለዋል፡፡ ፒያሳ የቆነጃጅት ማርና ወተት ናት፡፡ ካላመንክ ታሪክ አገላብጥ፤ መጻሕፍት ግለጥ፤ አንብብ፤ ጠይቅ። ‹‹እሳት ወይ አበባ››ን አንብበኸዋል? የዛሬ ወጣቶች ከ‹‹ዴርቶጋዳ›› ውጭ መቼ መጽሐፍ ታነባላችሁ? ለማንኛውም ‹‹ዴርቶጋዳ›› ውስጥ ስሙ የተጠቀሰ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ አለ፡፡ ስሙም ጸጋዬ ገብረመድኅን ይባላል፡፡ ነፍሱን ይማር፡፡ ከግብሮቹ አንዱ ፍጽም ኢትዮጵያዊ ቅኔዎችን መዝረፍ ነበር፡፡ ‹‹እሳት ወይ አበባ›› አንዱ ቅኔ የዘረፈበት ማሳ ነው፡፡ የሚገርምህ ይህን ድንቅ መጽሐፍ 105ኛ ገጽ ላይ ብትገልጠው ይህን ቅኔ ታነባለህ፡፡ ለፒያሳ የተዘረፈ ቅኔ፡፡

እግር እንይ

አርቀን ማስተዋል ማለት፤ የኛን ስልጣኔ ድልድይ፤

እግር ማየት ነው ብለዋል፤ እስቲ እንግዲህ እግር እንይ፤

ያባቶችህ ያይን ድንበር ከተረከዝ ሎሚ ሳያልፍ፤

አንተ ግን ጆቢራው- ዘራፍ፤

ጠረፍ አይወስንህ ጉብል፤

ጥሎህ በዘመንህ እድል፤

ዓይንህ ባት አልፎ እንዲዋልል፤

ቴይ ወዲያ ጀግንነት የለ፤ ተዚህ የከረረ ግዳጅ፤

ባደባባይ የዱር ገደል፤ስትናደፍ የእግር አዋጅ፤

ሌሊቱን በየሌት‹‹ግለብ››፤ቀኑን ጭምር በጠራራ፤

ሊነጋ እንደ ጧት ጆቢራ፤

በከተማው ስታቅራራ፤

በእድሜህ መንከራተት ስራ፤

—  —

እስቲ ደሞ አራዳ ወጥተህ በከተማው አደባባይ፤

ያንዷን ካንዷ ዳሌና ባት፤ እግሯን ከእግር ጋር አስተያይ፤

ደርቶልህ ያገር ልጅ ቅልጥም፤

ዳሌው ባቷ እስኪፈረጥም፤

እያናረ እስኪያገመግም፤

አንተ አድፍጠህ ከኃሏዋ በአይንህ ሳግ ስታነፈንፍ፤

ያችን ልክፍ፤ ያቺን ንድፍ፤

—  —

አርቀን ማስተዋል ማለት፤የኛን ስልጣኔ ድልድይ፤

እግር ማየት ነው ብለናል፤ አሜን በቃን እግር እንይ፡፡

ፀጋዬ ገ/መድኅን

ፒያሳ (1983)

አንተ አገርህ በሁለቱም ቅዱሳን መጽሕፍት መጠቀሷ ልዩ ኩራት እንደሚሰጥህ ሁሉ እኛ የፒያሳ ልጆችም በጸጋዬ ገብረመድኅን ሥራ መካተታችን ያኮራናል፡፡ ‹‹ቦሌ›› የሚለውን ቃል በሰላምታ መጽሔት እንጂ በየትኛውም ቅዱሳን መጻሕፍት አታገኘውም፡፡ ‹‹ጨርቆስ›› የሚለውን ስም በተጨቆኑ ቀልዶች ሲዲ ውስጥ እንጂ የትም አታገኘውም፡፡ ፒያሳን ግን በታላቁ ባለቅኔ ጸጋዬ ገ/መድህን መጽሕፍት እንደልብህ ታገኘዋለህ፡፡

ለማንኛውም ከላይ በቀረበልህ ግጥም በመመስረት የሚከተሉትን ከምንባቡ የወጡ ጥያቄዎችን መልስ፡፡

  1. ግጥሙ ደራሲው የት ቁጭ ብሎ የጻፈው ይመስልኻል?

ሀ. ጨርቆስ  ለ.ፒያሳ  ሐ. ቦሌ ድልድይ  መ. አሲምባ

  1. ከግጥሙ መንፈስ በመነሳት የ‹‹ቁንጅና ማርና ወተት የሚፈስባት ሰፈር›› የተባለችው?

ሀ. ላም በረት   ለ. ፒያሳ   ሐ. ካራቆሬ  መ. መልሱን ጸጋዬም ቢሆን አያውቀውም

ወደዛሬው የፒያሳ ጫወታ ልመልስህ! ፡፡

ፒያሳን ከሌሎች እህት ሰፈሮች ልዩ የሚያደርጋት ለላይኛውም፣ ለታችኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የምትመጥን በመሆኗ ነው፡፡ በቀላሉ እንዲገባህ ወጣት ምሳሌ ልስጥህ፡፡  አይበለውና ወንድነትህ አስቸገረህና እንደኔ በጨዋ መንገድ እንደ ጨው የምትጣፍጥ ፍቅረኛህን ‹‹ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ›› ብለህ፣ ኬክ ጋብዘህ፣ በጁስ ተለማምጠህ፣ በክትፎ ተለማምነህ ከንፈር ላይ ቂብ ማለት የማትችል ከሆነ፣ አልያም ደግሞ የሴት ቢሮክራሲ ከሰፈርህ ቀበሌ ጋር የሚመሳሰልብህ ከሆነ፣ ፒያሳ መፍትሄ አላት፡፡ እስኪመሽ መታገስ ከቻልክና ኪስህ ድፍን ብሮችን ካቆረ እነ ‹‹ባካል ፀ›› እነ ‹‹ብሉናይል››፣እነ ‹‹ጊቤ›› እነ ‹‹ቼ ጉቬራ›› ይተባበሩኻል፡፡ እስኪመሽ መታገስ ካልቻልክ ደግሞ ‹‹ገሊላ›› የሚባል ቤት አለልህ፡፡ ‹‹ገሊላ›› ቢራ ሳይሆን ማክያቶ አዘህ ከአስተናጋጆቹ ጋር ለ‹‹አጭሬ›› የምትደራደርበት ቤት ነው፡፡ ስለዚህ እና ሌሎች አራት ተመሳሳይ ድብቅ አገልግሎት ስለሚሰጡ እህት ኩባንያዎች በቅርቡ አጫውትህ ይሆናል፡፡

በነገርህ ላይ ‹‹ቼ ኩቬራ›› ለፒያሳ አዲስ ገብ ነው፡፡ ገና ከመምጣቱ የጎረምሶች ቡጢ ቤት ሆኗልኸል፡፡ ይሄ ቤት በጨርቆስ ክፍለከተማ ቢከፈት ይሻል ነበር፡፡ የፒያሳ ልጅ ይመታሃል እንጂ አይደባደብህም፡፡

ዋጋ ከተወደደብህ ደግሞ ቀውጢ ሰፈር ልጠቁምህ፡፡ ከትግራይ ሆቴል እስከ ጣይቱ ሆቴል ያለውን መንገድ ታውቀዋለህ? ይህ አጭር ጎዳና የያዘውን ረዥም ጉድ በዝርዝር ለመግለፅ እንደ መስቀል አደባባይ ሰፊ ብራና ቢገኝም የሚሞከር አይደለም፡፡ በያዘው የሴት አዳሪዎች ብዛት ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ሳይሆን አይቀርም፣ከአዲሳባ ግን ከቺቺኒያ ቀጥሎ ሁለተኛ እንደሆነ ስነግርህ ያለጥርጥር ነው፡፡ በዚህ ሰፈር ንጉሳቸውን እንደሚጠብቁ ሚኒስትሮች የመንገዱን ግራና ቀኝ ተሰልፈው የሚቆሙ ልጅ-እግር ኮማሪቶች በየእለቱ ይወለዳሉ፡፡

