የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያን ኳስ በትእግስት ተመለከቱ

ባሳለፍነው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ነበሩ፡፡ የደደቢትን እና የቅዱስ ጊዮርጊስን ጫዎታ ለ45 ደቂቃ በአበበ ቢቂላ ስቴድየም ተገኝተው ተመልክተዋል፡፡ ዐይተው ሲጨርሱ ለጋዜጠኞች እንዲህ አሉ፤  “በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለመጫወት የሚያስችል አቅም ያላቸው  ስድስት ተጫዋቾችን ዐይቻለሁ”

የምራቸውን ይኾን?

ሰር ዴቭ ሪቻርድስ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ፣ ከፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ ጋራ ተወያይተዋል፡፡ አቶ ኀይለማርያም ለሰር ዴቭ እንዲህ ብለዋቸዋል- “የኅብረተሰቡ የኳስ ፍቅር እና የእግር ኳሱ ደረጃ ተመጣጣኝ አይደለም፤ ስለዚህ እርዱን።”

ሰር ዴቭ በሸራተን አዲስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከተናገሩት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ቻናል ጋዜጣ እንደፃፈው፡፡

“ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያን ስጎበኝ በወታደር ነበር የታጀብኩት፤ በኢትዮጵያ ግን በሞተረኛ ብቻ ነው፡፡ ሰላማዊ አኗኗር ነው ያላችሁ፡፡”

“በልጅነቴ ለኢትዮጵያ ረኀብተኞች ገንዘብ አዋጣ እና አሰባስብ ነበር፡፡”

“ኢትዮጵያ ልመጣ ስል ጓደኛዬ ለምን ትሄዳለህ (እዚያ) ምን ታገኛለህ አለኝ፡፡”

ኢትዮ-ቻናል እና የፊት ገጹ

“ኢትዮ-ቻናል” ሲቆላመጥ “ቻናል” ይባላል፡፡ በአገር ቤት በሳምንት ሁለት ጊዜ ለመታተም የታደለ ጋዜጣ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የረቡዕ ዕትሙ “የዲያስፖራ ፖለቲካን” ክፉኛ የሚተቹ ጽሑፎችን እንጂ አንድም የተለመደ የጋዜጣ ዜና ይዞ አልወጣም፡፡ በፊት ገጹ የመጀመርያ ርእሰ-ጉዳይ ያደረገው “ኢትዮጵያን ሪቪው” የተሰኘውን ተነባቢ ድረ-ገጽን ነው፡፡ የድረ-ገጽን ባለቤት አቶ ኤልያስ ክፍሌ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያሳ አፈወርቂ ጋራ የተነሱትን ባለቀለም ፎቶ አትሞታል፡፡ የሚከተለውን ርዕስ ሰጥቶታል-“ጽንፈኛ ዲያስፖራዎች በሰሜን አሜሪካ እግር ኳስ ላይ የዘቀጠ ፖለቲካቸውን ይዘው ገቡ፡፡ የኢሳያስ ቅጥረኛ የኾነው ኢትዮጵያን ሪቪው ሰርጎ ገብቷል፡፡”

ከዚህ ዜና ባሻገር ብርቱካንን፣ ዶ/ር ያዕቆብን እና መኢአድን የሚተቹ የተለያዩ ገጾቹን የሸፈኑ ጽሑፎች ነበሩት፡፡ የቻናል ገጾች ትችት ብቻ አይደለም የያዙት፤ ሙገሳም አለበት፡፡ ለምሳሌ በፊት ገጹ “ማለቂያ የሌለው ደግነት” በሚል ርእስ ቢሊየነሩን ሼሕ አል-አሙዲንን የሚያሞካሽ ረዥም ጽሑፍ ከእነፎቶግራፋቸው አትሟል፡፡

ዶክተር መራራና ሰንደቅ ጋዜጣ

በሳምንት ረቡዕ የሚወጣው “ሰንደቅ” ጋዜጣ መድረክ በአንድዬው የፓርላማ አባሉ ላይ የያዘውን አቋም ያለፈው ሳምንት መሠረታዊ ጥያቄው አድርጎት ነበር፡፡ በርዕሰ-አንቀጹ “መድረክ በፓርላማ አባሉ ጉዳይ ግልጽ አቋሙን ለሕዝብ ያሳውቅ” ሲል ጠይቋል፡፡ በፖለቲካ ዐምዱ ደግሞ ዶክተር መራራን ይህንኑ ጥያቄ ብቻ እያነሳ ሰቅዞ ይዟቸው ነበር፡፡ ጋዜጣው ለዶክተሩ ካቀረባቸው አንድ ገጽ ሙሉ ጥያቄዎች ከ90 በመቶ በላይ የሚኾኑት በዚሁ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡በቀጥታም በተዘዋዋሪም፡፡ እርሳቸው ደግሞ “ሕዝብ የመረጠው ግለሰብ ፓርላማ አይግባ አላልንም፡፡” ሲሉ ጋዜጣውን ይሞግቱታል፡፡

