በቅርቡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህኅበር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ዓመታዊውን አለም አቀፍ ኮንፈረንስ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ስብሰባው ከሌሎች አመታት በተሻለ በጥራትም ሆነ በብዛት ወረቀቶች የቀረቡበት በመሆኑ የሚደነቅ ነበር፡፡
በስብሰባው ላይ ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ዋነኛ ትኩረት የነበረው የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገትና የወደፊት አቅጣጫ፣ እንዲሁም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እና ከገጠር ወደ ከተማ ተደረገ የተባለውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የሚመለከት ነበር፡፡
በርካታዎቹ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡት በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩትና በአቶ ነዋይ ገ/አብ በሚመራው የኢትዮጵያ የልማት ምርምር ተቋም ትብብር በሚመራው የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ድጋፍ ፕሮግራም ተመራማሪዎች ነው፡፡ ጥናቶቹ በበለጠ በባለሙያዎቹ ሊተነተኑ እና ክርክር ሊደረግባቸው የሚገቡ ቢሆንም፣ እንደ ታዛቢ በጣም አነጋጋሪ የሆኑ ሁለት ጉዳዮችን ላንሳ፡፡
የመጀመሪያው የግብርና ምርታማነትን የሚመለከት ነው፡፡ ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት የግብርና ምርታማነት ዕድገት ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ነው፡፡ ገበሬው የተሻሻሉ የምርት ግብዓቶችን የመጠቀም ፍላጎቱም እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን፣ ከግብርና ልማት ሠራተኞች ጋር ያለው ትብብርም አመርቂ አይደለም፡፡ እውነታው እንዲህ ከሆነ፣ ጥያቄው፣ “በየቀኑ የሚደሰኮርልን ተስፈንጣሪ የምርት ዕድገት ከየት መጣ?” ነው፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ጉዳይ እውነቱን ሊነግረን አይፈቅድም፤ ምርታማነት መቀነሱ ሲገለጽ ደግሞ የታረሰው መሬት በእጅጉ በመጨመሩ ምርታችንም ጨምሯል ይለናል፡፡ ምርታማነት እንዲህ እያሽቆለቆለ ባለበት ሁኔታ የግብርና ምርት ለአምስት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ በ8.5 በመቶ ዕድገት እንዲያሳይ የታረሰው መሬት መጠን ምናልባትም በእጥፍ መጨመር ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ ይህ እንዳልሆነ እኛም ካድሬዎቹም እናውቀዋለን፡፡
ታዲያ ችግሩ ምን ይሆን? የተለያዩ መላ ምቶች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ ይህን ተቃርኖ ያመጣው የኢሕአዴግ ቀሽም የውሸት ስታትስቲክስ ነው፡፡ ውሸቱ እድገት ሳይኖር አለ መባሉ አይመስለኝም፤ አለ የሚባለው ዕድገት እጅግ የተጋነነ መሆኑ እንጂ፡፡ ቀሽምነቱ ደግሞ የሚመስል ውሸት መዋሸት አለመቻሉ ነው፡፡ ማጣፊያው ያጠረው፣ ድሮም የነበሩት የምርታማነት ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ እንዲያውም ብሶባቸው ሳለ አደግን ለማለት ከመቸኮሉ የተነሳ የምርቱን መጠን በእጥፍ እጥፉ ጨምሯል ብሎ የውሸት አኀዝ ማቅረቡ ነው፡፡ ምናልባት ከዋሹ አይቀር ምርታማነቱም ጨምሯል ብለው ሊያሞኙን ቢሞክሩ ሳይሻላቸው አይቀርም ነበር፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ ኢኮኖሚው ምን ያህል /በተለይ ከገጠር ወደ ከተማ/ መዋቅራዊ ሽግግር አድርጓል የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድም በካድሬዎቹ የሚቀርብልን መረጃ ከአገሪቱ ጠቅላላ ገቢ የግብርና ድርሻ ወርዶ 42 በመቶ ስለደረሰ እና የአገልግሎት ዘርፉ ስለበለጠው፣ ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር እንዳደረገ ያሳያል የሚል ነው፡፡ በተጨማሪም በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ በመታየቱ ከዋና መንገድ በአጭር ርቀት ላይ የሚገኙ ቦታዎች ቁጥር ጨምሯል፣ ስለሆነም ሀገራችን ከገጠርነት ወደ ከተማነት በመቀየር ላይ ነች ይባላል፡፡ ይሁንና፣ ይህን ለማሳየት የሚቀርቡት ጥናቶች ራሳቸው እንደሚያረጋግጡት፣ የግብርናው ድርሻ ዝቅ ብሏል ቢባልም አሁንም 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚተዳደረው በግብርና ነው፡፡ 84 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረውም በገጠር ነው፤ ስለሆነም መዋቅራዊ ሽግግር ሲያልፍም አልነካን፡፡ በተጨማሪም የኢንዱስትሪው ዘርፍ የዕድገት መጠን የረባ ለውጥ አላሳየም፡፡ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል የሚባለው የአገልግሎት ዘርፍ መነሻው የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ነው፡፡ ይህም አሁን ባለው መጠን ሊቀጥል ስለማይችል መንግሥት እጅ ያጠረው ጊዜ ዘጭ ብሎ የሚወርድ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የመንግሥት ኢንቨስትመንት ከኢኮኖሚው ቢወጣ እሱን ተክቶ ኢኮኖሚውን ቀጥ አድርጎ የሚይዝ የግል ዘርፍ የለንም፡፡ ስለሆነም አለ የሚባለው ዕድገት እንኳንስ መዋቅራዊ ሽግግር ሊያመጣ፣ የሚጨበጥ እና ዘላቂ እድገት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
ይህን ስል ግን የኢኮኖሚ ዕድገት የለም እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ እድገት አለ፣ ግን እንደሚባለው የተጋነነ አይደለም፡፡ በትምህርት፣ ጤናና መሠረተ ልማት ላይ ብዙ ወጪ ተደርጓል፣ ድህነት ተኮር ስራ ተሰርቷል፤ ነገር ግን ግብታዊ እና ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ እንቅስቃሴ በመሆኑ ከፍ ያለ የጥራት ችግር ታይቷል፡፡ ግብታዊነቱ ጎልቶ የሚታየውም አሁን ያለው ሁኔታ በረዥም ጊዜ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው አንድምታ በደንብ አለመታሰቡ ነው፡፡
በሌላ አነጋገር አሁን የያዝነው መንገድ የት እንደሚያደርሰን የተሟላ ስዕል የለም፤ ከብዥታ በቀር፡፡ የመንገድ፣ የኃይል፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎትን ሽፋን መጨመሩ ጥሩ ነው፡፡ ግን ከዚያ በኋላስ? የምናስመርቀውን በመቶ ሺህ የሚቆጠር ባለሙያ የሚቀጥር የግል ዘርፍ አለን? ግማሹ ባለሙያ ስራ ፈጣሪ ሆኖ ባለሀብት እንዲሆን የተመቻቸ ሁኔታ አለን? የቁጠባ እና የኢንቨስትመንት ሁኔታችን ምን ይመስላል? ምርታማነቱ ያሽቆለቆለ እና የራሱን ሕዝብ መመገብ ያቃተው ግብርና ይዘን እንዴት ነው የአግሮ ኢንዱስትሪ አብዮት የምናካሒደው? በመንግሥት የሚደጎሙና መወዳደር የማይችሉ አነስተኛና ጥቃቅን ማህበራትን ይዘን እንዴት ነው ኢኮኖሚውን የሚለውጥ የሀገር ውስጥ ባለሀብት እንዲፈጥሩ የምንጠብቀው? ለመሆኑ የረባ ኢንዱስትሪ አለን? ከአየር ባየር ነጋዴዎች፣ ከገዢው ፓርቲ ድርጅቶችና ጥቅመኛ ባለሀብቶች ውጪ ይህ ነው የሚባል የግል ዘርፍ ባጭር ጊዜ ይኖረናል? የምናሰብው አብዮት በውጭ ኢንቨስትመንት ሊመጣ ይችላል? እነዚህን ጥያቄዎች ለማንሳት ኢኮኖሚስት መሆን የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ለመልሱ ግን የዘርፉ ባለሙያዎች ትንተናና አስተያየት ወሳኝ ነው፡፡
የኢኮኖሚ ለውጥን ማቀድ የአገልግሎት ሽፋንን እንደማሳደግ ቀላል አይደለም፤ እንዲህ አይነቱ ለውጥ የብዙ ተዋናዮች እንቅስቃሴ ድምር ውጤት ስለሆነ፡፡ ኢህአዴግ በመንገድ፣ በትምህርትና በጤና አገልግሎት ማደግ ሲኩራራ ዋናውን ጉዳይ የዘነጋው ነው የሚመስለው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ወቅታዊው አሳሳቢ ጉዳይ ስለኢኮኖሚው እውነተኛና አስተማማኝ መረጃ የሚገኘው እንዴት ነው? የሚለው ነው፡፡ ብቸኛው የመረጃ ተቋም የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በሆነበትና ከዚያ የሚገኘው መረጃ እርስ በርሱ በሚቃረንበት ሁኔታ እንዴት አድርገን ስለ ኢኮኖሚው ትክክለኛ ስዕል ማግኘት እንችላለን? የኢኮኖሚክስ ትንተናውስ ውሸትን ከማጋለጥ አልፎ እውነታውን ምን ያህል ሊያሳየን ይችላል? የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፤ እስቲ ያለንን ተስፋ ንገሩን።