ደግሞም በየምሽቱ ቁጥራቸው ይጨምራል፡፡ ከየት ነው የሚፈልቁት ልትል ትችላለህ፡፡ ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው፡፡ ሴቶቹ ‹‹አራት ኪሎ››ን፣‹‹አውቶብስ ተራ››ን፣‹‹ጣልያን ሰፈር››ን ከመሰሉ የጎረቤት ቀዬዎች ወደ ፒያሳ ይፈልሳሉ፡፡ ከነዚህ ጎረቤት ሰፈሮች አታለው የሚያመጧቸው ደግሞ እሳት የላሱ የፒያሳ ደላሎች ናቸው፡፡ እንዲህ ይሏቸዋል፤ ‹‹ፒያሳ የሚባል አገር አለ፡፤ ወርቅ  የሚታፈስበት፤ ባለፀጋ የሚኮንበት፣ፓስፖርት አውጪና ወደ ፒያሳ ልውሰድሽ ለቤተሰቦችሽ ዶላር ትልኪያለሽ፡፡››

ከየሰፈሩ በዚህ መልኩ በደላሎች ለስደት የተዳረጉ ትኩስ ኃይሎች ጣይቱ አካባቢን የስደት መጠለያቸው ያደርጓታል፡፡ ሰራተኛ ሰፈርና ዶሮ ማነቅያ  ባሉ ቆጥ ቤቶች አዳራቸውን ያደርጋሉ፡፡

አሁን አሁን እነዚህ የፒያሳ የጎዳና ኮማሪቶች መቆምያ ቦታ እያጡ ስለሆነ ተራ በተራ መተዛዘል ጀምረዋል፡፡ የፒያሳ ክፍለ ከተማ ለነዚህ የጎዳና ኮማሪቶች ወይ ኮንዶሚንየም ቤት ወይ ሴንሴሽን ኮንዶም ወይ መቆምያ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

ፒያሳን በቅርቡ በምሽት አይተኻት ከሆነ ‹‹ሰንሻይን ባር››፣ ‹‹ገብረትንሳይ ኬክ ቤት››፣ ‹‹መብራት ኃይል ህንፃ››፣ ‹‹ሲኒማ ኢትዮጵያ ደጅ››፣ ‹‹ማህሙድ ጋ››፣ ማህሙድ ቁልቁለቱን፣ ‹‹አራዳ አቀበቱን፣ አላሙዲን አጥሩን ሁሉም ደጆቻቸው በኮልኮሌዎች ተሞልተዋል፡፡ ደፈር ብለህ ከጠየቅክ ኮልኮሌዎቹ ‹‹አውትዶር ሰርቪስ›› ይሰጡኻል፡፡ እየመሸ ሲሄድ ደግሞ ይደፍሩኻል፡፡ ነብሱ፣ ባርዬ፣ባሪቾ፣ቀዮ እያሉ፡፡

በነገርህ ላይ አላሙዲን ላለፉት አስር አመታት ያጠረውን ‹‹የማዘጋጃ ሜዳ›› ሰሞኑን አምርሮ እየቆፈረው እንደሆነ አይቻለሁ፡፡ የቁፋሮዎን ጥልቀትና የወሰደውን ጊዜ በማየት የፒያሳ ጀዝቦች ‹‹ወርቁ ከአዶላ ሳይሆን ከፒያሳ ነው የሚወጣው›› እያሉ  ይቀልዳሉ አሉ፡፡ ይህ አላሙዲ ያጠረው ህንፃ ድሮ ወርቅ ወርቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ያፈራ ነበር አሉ፡፡ እነ መንግስቱ ወርቁን፤ እነ ወርቁ ኪዳኔን፤ እነ ወርቅነሽ ተስፉን (አራጋቢ ናት)፣ እነ ወርቅነህ ዘውዴን፤ እነ ወርቁ ድንቁን፤ እነ ፍቅሩ ኪዳኔን፡፡

የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሚገድለውም የሚያነሳውም አላሙዲን ነው የሚል ፒያሳዊ ፍልስፍና በቅርቡ ሰማሁ፡፡ እንዴት አልኩ፡፡ እንዲህ አሉኝ፤ እሳት የፒያሳ ልጆች፤

‹‹ሼኩ መጫወቻ ሜዳዎችን ለኢንቨስትመንት ይወስድና በምትኩ የውጭ አሰልጣኝ ይቀጥራል፡፡ከዚያ ቡድናችን ጥሩ ይጫወታል ግን የግብ እድል የለውም፡፡ ችግሩ ምንድነው ተብሎ ሲጠና ተጫዋቾቹ ጎል በሌለው ሜዳ ትሬይኒንግ እየሰሩ ነው ተባለ፡፡››

ሼክ አላሙዲ አሰልጣኙን ወስደው ሜዳውን ቢመልሱልን መልካም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ባንጫወትም የጎል እድል ይኖረን ነበር፡፡ሼኩ ቶሎ የፒያሳውን ህንፃ ገንብተው ጥሩ ጥሩ ዣንጥላ መሸጫ ሱቅ በመክፈት የስቴድየምን ህዝብ ይክሱታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምስኪን የስቴድየም ሕዝብ፡፡ አሁንም ጎል እየጠበቀ ይዘንብበታል!

ይኸው ስንት ስፖርተኛ ያፈራ የነበረው የፒያሳ ሜዳ አጥሩ ኮልኮሌዎችን አፈራ እልኸለሁ፡፡ ሆኖም ይህ ህንፃ ሲያልቅ ፒያሳ ምን መልክ ይኖራት ይሆን ስል አስባለሁ፡፡ ፈጣሪ ይህን ሳያሳየኝ እንዳይጠራኝ በርትቼ እጸልያለሁ፡፡

የጫወታችንን ውል አሲዘኝማ! ወደ ትግራይ ሆቴል አካባቢ እንመለስ፡፡

ከትግራይ ሆቴል እስከ ጣይቱ ባለው አካባቢው ያሉት ጥቃቅንና አነስተኛ መሸታ ቤቶች ቤት ያፈራቸውን፣ እድል የዞረባቸውን ቆነጃጅት በ‹‹ቴክ አወይ›› እንድትወስዳቸው ዋጋ ያደራድሩኻል፡፡

እነ ‹‹አቢሲኒያ›› በወጣት ላብ ያጥኑኻል፤ እነ ‹‹ኮንቲነንታል››ምራቅ የዋጡ፣ በስራቸው ዶክትሬት የጫኑ፣ ሰፊ የስራ ልምድ ያላቸው ወይዛዝርትን በግዢ ያቀርብልኻል፡፡ ሂድ ደግሞ ‹‹ናሽናል››፣ የአባትህ ታላላቆች ከሴት ጭን የሚወጣ እሳት ሲሞቁ ታገኛቸዋለህ፡፡ የሰፈርህን እድር በሊቀመንበርነት የሚመሩት ሰውዬ የሴት ዳሌ ቸብ ሲያደርጉ ባይንህ በብረቱ ትመለከታለህ፡፡ በነገታው የእድራችሁ ጡሩንባ ለምን በተደጋጋሚ እንደሚነፋ ይገባኻል፡፡

‹‹ትግራይ ሆቴል›› ድሮ ዝነኛ እንጂ ቆንጆ አልነበረም፡፡ እድሜ ለ‹‹አሸባሪዎች›› አሁን ቅልብጭ ያለ ህንፃ ሆኗል፡፡ ከምድር በታች አቀርቅረህ የምትገባበት ዘመናዊ ባር ተከፍቶበታል፡፡ ‹‹ጃምቦ ባር›› ይባላል፡፡ በዘናጭ ባለጌ ወንበሮች እየተሸከረከርክ፣ ዊስኪ ጠርሙሶች ከበው እያስካኩልህ እንደ ልዑል ትጠጣበታለህ፡፡ ከህንፃው አናት ደግሞ ‹‹ቶፕ ቪው›› ካፌ አለልህ፡፡ የፒያሳን አፈር የመሰሉ ጣርያዎች ቁልቁል እያየህ ‹‹አፈር ነኝና ወደ አፈር እመለሳለሁ›› እያልክ ተስፋ ትቆርጥበታለህ፡፡ ለማንኛውም የቀድሞው ትግራይ ሆቴል ከፈነዳ በኋላ እንዲህ አምሮበታል እልኻለሁ፡፡ ሆቴሉ ሰው ተስፋ ካለው ሞቶ መነሳት እንደሚችል የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው፡፡ አልዓዛር፡፡