ኾኖም “አንድ ሰው የስድስት ፓርቲ ጥምረት የኾነውን መድረክ መወከል አይችልም፡፡” የሚሉት ዶክተሩ “በባለፈው ፓርላማ 150 ኾነን ገብተንም አልቻልነውም” ሲሉ ለሰንደቅ ተናግረዋል፡፡ ስለርሳቸው የፓርላማ ልምድ በማውሳት “ቴአትር” የሚሉትን የፓርላማ ጫዎታ እየጠቃቀሱ ብቸኛው የመድረክ ተወካይ አቶ ግርማ ጥምረቱን በፓርላማ መወከል እንደማይገባቸው ይናገራሉ፡፡ “እኔ በባለፈው ፓርላማ ጠ/ሚኒስትሩ በሚገኙባቸውና ወሳኝ ጉዳዮችን ለሕዝብ ድምፅ ለማሰማት ሲፈለግ ብቻ በዓመት በአማካይ ሁለት ጊዜ ብገባ ነው፤ ከዚያ ውጭ የኢሕአዴግን ቴአትር ከመተወን ሌላ ሥራ ብሠራ ይሻላል ብዬ አልፎ አልፎ ነበር የምገባው፡፡” ይላሉ፡፡

ጥያቄ፡- አቶ ግርማ የተመረጥኩት በመድረክ ስም ስለኾነ ፓርላማ ውስጥ በመድረክ እቀጥላለሁ ቢሉ የምትወስዱባቸው እርምጃ ይኖራሉ?

ዶ/ር መረራ፡- ለምሳሌ (አቶ ግርማ) መድረክን እወዳለሁ…መድረክን አፈቅራለሁ ካሉ መብታቸው ነው፡፡ መድረክ ወክሎኛል ካሉ ግን መብታቸው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ግለሰቡ የኢሕአዴግን ትራንስፎርሜሽን በግላቸው እደግፋለሁ ብለው ድምፅ ቢሰጡ ያንን አንቃወምም፡፡ ትራንስፎርሜሽኑን በመድረክ ስም ነው የደገፍኩት ካሉ የእኛን አባልነት አቁመዋል ማለት ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የመድረክ ብቸኛ የፓርላማ አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ የዶክተር መረራን ሐሳብ በመንቀፍ “በመድረክ ስም ሐሳቤን ማንሸራሸሬን እቀጥላለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፤ ለሳምንታዊው አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ፡፡

ፓትሪያርኩ እና አወዛጋቢው ሐውልታቸው

የፓትሪያርኩ ሐውልት በ20 ቀናት ውስጥ እንዲፈርስ ሲኖዶሱ ከወሰነ በኋላ ውሳኔው በሰፈረበት ቃለ ጉባዔ ላይ ፓትሪያርኩ ላለመፈረም እያንገራገሩ እንደነበረ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ አውራምባ ጋዜጣ እንደዘገበው አቡነ ጳውሎስ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ” አሠርተዋል ያሏቸውን ሐውልቶች እንደ አስረጅ በመጥቀስ ለመሟገት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡

የአገር ቤት ምርቃት

 • “ጭብጨባ በልቼ የኖርኩ ሰው ነኝ” አብራር አብዶ ለሐምራዊ ጋዜጣ
 • “የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች ቁማሩን ተበሉ?” አውራምባ በወግ ዐምዱ
 • “ብዙውን ጊዜ መሰሪ ገፀ-ባሕርይን ወክለህ ትጫወታለህ፤ ከእውነተኛ ባሕርይህ ጋራ ይገናኛል?” አውራምባ ለአርቲስት ተስፉ ብርሃኔ ያቀረበው ጥያቄ
 • በአገራችን…ድሮም ቢኾን ሴቶች እና ወንዶች እኩል በተለያዩ ሥራዎች ይሳተፋሉ፡፡ ተመሳሳይ ደመወዝም ይከፈላቸዋል፡፡ ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ ወ/ሮ ነጻነት አስፋው የቀድሞው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ለአዲስ ልሳን
 • በግብረ-ሰዶማዊነት ይተዳደሩ የነበሩ ወጣቶችን መልሶ ለማቋቋም የፓናል ውይይት ይካሄዳል፡፡ አውራምባ ታያምስ
 • “እኔ የአዲስ ነገር ጋዜጣ አንባቢ ነኝ፤ ኅብረታችን በሰጣቸው ሥልጠናዎች ሁሉ የአዲስ ነገር ጋዜጠኞች እንዲሳተፉ አድርገናል፡፡…በጋዜጣቸው እንዳይጽፉ የሚከለክላቸው ወገን አልነበረም፡፡… መንግሥት ጋዜጣ ሲዘጋ ዝም እንደማንለው ሁሉ እነዚህ ግለሰቦች ጋዜጣውን እንደቀልድ ሲዘጉት በማየታችን አዝነናል፡፡” አቶ አንተነህ አብረሃም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ኅብረት ፕሬዝዳንት ሰንደቅ ጋዜጣ “አዲስ ነገር ሲዘጋ መንግሥትን የሚወግን አቋም ለምን አንጸባረቃችሁ” ብሎ ለጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡፡
 • “የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ የሠርቶ ማሳያ ሙከራ የሚካሄድበት የአርሶአደር ማሳ አይደለም፡፡” ኢትዮ-ቻናል እና ሰንደቅ ጋዜጦች በተመሳሳይ ቀን “ሽሽጉ ከሸጎሌ” በሚል ስም ያተሙት ዶ/ር ያዕቆብን የሚተች ጽሑፍ፡፡
Twitter Digg Delicious Stumbleupon Technorati Facebook Email

2 Responses to “የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ?”

 1. አይ ሰር ዴቭ የምር ለፕሪሚየር ሊጉ የሚመጥኑ 6 ተጫዋቾችን አይቻለሁ አሉ? ወይስ ዶሮን ሲያታልሏት ነገር ነው?

  የቻናል ነገር ምንም አስተያየት አያስፈልገውም! በቅርቡ ቻናል ኢ የሚባል ልማታዊ ፣ አላሙዲናዊ እና ታሪካዊ የመዝናኛ ቻናል (በቲቪ) እንጠብቃለን እንደምናየው ቢዝነስ ጦፎለታል ታምረኛው ሳሚ,,,

  አቶ ግርማ,,, ዝም ብለው ፓርላማ ገብተው ደሞዝ ቢበሉ ጥሩ ይመስለኛል የስነ ስዕል ፍቅር እና ፍላጎት ካላቸው በ 5 ዓመት ልምምድ አፈ ጉባኤውን ቁጭ ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ አልጠራጠርም ዋናው ተገቶ መለማመድ ነው! እንዲሁም መጸለይ!

  ብጹዕ እንጀራ አባታችን ይህን ያህል የሃውልት ፍቅር እንዳላቸው እስከ ዛሬ ድረስ አልገባኝም ነበር:: መስቀል አደባባይ ተደንቅረው የነበሩትን ሁለት የአዕዋፍ ዝርያዎች (እስከ ዛሬ ዶሮ ይሁኑ ፓሮት አልገባኝም) ቤታቸው በር ላይ የሰቀሏቸው ለካ ለሃውልት ካላቸው ፍቅር የተነሳ ነው? እርግጠኛ ነኝ ፓትርያርክ ባይሆኑ ኖሮ የሙታን ሃውልት ቀራጭ ይሆኑ ነበር:: ለማንኛውም አይዞት! አደባባይ ያቆሙት ሃውልት ቢፈርስም በልባችን ያቆሙት ሃውልት ለዘለዓለም አይፈርስም:: እንወዶታለን! ስጋ ስውዓት!

  አቶ አንተነህን,,, ጋዜጠኛ በሌለበት ሃገር የጋዜጠኞች ኅብረትን የሚመሩ አስማተኛ መሪ ብያቸዋለሁ!

 2. When I was home,My best friends were the local newspapers…. In the years 1999 to 2009,I have come across various news papers…i mean many of them… I used to read party newspapers like ‘abyotawi democracy’,newspapers who stayed long REPORTER,newspapers who were very racist like ADDIS ZENA…. BUt Beyond alll I hated two of them… IFTIN and ETHIOCHANNEL!…I would say they don’t know what they do!… they are full of silly hearsays…. I regereted a lot when I paid 5 Birr to read Ethiochannel the first time!…A year back,Addis neger became my favorite and didn’t stay long(with all due respect,I can say that the Addis neger Personnel arenot as rational as they were while they were in Ethio… I mean I am noticing some bias).Hate Ethiochannel!

Leave a Reply

You must be logged in to post a comment.