የጠፋው ትውልድ [አንድ ለቅዳሜ]
“የጠፋው ትውልድ” የሽግግር ዘመኖች ትውልድ ነው፤ ለዚያውም የከሸፉ ሽግግሮች። ይህ ጠቃሚ ጎኖች ቢኖሩትም ጉዳቶችም አሉት። አንዱ ጉዳቱ ትውልዱ በፖለቲካው ውስጥ አሻራውን የሚተውበት እድልና ጊዜ ማጣቱ ነው። ሆኖም ይህ ትውልድ ደርግ እና ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ መኖር ያልነበረባቸው፣ ድጋሚም መምጣት የሌለባቸው የፖለቲካ ስርአቶችና አመራሮች መሆናቸውን ኖሮ አይቷቸዋል። ይህ ትውልድ ሁሉንም ፖለቲካዊ ጽንፎች በአያቶላዎቹ ሲተነተኑ ሰምቷል፤ በፊት አውራሪዎቹ ሲተገበሩ አይቷል፣ ኖሯቸዋልም። ይህ ትውልድ የፖለቲካ ሐላፊነቱን ካልተወጣ አገራችን አዳዲስ ደርጎች እና አዳዲስ ኢህአዴጎችን ማስተናገዷ እንደማይቀር እሰጋለሁ። ያን ጊዜ ብዙ መንግሥቱዎች ወይም ብዙ መለሶች ይወሩናል፤ አያርግብንና! “የጠፋው ትውልድ” ከዚህ ልምድ የሚቀስመው ትምህርት አገሪቱን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚያሸጋገር ቀመር እና ፖለቲከኞች እንዲያፈራ ይረዳው ይሆን?
ይህ ትውልድ በመሠረቱ ስለ አገርም ይሁን ስለ ፖለቲካ ያለው አመለካከት በቅድሚያ የተቃኘው “እናት አገር” ወይም “ኢትዮጵያ” በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ ነው። የ“እናት አገር” ገናና ታሪክ፣ ሉአላዊነት እና አንድነት የፖለቲካው እንብርት ነበር። ስለ እናት አገር ለተከታዩ “አዲሱ ትውልድ” የሚተርፍ አክብሮትና ፍቅር ያደረበትም ለዚህ ነው። የአክብሮቱና የፍቅሩ መገለጫ ሁሉ “ትክክል” መሆኑን ግን እጠራጠራለሁ። አብዛኛው በተለይም ከተማ ቀመሱ በ”እናት አገር” ርዕዮተ ዓለማዊና ባህላዊ መሠረት ቢቀረጽም፣ በሒደት “በብሔረሰብ መብት” አስተምህሮ መማረክ የጀመሩ ቁጥራቸው የማይናቅ የትውልዱ አባላት አሉ።

15 January 2011 