በዚህ የጣይቱ ሰፈር ምን የሌለ ነገር አለ!

ጆሮህ ለሙዚቃ የሰለጠነ ከሆነ፣ በእንግሊዝኛ ማስነጠስ የሚቀናህ ከሆነ፣ የኮማሪቶች ከበርቻቻና ለከት የሌለው ሳቅ የሚያንገሸግሽህ ከሆነ፣ ማንም ባንተ ዛቢያ እንዲሽከረከር የማትሻ ከሆነ፣  ልምከርህ፡፡ ጣይቱ ሆቴልን ተደግፋ የቆመች ትንሽዬ ‹‹ፐብ›› አለች፡፡ ‹‹ፎክላንድ ፐብ›› ትባላለች፡፡ በሙዚቃ ብቻ ስሜትህን አርክተህ፣ ጣጣህን ጨርሰህ፣ የኮንዶም እንኳ ሳታወጣ ወደ ቤትህ ትመለሳለህ፡፡ ወደቤት መሄድ ካልፈለክም ‹‹ፎክላንድ ፐብ›› እስኪነጋ ትታገስኻለች፡፡ በሙዚቃ ፍቅር ያበዱ ዜጎችን ‹‹ሃንግኦቨር›› በሌለው ሙዚቃ የምታሰክር ቀሽት የፒያሳ ፐብ ናት፤ ፎክላንድ፡፡

የሚገርምህ ጣይቱ ሆቴልን ካጀቡት መንግስታዊ ያልሆኑ መጠጥ ቤቶች ሁልጊዜ ፀብና ግርግር አይጠፋም፡፡ ‹‹እከሌ እንትኑን የገደለው እኮ እዚህ ቤት ነው!›› ትባላለህ፡፡ እድለኛ ከሆንክ ብቻ ነው ከዚህ ቀውጢ ሰፈር ሳትፈነከት የምትወጣው፡፡ በነገርህ ላይ በጣም እድለኛ ከሆንክ ደግሞ በእርምጃ ርቀት ብሔራዊ ሎቶሪ አለልህ፡፡ ቦሌ አካባቢ ቶምቦላ ብታሸንፍ አዝዋሪው ብርህን ዋናው መስሪያ ቤት ሄደህ እንድትወስድ ነው የሚነግርህ፡፡ ፒያሳ ቶምቦላ ቢደርስህ ግን ብርህን እጅ በእጅ መውሰድ ትችላለህ፡፡ከዋናው መስሪያ ቤት፡፡ ጣይቱ ጎን፤ እስኪነጋ ጠብቀህ፡፡

እድለኛ ካልሆክ ደግሞ በፒያሳ በአንደኛው መጠጥ ቤት ከአንድ ጠጪ በተወረወረ ሸራፋ ብርጭቆ ጭንቅላትህን ትተረተራለህ፡፡ ከብሔራዊ ሉቶሪ ፊትለፊት እድለኛ ያልሆኑ ሰዎችን የሚያጉር የአራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ ጣብያ አለልህ፡፡ አዳርህ  የተጠቀሙበትን ለ‹‹ሸሌ››አልከፍልም ካሉ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር ይሆናል፡፡ ጠዋት የዋስ መብት ተሰጥቶህ አልያም መንግስታችን የይቅርታ ደብዳቤ አስፈርሞህ ወደቤትህ ታመራለህ፡፡

(ይቀጥላል)

Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email